ከማን ምን ይጠበቃል?

0
18

ለሁሉም ሴክተር ብቁ የሆነ፣ ሚዛናዊ ዕይታ ያለው፣ በምክንያት የሚያምን፣ ውጤታማ እና ተወዳዳሪ የሰው ኀይል በማፍራት ሕዝብ የሚፈልገውን አገልግሎት ለመስጠት ውጤታማ የትምህርት ሥራ ማከነወን እንደሚገባ ይታመናል፡፡ ይህንንም ዕውን ለማድረግ ሁሉም ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሕጻናትን ወደ ትምህርት ቤት መላክ፣ የፈጠራ አቅማቸውን ሊያሳድግ የሚችል ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት መስጠት፣ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሳደግ፣ ብቁነታቸውን በየጊዜው ማረጋገጥ እና የትምህርት ሥራው እንዳይስተጓጎል በትኩረት መሥራትም ይጠበቃል፡፡ ይሁን እንጂ የትምህርት ዘርፉ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሚያጋጥሙ ችግሮች በተደጋጋሚ እየተፈተነ መጥቷል፡፡

በምክትል ርእሰ መስተዳደር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) የ2018 ዓ.ም የተማሪ ምዝገባን መሠረት አድረገው መግለጫ በሰጡበት ወቅት ትምህርት ላይ የገጠመው ችግር መሠረቱን የሚያደርገው ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ በወቅቱ የጸደቀው ሥርዓተ ትምህርት በአብዛኛው በማስታወስ፣ አንብቦ በመፈተን እና ክፍል በማስቆጠር ላይ ያተኩረ በመሆኑ ልጆች አካባቢያቸውን እንዲያውቁ፣ በዙሪያቸው ያለውን ሐብት ወደ ውጤት የሚቀይሩ እና በተግባር የሚገለጥ የሕይወት ዘመን ትምህርት እንዲያገኙ የተቃኘ እንዳልነበረ አስታውሰዋል፡፡ ይህም ለሰላም ግንባታ እና ለልማት ሥራዎች እንቅፋት ሆኖ መስተዋሉን ሲያስታውሱ፤ አሁናዊ ግጭቱም ከዚህ የመነጨ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) የአማራ ክልል ወደ ትጥቅ ግጭት ከገባበት ጊዜ ጀምሮ የትምህርት ሥራው በእጅጉ መፈተኑን ቁጥራዊ አኃዞችን እያነሱ አስረድተዋል፡፡ በ2016 ዓ.ም ብቻ ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ተማሪዎች የትምህርት ቤት ደጃፍን አልረገጡም፡፡ ይህም በዓመቱ መዝግቦ ለማስተማር ከታቀደው ስድስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ተማሪዎች ውስጥ እንደሆነ ኃላፊዋ ጠቅሰዋል፡፡

በ2017 የትምህርት ዘመንም የትምህርት እንቅስቃሴው ላይ የደረሰው ችግር ተባብሶ መክረሙን ኃላፊዋ ገልጸዋል፡፡ በዓመቱ ሰባት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ለማምጣት ታሳቢ ተደርጎ ሲሠራ ቢቆይም አራት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ተማሪዎች የትምህርት ቤት ደጃፍን ሳይረግጡ መክረማቸውን አስታውቀዋል፡፡ ተመዝግበው የዓመቱን ትምህርት ማጠናቀቅ የቻሉት ከሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን እንደማይበልጡም ይታወሳል፡፡ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ቢመዘገቡም በጸጥታ ችግር ምክንያት ትምህርታቸውን አቋርጠው ስለመክረማቸው ኃላፊዋ አስታውቀዋል፡፡ ሁለት ዓመታትን የተሻገረው ግጭት በአጠቃላይ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ከትምህርት አርቋል፡፡

የትምህርት ሥራ በደቂቃ የተከፋፈለ ነው ያሉት ኃላፊዋ፣ ወራት እና ዓመታት በባከኑ ቁጥር ክልሉ በትምህርት ከሚፈለገው በላይ ወደ ኋላ እንዲቀር የሚያደርግ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በ2017 ዓ.ም ብቻ ከትምህርት ገበታ የራቁ ተማሪዎች ቁጥር ከአፍሪካ የ15 ሀገራትን፣ ከኢትዮጵያም የአምስት ክልሎችን የሕዝብ ቁጥር የሚበልጥ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በትምህርት ሥራው ላይ የደረሰው ችግር የሚያደርሰው ተጽእኖ በክልሉ ብቻ የሚወሰን እንዳልሆነ ዶ/ር ሙሉነሽ ጠቁመዋል፡፡ ሀገራችን፣ አህጉራችን እና ዓለማችን የሚፈልጉትን ወሳኝ እና ችግር ፈቺ ምሁር የሚያሳጣ እንደሚሆን እምነታቸው ነው፡፡

ችግሩ ዕውቀት እና የእያንዳንዱን ተሰጥኦ በማባከን እንደ ሕዝብ ለሚነሳው የመልማት አቅም እና ፍላጎት የራሱን አሉታዊ አሻራ እንደሚያሳርፍም ተናግረዋል፡፡ ችግሩ የትውልድ ቅብብሎሽን የሚያቋርጥ፣ የክልሉን የመልማት አቅም የሚያጓትት፣ የአገልግሎት አሰጣጡን ከመዘመን ወደ ኋላ የሚያስቀር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የክልሉ ሕዝብ ከማንኛውም ተሳትፎ እንዲነጠል የሚያደርግ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡

የ2018 የትምህርት ዘመን ክልሉን በብዙ ነገሮች ወደ ኋላ ከሚጎትት ችግር የሚያወጣ እንዲሆን መተባበር እንደሚገባም ዶ/ር ሙሉነሽ ገልጸዋል፡፡ የአዲሱ ዓመት የትምህርት ሥራ እስካሁን ከትምህርት ውጪ ሆኖ የቆየውን የተማሪ ቁጥር በሚቀንስ አግባብ የሚከናወን መሆኑም ተጠቁሟል፡፡ ችግር ላይ ያለውን የትውልድ ቅብብሎሽ በሚያስቀጥል አግባብ በትኩረት ይሠራል ብለዋል፡፡

በትምህርት ዘመኑ የባከነውን የትምህርት ዓመት የሚያካክስ እንዲሁም  ባለፉት ዓመታት ከትምህርት ውጭ ሆነው የቆዩ ተማሪዎች መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራውን በአግባቡ ካስኬዱ ተማሪዎች እኩል እንዲሄዱ የሚዲያርግ የተፋጠነ የትምህርት ሥርዓት መዘርጋቱንም ጠቁመዋል፡፡ ይህም ወላጆች እና ተማሪዎች ተስፋን ሰንቀው የትምህርት ሥራው አጋዥ እንዲሆኑ የሚያበረታታ ነው ብለዋል፡፡ መምህራን ወደ ሙያቸው ተመልሰው ውጤታማ የመማር ማስተማር ሥራን እንዲወጡ የሚያግዝ የሙያ ስልጠና እና የስነ ልቦና ድጋፍ እየተሰጠ ነው ብለዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት አንደኛ ክፍል የሚተካው እና 12ኛ ክፍል ላይ መልቀቅ የነበረበት ተማሪ ባለመልቀቁ ከፍተኛ ክምችት መኖሩን አስታውቀዋል፡፡ በአጠቃላይ የዚህ ዓመት የተማሪ ምዝገባ የሦስት ዓመቱን ታሳቢ አድርጎ ይከናወናል ብለዋል፡፡ በመሆኑም ሁሉም እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሕጻናትን አስሶ ወደ ትምህርት ገበታ ማምጣት ከሁሉም እንደሚጠበቅ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በትምህርት ዘመኑ ሰባት ሚሊዮን 445 ሺህ 545 ተማሪዎችን ለመመዝገብ ዕቅድ ስለመያዙ ቢሮ ኃላፊዋ አስታውቀዋል፡፡ ዕቅዱ በእያንዳንዱ የትምህርት ቤት ቁጥር ተከፋፍሎ እስከ ታች ወርዷል፡፡

ዕቅዱን ለማሳካት፣ የትውልድ ቅብብሎሹን ለማስቀጠል፣ እንደ ክልል የሚጠበቀውን ተወዳዳሪ የተማረ የሰው ኅይል ለማፍራት፤ የክልሉ ሕዝብ ለትምህርት ያለውን ዋጋ ለመመለስ በርብርብ መሥራት እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡

 

ወላጆች ልክ እንደ ተማሪዎች ሁሉ ባለፉት ሁለት ዓመታት እንደ ክልል ባጋጠመው የሰላም መደፍረስ በሥነ ልቦና ተጎጂ ሆነው አልፈዋል ያሉት ኃላፊዋ፤ ነገር ግን በትምህርት ዘመኑ ለመመዝገብ የታቀደውን የተማሪ ቁጥር ለማሳካት የወላጆች ሚና ከፍተኛ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ “ወላጆች ‘ባለፉት ሁለት ዓመታት የባከኑ የትምህርት ጊዜያት የሚካካሱበት ጊዜ አሁን ነው‘ ብለው ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት መላክ ይኖርባቸዋል” ብለዋል፡፡ ወላጆች ያልተፈጠረን ችግር ይፈጠራል ከሚል ስጋት ወጥተው በብሩህ ተስፋ ልጆቻቸውን ቀድመው ከማስመዝገብ ጀምሮ አስፈላጊ የትምህርት ቁሳቁሶችን በማሟላት ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ ጠይቀዋል፡፡

አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች ቢሮው ከተለያዩ አካላት ያሰባሰበውን የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያበረክትም አረጋግጠዋል፡፡ የሚባክን የትምህርት ጊዜ እንዳይኖር ልጆቻቸውን መከታተል፣ የትምህርት ማኅበረሰቡን ማቅረብ እና ከለላ ማድረግ ከወላጆች እንደሚጠበቅ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

“ትምህርት ቤቶች የልጆቼ ነገ መዳረሻ ናቸው” በሚል መንፈስ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በየጊዜው መቃኘት እና አስፈላጊው መሠረተ ልማት እንዲሟላ ማድረግ ላይ ሊሠሩ እንደሚገባም  ተጠቁሟል፡፡ የትምህርት ቤቶችን ግቢ ሳቢ እና ማራኪ ማድረግ፣ መጠገን፣ ማጽዳት… ለትምህርት ሥራው ውጤታማነት በትጋት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ መምህራንን ጨምሮ የትምህርት ማኅበረሰቡን (መርሱ) እንደ ልጆቹ ተንከባካቢ ቆጥሮ አስፈላጊውን ጥበቃ እና ከለላ በመስጠት እንደሚኖርበት  ዳግም የማይቋረጥ ትምህርት እንዲኖር አስተዋጽኦው ከፍተኛ መሆኑን በመተማመን ነው፡፡

 

የሰላም መደፍረሱ በትውልድ ቅብብሎሽ ላይ እያደረሰ ካለው ችግር ለመውጣት የመምህራን እና የትምህርት አመራሩ ሚና ሊጠናከር እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ ልጆች ትምህርት እንዳይማሩ የተዛነፈ አስተሳሰብ ያለው አካል ሁሉ የትምህርትን ፋይዳ እንዲረዳ በማድረግ ረገድ የበኩላቸውን ሚና የመወጣት አደራ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

የትምህርት ተቋም ዋነኛ ሥራ ትውልድ ቀረጻ እና ግንባታ ላይ በመሆኑ መምህራን፣ ርእሳነ መምህራን እና ሱፐርቫይዘሮች ነገ የተሻለ እና ያማረ እንዲሆን በትጋት የመሥራት አደራን ሰጥተዋል፡፡

 

ዶ/ር ሙሉነሽ አጋር ድርጅቶች (አካላት) እስካሁን በችግር ውስጥ ያለፈው የትምህርት ሥራ ሳይስተጓጎል እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በእስካሁን ሂደት የነበራቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደነበር ያነሱት ኃላፊዋ፤ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሳደግ፣ ተማሪዎች እና መምህራን ከድባቴ ወጥተው የተሳካ የትምህርት ሥራን ለማከናወን የሥነ ልቦና ድጋፍ በመሥጠት እና ክልሉ ያለበትን ሁኔታ ለሌሎች በማሳወቅ የተለመደ ድጋፋቸውን እንዲያበረክቱም ጠይቀዋል፡፡

ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ ልዩ ልዩ የማኅበረሰብ አደረጃጀቶች እና ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል የክልሉ የትምህርት ሥራ ቀድሞ ይታወቅበት ወደነበረው ከፍታ እንዲመለስ በርብርብ መሥራት እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡

የአማራ ክልል ያለፉትን ሁለት ዓመታት በፈተና ውስጥ ቢያልፍም ካለፈው ይልቅ የመጪው ጊዜ ተስፋ ትልቅ በመሆኑ ሁሉም በደረሰው ችግር ከመቆዘም ወጥቶ ዕድሜው ለትምህርት የደረሰ ሁሉ ወደ ትምህርት እንዲመለስ ግፊት መድረግ እንዳለበት ኃላፊዋ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የነሐሴ 26 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here