እግር ኳስ በስሜት ወይስ በስሌት?

0
34

ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ደማቅ አሻራቸውን ካሳረፉ ባለሙያዎች ውስጥ አንዱ ናቸው:: ኢትዮጵያ ከመሠረተችው የአፍሪካ ዋንጫ ለ31 ዓመታት ከተራራቀች በኋላ ወደ መድረኩ እንድትመለስ ያስቻሏትም እኚሁ ባለሙያ መሆናቸው አይዘነጋም::

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ሲነሳ ሀገራችን የአህጉሩ እግር ኳስ መሥራች መሆኗ፣ ይድነቃቸው ተሠማን ያህል ሀገራዊና አህጉራዊ የዘርፉ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰው ማፍራታችንን ጠቅሰን የምንሸጋገረው ወደ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው ነው::

አሚኮ በኩር ከኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው ጋር ባደረገችው አጭር ቆይታ የሀገራችን እግር ኳስ ውድቀት መንስኤው ምንድነው? መፍትሔውስ? በሚሉ ሀሳቦች ዙሪያ ምላሻቸውን አግኝታለች::

“የሀገራችን እግር ኳስ እንደ ካሮት ወደ ታች ለማደጉ ምክንያቱ ዘርፈ ብዙ ነው” ያሉት ኢንስትራክተሩ በዓለማችን ላይ እግር ኳስ ሳይንስ፣ ጥበብ እና ቢዝነስ ስለመሆኑም ያለን መረዳት ዝቅተኛ ነው ብለዋል::

የኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻውን ገለጻ ከእግር ኳስ ነባራዊ ሁኔታ ጋር እናዛምደው ካልን በእርግጥም እግር ኳስ እሳቸው እንዳሉት ሳይንስ፣ ጥበብ እና ቢዝነስ በስፋት የሚስተዋሉበት ነው:: የዓለም እግር ኳስ ኢንስትራክተሩ ካሉት በተጨማሪ የዓለም የሃብት ሚዛን መገለጫ እና የሀገራት የፖለቲካ ነጸብራቅ መሆን ከጀመረም ዓመታት ተቆጥረዋል::

የዓለም እግር ኳስ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታው ተመዝኖ አሁን ላይ በሀገራት  እየተመራ ያለበት መንገድም  ዘልማዳዊ መሆኑ ቀርቷል:: እግር ኳስ ጥበብ ስለመሆኑም መገለጫው በብዙ የዓለም ሀገራት ዘንድ በርካታ የእግር ኳስ ታዳሚዎች መኖራቸው እና በመድረኩ (ሜዳው) ላይ የሚተውኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ  ባለሙያዎች መፈጠራቸውንም እንደ አብነት ማንሳት ይቻላል::

ኢንስትራክተር ሰውነት እግር ኳስን ቢዝነስ ነው ማለታቸውም ቢሆን ለዘርፉ የሚበጀተው በጀት፣ ለተጨዋቾች የሚከፈለው ክፍያ፣ ለስታዲየሞች ግንባታ የሚወጣው ወጪ፣ ከማስታወቂያዎች የሚገኘው ገቢ፣ ከደጋፊዎች የሚሰበሰበው ገንዘብ፣ ከስታዲየሞች መግቢያ የሚገኘው መዋዕለ ነዋይ እና ሌሎች በቢሊዮን የሚቆጠሩ ወጪና ገቢዎች የዘርፉን ቢዝነስነት አመላካች ናቸው::

ኢንስትራክተር ሰውነት የኛ ሀገር እግር ኳስ ከድጡ ወደ ማጡ ለመጓዙ ምክንያቶቹ ብዙ ቢሆኑም ዋና ዋናዎቹ ያሏቸው ግን እግር ኳሳችን  የሙያው ባለቤት ባልሆኑ ግለሰቦች መመራቱ፣ አሠልጣኞች በቂ ዕውቀት የሌላቸው መሆኑ፣ ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ማነስ፣ የአሠለጣጠን ዘይቤዎቻችን ሳይንስንና የወቅቱን ቴክኖሎጂዎች ያልተከተሉ መሆናቸው፣ ታዳጊ ሕጻናት ላይ ያተኮሩ ሰፊ ሥራዎች አለመኖራቸው፣ በዘርፉ ውስጥ የሚታይ ዘረኝነት፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎች በበቂ ሁኔታ አለመኖራቸውና ሌሎችም የውድቀታችን መንስኤዎች መሆናቸውን ገልጸዋል::

“በኛ ሀገር እግር ኳስ ተጨዋች የሚገዛው ወደ ገበያ ሄደን ደስ ያለንን ሸሚዝ እና ሱሪ በምንገዛው መልኩ ነው” ያሉት ኢንስትራክተሩ በራስ ጥረት ታዳጊዎችን ማብቃት ላይ የሁላችንም ድክመት ይስተዋላል ብለዋል:: በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውስጥ ብዙ ልምድ ያላቸውን ተጨዋቾች በብዙ ብር አስፈርሞ በማሰለፍ ዋንጫን ማሳካት ጥሩ ቢሆንም ለሀገሪቱ እግር ኳስ እድገት ግን ፋይዳው ይሄ ነው የሚባል አይደለምም ብለዋል::

እግር ኳስ በባህሪው ምን ይፈልጋል? ለሚለው ጥያቄ መልስ መስጠት የማይችሉ የእግር ኳስ አሠልጣኞች እና የእግር ኳስ አመራሮች የሀገራችንን እግር ኳስ በምንም መልኩ ሊያሳድጉት እንደማይችሉም ኢንስትራክተር ሰውነት ገልጸዋል::

የሀገራችንን እግር ኳስ ማሳደግ ስናስብ ሌሎች ሀገራት እግር ኳሳቸውን እንዴት አሳደጉት? ብሎ ማሰብን ይጠይቃል ያሉት ኢንስትራክተሩ የእግር ኳስ ሙያ ቅንነትንና ታማኝነትን እንደሚፈልግም አንስተዋል:: ለሀገር ክብር ሲባል የአቅምን ያህል አስተዋጽኦ ማድረግም ከእግር ኳስ ተጨዋቾች፣ ከአሠልጣኞችና ከዘርፉ ባለሙያዎች የሚጠበቅ ስለመሆኑም አንስተዋል::

የሀገራችን እግር ኳስ ለምን አላደገም? ለሚለው ጥያቄ በባለሙያዎች ባለመመራቱ፣ በታዳጊዎች ላይ ባለመሠራቱ እና ለሙያው ብቁ የሆኑ አሠልጣኞች ባለመኖራቸው እንደምንለው ሁሉ ለእግር ኳስ የሚያስፈልጉ መሠረተ ልማቶች ባለመሟላታቸው የሚለው እሳቤም በቀዳሚነት መቀመጥ እንዳለበት ኢንስትራክተሩ ገልጸዋል::

ለሀገራችን እግር ኳስ እድገት በመሠረታዊነት የሚያስፈልጉት የበቁ ባለሙያዎች፣ ታዳጊዎችን ያማከለ አሠራር እና የእግር ኳስ መሠረተ ልማቶች ናቸው ካልን በዚህ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት የሚጠበቅባቸው ደግሞ የሀገሪቱ መንግሥት እና ባለሀብቶች መሆናቸውን ባለ ሙያው ገልጸዋል::

ከምንም በላይ እግር ኳሳችን በታዳጊ ሕጻናት ላይ ማተኮር አለበት የሚሉት ኢንስትራክተር ሰውነት ጊዜ ወስዶም ቢሆን የሀገራችንን እግር ኳስ በጽኑ መሠረት ላይ ማቆም እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል:: ኢንስትራክተሩ ሙያዊ አስተያየታቸው ለሁለቱም ጾታዎች እና በሁሉም የዕድሜ እርከን ላይ ለሚገኙ የእግር ኳስ ተጨዋቾች መሆኑንም ጠቁመዋል::

በእግር ኳስ ታሪካቸው ከሀገራችን ያነሱ የነበሩ የአፍሪካ ሀገራት በምን መልኩ ሠርተው ቀደሙን? የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጅቡቲ እና በሶማሊያ አቻዎቹ እንዴት መፈተን ቻለ? የኬኒያ እና የሱዳን እግር ኳስ ማንሰራራት ሲችል የኛን ምን ነካው? ስለምን እግር ኳስን ቀድመን የጀመርን ኢትዮጵያውያን አብረውን ከጀመሩት ሀገራት በውጤት አነስን? ብለን በቁጭት መሥራትም ይጠበቅብናል ብለዋል ኢንስትራክተሩ::

“እግር ኳስ በስሜት ሳይሆን በስሌት መመራት አለበት” ያሉት ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው በኛ ሀገር ያለው እግር ኳስ ግን በዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎችም ሆነ በሌሎች የዘርፉ ሙያተኞች እንደማይደገፍ ጠቁመዋል:: እግር ኳሱ በባለሙያዎች የማይመራ ሆኖ ከቀጠለ ደግሞ ወደፊት ከአሁኑም የባሰ የከፋ ውጤት እንደሚመዘገብ ጠቁመዋል::

ብሔራዊ ቡድንን ያህል ትልቅ ነገር በቂ የአሠልጣኝነት ሙያ በሌላቸው ሰዎች እንዲመራ ማድረግ በሀገራችን እግር ኳስ እና በደጋፊዎች ላይ ሁሉ መቀለድ ነው ሲሉም አብራርተዋል::

ኢንስትራክተር ሰውነት “አንድ የግብርና ባለሙያ የሆነ ሰው እግር ኳስን ከልቡ ሊወድ፣ ትላልቅ የውጪ ክለቦችን ሊደግፍ ወይም ስለ አሰላለፍ እና አጨዋወት ትንታኔ ሊሰጥ ይችላል፤ ያ ሰው ግን በፍጹም የአንድ ክለብ አሠልጣኝ ሊሆን አይችልም” ብለዋል:: ምክንያታቸውን ሲያቀርቡም እግር ኳስ መመራት ያለበት በዘርፉ በቂ እውቀት ባላቸው ሰዎች መሆኑን አንስተዋል::

“ብዙ ሀገራት በእግር ኳሳቸው እና በታዳጊዎች ላይ በርካታ መዋዕለ ነዋይ አፍስሰው ውጤታማ ሆነዋል” ያሉት ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው በኛ ሀገር ግን ለእግር ኳሱ በርካታ ገንዘብ እየወጣ ውጤታማ አለመሆናችንን ገልጸዋል:: ኢንስትራክተሩ አሁን እየተከተልን ያለው አሠራር ውጤታማ ካላደረገን የሌሎች ሀገራትን ጥሩ ተሞክሮዎች መከተል እንዳለብንም ጠቁመዋል::

በሀገራችን እግር ኳስ ተጨዋቾች “ፕሮፌሽናል” መሆን ላለመቻላቸው ምክንያቱ በእግር ኳሳችን ላይ እየተተገበሩ ያሉ ነገሮች ትክክል ባለመሆናቸው እንደሆነም ባለሙያው አሳስበዋል:: በአጠቃላይ የሀገራችን እግር ኳስ የሕዝብን ፍላጎት የሚያረካ እና በአንድነት የሚያስተሳስር ገመድ እንዲሆን እንደ ሀገር ብዙ የሚጠብቁን የቤት ሥራዎች እንዳሉብንም ገልጸዋል::

(እሱባለው ይርጋ)

በኲር የመስከረም 26 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here