ከሁሉም አካላት የሚጠበቅ ኃላፊነት

0
44

ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ክብረ በዓላት የቱሪዝም ዘርፉን ለማስፋፋት ከሚያግዙ ተግባራት መካከል ዋናዎቹ ናቸው:: ቱሪዝምም ለሀገር እድገት እና ልማት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን ለተቋማት እና ለግለሰቦች የነፍስ ወከፍ የገቢ ምንጭ በመሆን ያገለግላል::

በተጨማሪም የማህበረሰቡን እሴት፣ ባህል፣ ወግ፣ ልማድ እንዲሁም ሃይማኖታዊ ክዋኔ ለማስተዋዋቅ እና ለማጎልበት ሚናው የጐላ ነው:: ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ያስመዘገበቻቸው በርካታ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ  የመስህብ ሀብቶች ይገኛሉ::  በአማራ ክልል:: የአማራ ክልል በዩኔስኮ ከተመዘገቡት የመስህብ ሀብቶች በተጨማሪ በርካታ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ የመስህብ  ኩነቶች ባለቤትም ነው:: ይሁንና ክልሉ በዘርፉ እያገኘ ያለው ጥቅም ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም::

በመሆኑም ክልሉ ባለው የተፈጥሮ፣ ሰው ሠራሽ፣ የታሪክ፣ የሃይማኖት እና ባህላዊ ፀጋዎቹን ለመጠቀም እና የቱሪዝም ዘርፉን ለማስፋፋት ይረዳው ዘንድ ያሉትን ሀብቶች በአግባቡ ማስተዋወቅ፣ መንከባከብ እንዲሁም ለማህበረሰቡ በየወቅቱ መረጃ መስጠት እና ማነቃቃት ይኖርበታል::

በክልላችን የተለያዩ አካባቢዎች ከያዝነው የነሐሴ ወር አጋማሽ ጀምሮ የቡሔ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል፣ እንግጫ ነቀላ እና የከሴ አጨዳ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ኩነቶች ወይም ክዋኔዎች  በድምቀት ይከበራሉ:: በዓላቱ ሲከበሩም ዋነኛ መገለጫቸው የክልሉን ሕዝብ ባህል፣ ወግ፣  ልማድ፣ ማንነት፣ ተቀባይነት… በሚያሳይ መልኩ ነውና እነዚህን መገለጫዎች ማስቀጠል አለበት::

እነዚህን ክዋኔዎች በማክበር ማስቀጠልም ማህበራዊ አንድነትን ለማጠናከር እና ምጣኔ ሃብቱን ለማነቃቃት እንዲሁም አካባቢውን ለማስተዋዋቅ ይረዳል::

በዓላቱ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ትውፊትን በማጣመር የሚከናወኑ  በመሆናቸው ተቀባይነታቸው የጐላ ነዉ። ይህም  የቱሪዝም ዘርፉ እንዲያንሰራፋ፣  አካባቢውም ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት እንዲያመጣ  እና ለማህበራዊ መስተጋብር ሁነኛ ፋይዳ  አላቸው።

በመሆኑም በዓላቱ እና ክዋኔያቸው ሳይደበዝዙ እና ሳይበረዙ   በድምቀት ይከበሩ ዘንድ ከባለድርሻ አካላት እንዲሁም ከእያንዳንዳችን ትኩረት መስጠት እና ሰፊ ሥራ መሥራት ይጠበቃል::

የክልሉ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ከሰሞኑ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው የዘንድሮው በዓል መሪ ቃል “ባህላዊ እሴቶቻችን ለዘላቂ ሰላማችን፣ የነበርንበት፣ ያለንበት እና የምንደርስበት” የሚል ነው::

ክልሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ጐብኝዎች መዳረሻ ሲሆን ክብረ በዓላቱ ደግሞ የክልሉን ሕዝብ ባህል፣ ታሪክ፣ ትውፊት፣ ቅርስ… ማሳያ እና ማስመስከሪያዎች እንደሆኑ ቢሮው አውስቷል::  በዓላቱ በያካባቢዉ ሲከበሩ የክልሉ ሕዝብ የቀደመ የእንግዳ  ተቀባይነት ባህሉን በተግባር እንዲያሳይም ቢሮው  ጥሪ አቅርቧል::

የክልሉ ልዩ መገለጫ የሆኑትን እነዚህን በዓላት  ማክበር የማህበረሰቡን እሴት ለማስጠበቅ እና ትውልዱ  ጠንካራ የማንነት ስሜት እንዲላበስ በማድረግ ረገድ ሁነኛ ሚና ከመጫዎቱም  በተጨማሪ ለቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃትም አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነዉ።

በመሆኑም በክልሉ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከበሩ በዓላትን በወጉ  እንዲከበሩ እና ጐብኝዎችም  ወደየአካባቢዎች እንዲንቀሳቀሱ መረጃ በመስጠት፣ ድጋፍ በማድረግ እና በዓላቱ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፉ እንዲሁም ኩነቶቹ ወደ ቱሪዝም ገበያው እንዲገቡ  ያላሰለሰ ድጋፍ እና ትብብር ማድረግ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው::

በኲር የነሐሴ 12 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here