ኦቦዶ ኘሪንሲፔ ተፈጥሯዊ ፓርክ

0
63

ፓርኩ በ2006 እ.አ.አ በሰኔ ወር በዱር እንስሳት እና እፅዋት ሀብቱ ከደሴቷ ስፋት 45 በመቶ በመያዙ፤ በዓለም ዓቀፍ የብዝሃ – ህይወት ጥበቃ ከዓላማው ጋር የሚጣጣም በመሆኑ እውቅና ተሰጥቶታል::

ለፓርኩ መመስረት የኘሪንሲፔ የደን ስነምህዳር ጥበቃ ሊጠፉ የተቃረቡ የእንስሳት እና እፅዋት ዝርያዎችን እና መኖሪያ ቀጣናዎችን መጠበቅ የመጀመሪያ ተልኮው ነው:: በሁለተኛ ደረጃ ከቀጣናው የሚፈልሱ እንስሳትን  መንከባከብ፣ የዝግመት ለውጥ (ኢቮሉዊሽን) ሂደቶችን ቀጣይነት ማረጋገጥ ሀብቶቹን በስርዓት መጠቀም እና ማስተዋወቅ በሶስተኛነት ተቀምጧል፣ የደኑን ተለዋዋጭነት ከዘላቂ የሀብት አጠቃቀም አንፃር ማስተዋወቅ እና የሰዎን እንቅስቃሴ በደን ስነምህዳሩ ላይ ተፅእኖውን መገምገም እንዲሁም የአካባቢውን ተፈጥሯዊ እና ባህላዊ እሴቶች በማይጐዳ መልኩ ለነዋሪው ማህበረሰብ ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ማስተዋወቅ ለፓርኩ የማእዘን ድንጋይ ሆነው ተቀምጠዋል::

የኘሪንሲፔ ተፈጥሯዊ ፓርክ የደቡብ ተዳፋት፣ ደረቅ የባህር ዳርቻ፣ የወይራ ደን፣ የባህር ላይ ቀጣናን ያካተተ ነው:: በዚህም በህግ ቁጥር 10 እና 11 1999 እ.አ.አ ጥብቅ የእፅዋት እና እንስሳት ተፈጥራዊ ቅርስ ሆኖ ለመመዝገብ ሁኔታዎችን አመቻችቷል-የደሴትዋ አስተዳደር:: በ2006 እአአ በብዝሀ- ህይወት ሀብት ዓለም አቀፍ እውቀና ተችሮታል::

የኘሪንሲፔ ተፈጥሯዊ ፓርክ በሁለት መልካዓም ድራዊ ልዩነት ያላቸው ቀጣናዎች – የባህር ዳርቻን ጨምሮ 7,124 ሄክታርን ይሸፍናል:: በሰሜን ምእራብ የደሴቷ ቀጣና 229 ሄክታር የወይራ ዛፍ ደን ተንሰራፍቶበትም ይገኛል::

ተፈጥሯዊ ፓርኩ ለጥበቃ እና ቁጥጥር ያመች ዘንድ በተለያዩ የአስተዳደር ቀጣናዎች ተከፍሏል:: የጐብኚዎች እንቅስቃሴም ቁጥጥር እና ጥበቃ ይደረግበታል::

የፓርኩ የዓየር ንብረት ሞቃት ርጥበታማ ሲሆን ዝናባማው ወራት ከሰኔ እስከ መስከረም ያሉት መሆናቸው ተለይቷል:: ቀዝቃዛ እና ደረቅ ወራት ደግሞ ጥር እና የካቲት ናቸው::

ዓመታዊ አማካይ የዝናብ መጠን ዝቅተኛ ሰሜን እና ሰሜን ምስራቅ ቀጣናዎች 2000 ሚሊ ሊትር እንዲሁም በደቡባዊ ከፍታማ ቀጣናዎች 4000 ሚሊ ሊትር ተመዝግቧል:: ዓመታዊ አማካይ የዓየር ንብረቱም 25 ዲግሪ ሴልሺየስ ነው::

ኘሪንሲፔ ለደሴቷ ኗሪዎች እና ለብዝሃ ህይወቱ አስፈላጊ የሆኑ ሦስት ወንዞች አሏት:: ፓፓጊዮ ወንዝ ደግሞ ለዋና ከተማዋ ሳንቶ አንቶኒዮ ኗሪዎች የመጠጥ ውኃ ምንጭ ሆኖ ያገለግላል::

ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ባዮዳይቨርሲዳድ – ሲ ኤች ኤም. ኤስ ቲ፣ ኘሪንሲፔ ኮሌክሽን ድረ ገጽ እና ሪፋንድ ሬይንፎረስት ድረ ገፆችን ተጠቅመናል::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የነሐሴ 12 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here