ከሁላችንም የሚጠበቅ ጉልህ ተግባር!

0
129

በአማራ ክልል በየጊዜው የሚከሰቱ ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ለዜጎች የምግብ ዋስትና መረጋገጥ ፈተና ሲሆኑ ይስተዋላሉ። ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እና ጎርፍ በሰብል ላይ የሚያደርሰው ጉዳት፣ የዝናብ እጥረት እንዲሁም ግጭት የዜጎች ሕይዎት እንዲፈተን፣ መሬቱም ፆም እንዲያድር ምክንያት ሆነዋል።

በዚህ ዓመት በሰሜን ወሎ ቡግና ወረዳ በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ምክንያት ከ110 ሺህ በላይ ወገኖች ለምግብ እጦት በመጋለጣቸው አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ አስፈልጓቸዋል። እነዚህ ወገኖች አስቸኳይ የሰብአዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የታወቀውም በአካባቢው አንፃራዊ ሰላም በመስፈኑ ነው።

በአማራ ክልል ከአንድ ዓመት በላይ የቆየው ግጭት የምግብ እጥረት ችግሮች ሲፈጠሩ   ድጋፍ የማድረጉን እንቅስቃሴ አዳጋች አድርጎት  የቆየ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን አንፃራዊ ሰላም በመስፈኑ በቡግና ወረዳ ለሚገኙ 110 ሺህ 563 ዜጎች የዕለት ደራሽ እርዳታ ማቅረብ ተችሏል።

ክልሉ ከአምስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ የሚታረስ መሬት እንዲሁም በርካታ አምራች የሰው ኃይል ያለው፣ 177 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ዓመታዊ  የዝናብ ውኃ የሚያገኝ ሆኖ ሳለ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እርዳታ ጠባቂ እጆች የሚታዩበት ሆኗል። ለዚህም መፍትሄ የራቀው ግጭት በቀዳሚ መንስኤነት ይጠቀሳል፡፡ በዚህ ግጭት ምክንያት ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው እየተፈናቀሉ እና መሬቱም  ፆም እያደረ ይገኛል። በአማራ ክልል ከ700 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች በመጠለያ እና በማሕበረሰቡ ውስጥ የሚገኙ መሆናቸው የችግሩን አሳሳቢነት ያሳያል።

ከግጭቱ በተጨማሪም ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሰብል ላይ ያደረሰው ጉዳት፣ጎርፍ እና የዝናብ እጥረት ዜጎች የምግብ ዋስትናቸውን እንዳያረጋግጡ ፈተና ሆነውባቸዋል። የዝናብ እጥረቱን ተከትሎ ባለፈው ዓመት በዘጠኝ ዞኖች ተከስቶ የነበረው ድርቅም ከአንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን በላይ አምራች እጆች እርዳታ ጠባቂ እንዲሆኑ አድርጓል፤ አርሶ አደሩን የምግብ እጥረት እንዲገጥመው፣ ሕፃናት ከት/ቤት እንዲቀሩ፣እንስሳትም እንዲሞቱ እና እንዲሰደዱ  ምክንያት ሆኗል።

በዚህ ዓመትም ድርቁ አሳሳቢ ሆኖ የቀጠለ ሲሆን ችግሩ ከበረታባቸው አካባቢዎች መካከልም ሰሜን ወሎ ዞን ይጠቀሳል። በዞኑ ያለው የእለት ደራሽ እርዳታ ጠባቂ ቁጥር ከአምናው በ80 በመቶ የቀነሰ ቢሆንም አሁንም በከፋ የምግብ እጥረት ውስጥ የሚገኙ ወገኖች አሉ። ይኸውም ሁለት ሺህ 294 ሕፃናት በአጣዳፊ የምግብ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ፣ በመካከለኛ ደረጃ የምግብ እጥረት ውስጥ እያለፉ የሚገኙ ደግሞ 39 ሺህ 156 ሕፃናት መሆናቸው ታውቋል። ከእነዚህ ሕፃናት መካከልም 49 በመቶ የሚሆኑት የሚገኙት  በቡግና ወረዳ ነው።

በአማራ ክልል ከአንድ ዓመት በፊት ጀምሮ በተከሰተው ግጭት የተነሳ በአካባቢው ለሚገኙ እርዳታ ለሚፈልጉ ሕፃናት አልሚ ምግቦችን በወቅቱ ማድረስ አልተቻለም ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን አንጻራዊ ሰላም በመስፈኑ ሕፃናትን ጨምሮ ለተቸገሩ እና የዕለት ደራሽ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች በዩኒሴፍ፣ በዓለም ምግብ ድርጅት፣ በቀይ መስቀል እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በኩል የቀረቡ ድጋፎች ወደ አካባቢው ደርሰው በመሰራጨት ላይ ይገኛሉ።

እርዳታ ለሚፈልጉ ወገኖች ፈጥኖ ባለመድረስ ምክንያት አንድም ሕይዎት እንዳይጠፋ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ ለዚህም ሁሉም አካላት  ትብብር ማድረግ አለባቸው።

ከዚሁ ጎን ለጎንም ችግሩ በዘላቂነት የሚወደገድበትን መንገድ መሻት ያሻል፡፡ ክልሉ ተስማሚ የአየር ንብረት፣በቂ የሚለማ መሬት እና በርካታ አምራች ኃይል ያለው እንደመሆኑ መጠን በምግብ ራስን ለመቻል ማልማት ላይ ከፍተኛ ትኩረት ማድረግ ለነገ የማይባል ተግባር ነው። ከድህነት የሚያወጡ የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ በመሥራት እና ምርት እና ምርታማነትን የሚጨምሩ የግብርና ሥራዎችን በርትቶ ማከናወን ያስፈልጋል። እርዳታ ሰጭዎችም ጊዜያዊ እርዳታ ከመስጠት ወጥተው በቋሚ የልማት ሥራዎች ላይ ድጋፍ እንዲያደርጉ አቅጣጫ ማሳየትም ከሁላችንም የሚጠበቅ ጉልህ ተግባር መሆን አለበት!

በኲር የታኅሳስ 21 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here