ከመሠረታዊ ወታደርነት እስከ   ረዳት ኮሚሽነር

0
95

“ገና ከመወለዴ በፊት ንጉሡን ለመጣል የሚደረግ የትጥቅ ትግል ነበር፤ እኔ ከተወለድሁ በኋላ ደግሞ የነበረውን አገዛዝ ለመጣል በነበረ ትግል ሌላ ጦርነት ቀጠለ፡፡ በ90ዎቹ ዓ.ም ደግሞ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ተከሰተ፤ ከዛ ቀጥሎ የትግራይ አሁን ደግሞ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ነን፡፡ ይሄ የሚያሳየው ሀገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በማያባራ ጦርነት ውስጥ በመሆኗ ለብዙኃኑ ሞት እና ጉዳት ዋናው ምክንያት መሆኑ ያሳዝነኛል!” በማለት ከልጅነቷ  ጀምሮ ዛሬ ለደረሰችበት ደረጃ ያለፈችበትን አስተማሪ የሕይወት ተሞክሮ ያጋራችን የአማራ ክልል ፓሊስ ኮሚሽን ኮሙኒኬሽን ረዳት ኮሚሽነር መሰረት ደባልቄ ናት፡፡

ረዳት ኮሚሽነር መሰረት ትውልድ እና እድገቷ ደቡብ ጎንደር ዞን በቀደመው አጠራር  ላይ ጋይንት አውራጃ በአሁኑ ንፋስ መውጫ ከተማ ነው፡፡  ትምህርት የጀመረችው በዚያው በንፋስ መውጫ ከተማ ነበር፡፡ የያኔዋ ታዳጊ ከ9ክፍል ወደ 10ኛ ክፍል በተዘዋወረችበት በ1982 ዓ.ም አካባቢያቸው ከደርግ አገዛዝ ነፃ የወጣበት ወቅት ነበር፡፡ ይህን ተከትሎም  ወላጅ አባቷ በኃይለ ሥላሴም ሆነ በደርግ ትልቅ ኃላፊነት ስለነበራቸው በወቅቱ በጡረታ ቢገለሉም  “ፊውዳል እና የኢሠፓ አባል ነዎት” በሚል መታሠራቸውን ታስታውሳለች፡፡

በተማሪነቷ  ጊዜ  መምህር ወይም የግብርና ባለሙያ የመሆን ምኞት የነበራት ረዳት ኮሚሽነር መሰረት  በወቅቱ የነበረው አስከፊ ጦርነት ነገሮችን ሁሉ እንደቀየራቸው ታስታውሳለች፡፡

የዛሬዋ ረዳት ኮሚሽነር መሰረት ደባልቄ ገና የ16 ዓመት ታዳጊ እያለች አባቷ መሳሪያ ይዘው ስትመለከት በጣም ትፈራ ነበር፡፡   ይሁንና የደርግ አገዛዝ በሚያደርሰው ተደጋጋሚ የአየር ጥቃት   በጣም የምትወዳት የልጅነት ጓደኛዋን በሰኮንዶች ከነጠቃት እና እሷም ለጥቂት ካመለጠች በኋላ በሩቅ ትፈራው የነበረውን የጦር መሳሪያ ታጥቃ ደርግን ለመጣል በአካባቢያቸው የሚንቀሳቀሰውን የታጠቀ ቡድን ተቀላቀለች፡፡

በወቅቱ የፓለቲካ ትምህርት እና ወታደራዊ ስልጠና ወስዳ በ1983 ወደ ሰራዊቱ በውትድርና ለማገልገል ተቀላቀለች፡፡ ሰራዊቱ ወዲያው ድል አድርጎ አዲስ አበባ ቢገባም  ከኦነግ ጋር ጦርነት ስለነበር በወቅቱ በርካታ ሴት ወታደር እና የጋንታ አመራር ሴቶች እንደነበሩ ታስታውሳለች፡፡

ባለታሪካችን ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ በውትድርና በቆየችበት መከላከያ ሰራዊት ከተራ ወታደርነት እስከ ቲም መሪነት፣ የጋንታ፣ ኀይል እና ሬጅመንት አመራር በመሆን ሠርታለች፡፡ ከዚህ ባለፈም በቢሮ (ስታፍ) ውስጥ እና በጦር ሰራዊት በምክትል አዣዥነት ደረጃ አገልግላለች፡፡

ረዳት ኮሚሽነሯ ቀላል የጦር ጉዳት ደርሶባት እንደነበር አስታውሳለች፡፡ በወቅቱም እሷ እና መሰሎቿ አቋርጠው የሄዱትን ትምህርት እንዲቀጥሉ በተለይ ሴቶች ጦላይ ውስጥ በልዩ ሁኔታ በተከፈተ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ተፈቀደላቸው፡፡ ረዳት ኮሚሽነሯም  እድሉን በመጠቀም ትምህርቷን ቀጠለች፡፡  12ኛ ክፍል ካጠናቀቀች በኋላ ወደ ሀገር መከላከያ እንድትመለስ ብትፈልግም የደረሰባት የጦር ጉዳት አስቸጋሪ ስለነበር አልቻለችም፡፡ በወቅቱም ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባ ነጥብ ከመጣላት ትምህርቷን  ለመቀጠል ወሰነች፡፡ ይህ ሀሳቧም ባለመሳካቱ  ወደ ፓሊስ ሰራዊት ገባች፡፡

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በተለያዩ የሥራ መደቦች የሰው ኀይል እንደሚፈልግ ያወጣውን ማስታወቂያ ተከትሎ በመመዝገብ ለምደባ እጣ ሲወጣ ረዳት ኮሚሽነር መሰረት ደቡብ ጎንደር ደረሳት፡፡ በዚሁ ዞን እያገለገለች እያለች ደግሞ  ባሕር ዳር ዩንቨርሲቲ ባወጣው የትምህርት እድል  ተወዳድራ በማለፍ  የሕግ ትምህርት  መማር ጀመረች፡፡

ረዳት ኮሚሽነር መሰረት ሥራዋን እየሠራች በተከታታይ  በክረምት ትምህርት መርሀ ግብር   ተምራ ለመመረቅ መብቃቷን ተናግራለች፡፡  በወቅቱም ረዳት ኮሚሽነሯ  በመከላከያ  ብዙ ውጣ ውረድ በማሳለፏ ካላት ልምድ አንጻር  የወንጀል መከላከከል የሥራ መደብ  ክፍት በመሆኑ እንድትመደብ ጠየቀች፡፡

እርሷ እንደምትለው በወቅቱ በዚያ የሥራ መደብ ሴቶችን መመደብ አይታሰብም ነበር፤ ምክንያቱ ደግሞ  ብዙ ውጣ ውረድ አለው ተብሎ ስለሚታሰብ ነው፡፡  “ብዙ ሴቶች ተመድበውበት በማያውቁት ቦታ ነው ሠርቼ ማሳየት ያለብኝ!” በሚል አቋሟ በመፅናት የወንጀል መከላከል ኃላፊ በመሆን በላይ ጋይንት ወረዳ ተመደበች፡፡ ከእሷ በፊት በመደቡ  ላይ የሠራች አንዲት ሴት ነበረች፤ ባለታሪካችን ከሷ ቀጥሎ በክልሉ ወንጀል መከላከል ኃላፊ በመሆን ተመድባ መሥራት ችላለች፡፡

ሥራው ውጣ ውረድ የሚበዛው፣ ለሊት እና ቀን እረፍት የሌለው የስርቆት፣ የግድያ ወንጀል…. ፈፃሚዎች ጋር ክትትል እና በቁጥጥር ስር ማዋልን እንደሚሻ ረዳት ኮሚሽነሯ ጠቁማለች፡፡ በአንድ  ወቅት በሥራ ያጋጠማትን  የማትረሳው ገጠመኝም አጫውታናለች፤  “አንዲት ተበዳይ ከቆቦ በጠና የታመሙ አባቷን ለማሳከም ወደ ባሕር ዳር በሌሊት ስትሄድ ጨጨሆ መድኃኒዓለም አካባቢ  ስትደርስ ሽፍቶች  አስቁመው ወርቋን እና  ብሯን ዘርፈዋታል፡፡ ከዚህ የከፋ ደግሞ አስገድደው ደፍረዋታል፡፡ ከደረሰባት ዝርፊያ በላይ የደረሰባት በደል ስለሚያሳዝን የዛኑ ቀን ከኅብረተሰቡ መረጃ ስናፈላልግ አንዱን ተጠርጣሪ ደረስንበት፡፡ ይዘን ስንጠይቀው  ሊያምን ስላልቻለ ቀጥታ ወደ ቤቱ በመሔድ እህቱን የሠጠሸን ወርቅ እና ገንዘብ አምጪ!? አልኳት፤ ‘ኸረ አልሠጠኝም’ ስትል ልጁ ‘ሰጥቻለሁ እያለ!‘  ስላት ‘እኔ አልነካም እያልሁት ከምድጃው ስር ነው  ቀብሮት የሄደው‘ በማለት  ንብረቱን ሰጠችን፡፡ ንብረቱን ስናገኝ እሱም ጠበቅ ተደርጎ ሲመረመር ግብረ አበሮቹ ያሉበትን ቦታ ጠቁሞ ያዝናቸው፡፡ በዛው ቀን  መሳሪያ ተሰርቆ ደርሰን፤ ያንንም በዛው ቀን ያስመለስሁበትን አጋጣሚ አልረሳውም” በማለት ሴትነቷ ለሥራዋ የበለጠ ጥንካሬን እንደሰጣት ታስታውሳለች፡፡

“በምርመራ ዘርፍ ሴቶች የሰዎችን ፊት በትክክል የማንበብ ችሎታ አላቸው” የምትለው ረዳት ኮማንደር መሰረት የእርሷ ተሞክሮ ለዚህ ማረጋገጫ እንደሆነ ታምናለች፡፡ ረዳት ኮሚሽነሯ   በዛው የታች ጋይንት ወረዳ በከልሉም የመጀመሪያዋ ፓሊስ አዛዥ በመሆን ሥትሠራ ቆይታ በ2006 ዓ.ም ወደ ባሕር ዳር ከተማ የትራፊክ ፓሊስ አዛዥ ሆና ተመደበች፡፡

በወቅቱም በከተማዋ ስድሥት ጣቢያ እና አንድ መምሪያ ሲኖር ሁለቱን ጣቢያዎች ብቻ ወንዶች ሲመሩት ሌሎች የጣቢያ ኃላፊዎቹ ሴቶች እንደነበሩ ታስታውሳለች፡፡ ሴቶች በሥራ ትጉ ነበሩ፡፡ በተለይም በወቅቱ ሥርዓት አልባ የነበረውን  የባጃጅ አገልግሎት ለማስተካከል ጥናት ተደረገ፡፡ በወቅቱ የነበረው  አንድ ማኅበር ብቻ ስለነበር   የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መሥራት ተጀመረ፡፡ የባጃጅ አገልግሎቱን  ለማስተካከል ከፍተኛ ጥረት በመደረጉ እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ ኅብረተሰቡ ያለቅሬታ መስተናገድ ችሎ እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ ለዚህም  ሴቶች በአመራርነት ሲመጡ ተደራራቢውን ጥቃት ለመከላከል የሚኖራቸው አስተዋፅኦም ከፍተኛ እንደሆነ ታምናለች፡፡

ላለፉት 33 ዓመታት ሕግን በማስከበር በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ያገለገለችው ረዳት ኮሚሽነር መሰረት፤ ከሥራዋ እና ቤተሰቧን ከመምራት ጎንለጎን  በማኔጅመንት የትምህርት ዘርፍም  ዲግሪዋን ይዛለች፡፡  “ብዙ ጊዜ የማደግ እና   የመለወጥ ፍላጎቴ ማኅበራዊ ሕይወቴን  ደካማ አድርጎታል” የምትለው ባለታሪካችን ለሥራዋ ስኬታማነት   ከትግሉ ወቅት  ጀምሮ አብሯት ዛሬ ድረስ የዘለቀው እና አብሯት  ያደገው ባለቤቷ ጥሩ አጋሯ እንደሆነ ገልፃለች፡፡ ሴቶች በምንም ሥራ ውስጥ ቢሆን ዙሪያቸውን መመልከት፣ ከዕድሜም አንፃር፣ ከጊዜም አኳያ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸው አስገንዝባለች፡፡

“ጦርነት የሚያስከትለው የንብረት ጥፋት ብቻ አይደለም፡፡ ክቡሩን የሰው ልጆች ሕይወት የሚነጥቅ ነገር ነው፤ እኔ በዘመኔ ሁሉ ስወለድ ጀምሮ አብዛኛው ጊዜ ጦርነት ነው፤ አሁን ያለንበት ጦርነት ደግሞ እናቶች ልጆቻቸውን እያጡ ነው፣ ልጆች ትምህርት አቋርጠው በየቦታው ነው ያሉት፤ ሴቶች ከወንዶች በበለጠ እጥፍ ድርብርብ የሆነ ጉዳት ላይ ናቸው፤ እና በተለየ ልብ ሊባሉ ይገባል” በማለት አስገንዝበዋል፡፡

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የሚያዝያ 13 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here