በ2017/2018 የምርት ዘመን ከዘጠኝ ሚሊዮን ኩንታል በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት ዕቅድ አውጥቶ ወደ ሥራ መግባቱን የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ አስታውቋል። ዝግጅቱ በዞኑ ያለውን የአፈር ለምነት ለማሻሻል እና የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ያለመ ነው።
የባሶና ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር አበበ በዛ በጓሯቸው ጉድጓድ በመቆፈር እና የግብርና ባለሙያዎች በሚሰጧቸው ድጋፍ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርታቸውን እያሳደጉ ነው።
የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አበበ ጌታቸው እንደገለጹት መምሪያው የአፈር ለምነት ንቅናቄ መድረኮችን በማካሄድ እና የተፈጥሮ ማዳበሪያዎችን በማምረት ላይ ይገኛል። በተለይም መደበኛ ኮምፖስት፣ በርሚ ኮምፖስት እና ባዮ ሳለሪ ኮምፖስት በስፋት እየተመረቱ ነው።
መምሪያው እስካሁን ስምንት ሚሊዮን 455 ሺህ ሜትር ኩብ ኮምፖስት የተዘጋጀ ሲሆን በዚህም የዕቅዱን 98 በመቶ ማሳካት ችሏል።
መምሪያው እንዳሰታወቀው በዞኑ በምርት ዘመኑ ከሁለት መቶ ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተፈጥሮ ማዳበሪያ ይሸፈናል ተብሎ ይጠበቃል። የተፈጥሮ ማዳበሪያን መጠቀም የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ዋጋ መናር እና የአቅርቦት እጥረት ላስከተለው ችግር ዘላቂ መፍትሄ እንደሆነ መምሪያው ገልጿል።
የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅቱ በዞኑ ያለውን የግብርና ምርታማነት ለማሳደግ እና የአርሶ አደሮችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ነው የተገለጸው።
(ሰናይት በየነ)
በኲር የመጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም