ከምቾት ፈቀቅ…

0
120

ሁለት ተመሳሳይ ግልገል የንስር ወፎችን የተመለከተ አንድ ንጉሥ አብዝቶ ወደዳቸው። ወፎቹን አምጡልኝ ብሎ እያበላ እያጠጣም አሳደጋቸው። ንስሮቹ መብረር የሚችሉበት ዕድሜ መጣ። አንደኛው ወፍ ሲበር ሌላኛው  ብርር ብሎ ዛፍ ላይ ወጥቶ ይውላል። አንደኛው ከተማውን ሲያካልል ውሎ የሚበላም የሚጠጣም ጠግቦ ይመጣል። መብረር ያልቻለው ግን አንዲት ዛፍ ላይ ቁጭ ብሎ ይውላል። በራሱ ምግብ ፈልጎ አይበላም። ከቤቱ ዙሪያ ካለች ዛፍ አይወርድም።

ይህንን ያየው ንጉሡ በሁለቱ ወፎች ልዩነት አብዝቶ ይጨነቃል። በዙሪያው ያሉ ሰዎችን አማከረ፤ ጠየቀ። አንደኛው ወፍ መብረር የማይችልበትን ምክንያት ለማወቅ አልቻለም። ንጉሡ በከተማው “ይህ ወፍ እንዲበርር ለሚያደርግልኝ ሰው ሽልማት እሰጣለሁ!” ብሎ አዋጅ ያስነግራል። ይህንን የሰማ አንድ ምስኪን ደሀ ሰው ወደ ንጉሡ መጣ። ንጉሡ “ይህን ወፍ እንዲበር ለማድረግ አልቻልንም፤ አንተ ምን የምታውቀው ነገር አለህ?” ብሎ ጠየቀው። ያ ምስኪን ሰውም ማድረግ የሚችለውን ነገር አደረገ።

አንድ ቀን ወፉ ዛፉ ላይ እንዳለ  የሚያርፍባትን ዛፍ ያ ምስኪን ሰው ቆረጠበት። በድንጋጤ ወፉ መብረር ጀመረ። ከተማውንም ሲዞር እና ሲያካልል ውሎ መጣ። ከወንድሙ ጋርም እኩል መብረር እንደሚችል በማየቱ ንጉሡ በጣም ተደሰተ።

ይህ ግልገል ንስር ከሌላኛው ወንድሙ የተለየ ተፈጥሮ አልነበረውም። ነገር ግን ያችን የደጁን ዛፍ የሙጥኝ ብሎ በመያዙ ሌላ ሕይወት ያለ አልመሰለውም። ከዚያች ዛፍ ተነስቶ ቢበር ሕልውናው የሚናጋ፣ የሚሰበር፣ የሚሞት መስሎት ነበር። ያች የለመዳት ዛፍ ምቹ ናት። ምቹነቷ ግን በጊዜያዊነት ለመቆየት እንጅ ለማደግ እና የተሻለ ምግብ ለማግኘት አልነበረም።

የንጉሡን ትዕዛዝ ተቀብሎ የምቾቱን ዛፍ የቆረጠለት ሰው በሕይወቱ ውስጥ  መልካም አጋጣሚን የፈጠረለት ነው። የተሻለ ዓለም እንዳለ እንዲያውቅ፣ የንስሩ አቅም ዓለምን በአክናፉ ማካለል መሆኑን እንዲያውቅ አድርጎታል።

“ተዋጊ በሬ ከሳር ይጥላል” እንደሚሉት አበው በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ አንዳንድ ሰዎች ጠላት ቢመስሉንም እድል ሆነው ይመጣሉ። ጣላቶቻችን የምር ጠላቶች አይደሉም፤ የሚደርስብንን ጥቃት የምንተረጉምበት አረዳድ ነው ልዩነቱ። ከሞቀ አልጋው፣ ከተመቻቸበት ኑሮው፣ ከሚስማማው አየር፣ ከለመደው ስራ ሲገፉት ወይም ሲለውጡት ማንም ደስ አይለውም። “እልፍ ቢሉ እልፍ” ነውና ሰዎች የነበሩበትን ምቾት ከለቀቁት በኋላ እጅግ የተሻለ ነገር ሲገጥማቸው “ምን ሆኜ ነው ያን ይህል ዘመን እዚያ የቆየሁት?” ይላሉ።

ጠንካራ ሰዎች  ጠላቶቻቸው ለመበደል ወይም እነሱ ለመጠቀም ሲሉ የሚያደርሱባቸውን መገፋት ለለውጥ መልካም እድል አድርገው ይወስዱታል። ንስሩ ያንን ዛፍ የቆረጠለትን ሰው ሲያመሰግን ይኖራል- የሚፈራውን፣ የማይደፍረውን ዓለም አሳይቶታልና።

የምቾት ዞን ወይም ቀጣና ሰዎች ለረጂም ጊዜ የቆዩበትን፣ የለመዱትን፣ የኖሩበትን፣ በደንብ የሚያውቁትን ሁኔታ ይወክላል። በዚህ የምቾት ቦታ ውስጥ ማደግ የለም። በዚህ ውድድር በበዛበት ዓለም ሰዎች በምቾት ውስጥ ከቆዩ ይሸነፋሉ፤ ከኋላ ተገፍተው ይቀራሉ፤ መኖራቸው ይቀራል።

ፖዘቲቭ ሳይኮሎጂ  ድረ ገጽ “አደጋዎች የሌሉበት፣ ከጭንቀት ነጻ፣ ማደግ እና መለወጥ የሚቀነጭርበት ስፍራ የምቾት ቀጣና ወይም ክልል ይባላል” በማለት አስቀምጦታል። ከዚህ ስፍራ መውጣት ራስን ለመረዳት፣ ውጤታማ ለመሆን እና አዳጊ የእዕምሮ ስሪት ለመያዝ እጅግ ጠቃሚ መሆኑንም ገጹ አስቀምጧል።

የምቾትን ገዳይነት ብዙ የሰብዕና ግንባታ እና አመለካከት ለውጥ አሰልጣኝ መምህራን እና ምሁራን ጽፈውበታል። እድገት እና ለውጥ ሁልጊዜ የምቾት ክልልን እንደወጣን ይጀምራል በሚለው ይስማማሉ።

አንድ ሰው በማያድግ እና ወደ ኋላ በሚጎትት የምቾት ክልል ውስጥ ነው ሲባል ማሳያዎች አሉት። “ጌትስ ቤተር ናው” ድረ ገጽ በምሳሌነት ጠቅሷቸዋል። አልተዘጋጀሁም፤ ለዚህ ጉዳይ ገና ነኝ የሚል እሳቤ ሰዎች ከምችት አጥራቸው ወጥተው ዓለምን በአዲስ እሳቤ እና ተግባር እንዳይመለከቱ የሚያደርጋቸው ነው።

ትላልቅ ግቦችን ማስቀመጥም እንዲሁ በምቾት ቀጣና ውስጥ ለመቆየት አዕምሮ የሚፈጥረው አጥር ነው። ብዙ ሰዎች ንግድ መጀመር ይፈልጋሉ። “አሁን ንግድ አልጀምርም። የዛሬ አምስት ዓመት ነው በሚሊዮን ብር ካፒታል አጠራቅሜ የምጀምር” ይላሉ። ግን አምስቱ ዓመት ያለምንም ዝግጅት እና ተግባር በከንቱ ያልፋል። ከአምስት ዓመት በኋላ ላስቀመጡት ትልቅ ግብ ዛሬ ትናንሽ ተግባራትን አይከውኑም።

ስለማናውቀው ነገር መፍራትም በምቾት ክልል ውስጥ እንድንቆይ የሚያደርገን ሌላው ምክንያት ነው። የሆነ ክፉ፣ መጥፎ፣ አስቸጋሪ ጊዜ እና ክስተት ይገጥመናል በሚል አዕምሯችን ይፈራል። ስለዚህም አዲስ ነገር ከመጀመር ይልቅ በለመደው  ስፍራ መቀመጥን ይመርጣል።

የሰው ልጆች ተፈጥሮ ምቾትን የሚፈልግ፣ ከአደጋ የሚጠበቅ ነው። ችግሮች ፈተናዎች፣ አደጋዎች መቼ እንደሚገጥሙት አያውቅም። ለዚህም ሁልጊዜ ራሱን ለመጠበቅ ሲል አዕምሮ የምቾት ክልል ውስጥ መቆየትን ይመርጣል። በቅጽበት ሕይወትን የሚነጥቅ አደጋ ሊያጋጥመን ይችላል። ከዚህ የተነሳ መኖርን ስለሚሻ የምቾት ስፍራ ሙጥኝ ማለትን ይመርጣል።

መውድቅን መፍራትም ሌላው ምልክት ነው። በምቾት ክልላችን መቆየት የመውደቅ አደጋን ይቀንሳል። ወደቅሁ በሚል ለራሳችን የምንሰጠውን ዋጋ እንዳይቀንስ ያደርገናል። አንዳንድ ሰዎች አዳዲስ ነገሮችን ሲሞክሩ ይደነቃቀፋሉ። ተመልካች የሆነ ሰው “አይ እንዲያው ከዚህ ሁሉ ስቃይ አርፎ ቢቀምጥ” ብሎ ራሱን ጠንቃቃ እና ጎበዝ አድርጎ ይስላል። የሞከረውን ሰው ደግሞ ተሸናፊ እና ደካማ ያደርገዋል። በፍርሀት መቆም ለዚህ መሰረት አልባ ጉራ ያበቃን ይሆናል። እውነታው ግን ከማይሞክሩ ሰዎች ሞክረው የሚወድቁት ይሻላሉ- የመነሳት ልምድ አላቸውና።

የቀድሞ አሉታዊ ልምዶች ሰዎችን በምቾት ምሽጋቸው ውስጥ እንዲቆዩ ሊያደርጓቸው ይችላሉ። ከዚህ በፊት የከሰረ ነጋዴ፣ በልጅነቱ መጥፎ ጠባሳ ያለበት ሰው፣ ተቀባይነት ያጣ ሰው ከለመደው የምቾት ቦታ ወጥቶ አዲስ ሕይወት ለመጀመር ይቸገራል። “ያያዝኋትን ይጠብቅልኝ!”፣ “ያለችኝን ይባርክልኝ!”፣  “አተርፍ ባይ አጉዳይ” የሚሉ ተረቶችን ለራሳችን በመንገር በያዝነው ስፍራ ለመቆየት ልንገደድ እንችላለን።

ደካማ በራስ መተማመን ሲኖር ሰዎች የራሳቸውን አቅም ዝቅ አድርገው ይሰፍሩታል። ሙሉ ቢሆን እንኳን ራሳቸውን ከስፍር አጉድለው ለመራመድ አቅም አልባዎች ይሆናሉ፤ በለመዱት እና በሚቆጣጠሩት አካባቢ  ብቻ ተወስነው ይቀራሉ።

የምቾት ስፍራ እንደ ማምለጫ ሆኖም ያገለግላል። የሰው ልጆች ከሚያውቁት እና ከለመዱት ርቀው በተጓዙ መጠን ለውጥ አይቀሬ ነው። ያ ለውጥ ግን በቀላሉ አይመጣም፤ ጭንቀት እና ውጥረት አለበት። አዕምሮ ያንን ጭንቀት እና ውጥረት ስለሚጠላው በምቾት ክልል ውስጥ ይቆያል።

ከምቾት ክልል መውጣት በራስ መተማመንን ያሳድጋል። ግቦችን ለማሳካት ይቻላል። ስለ ዓለም በጠባቡ የተሸነቆረ ዕይታችንን ያሰፋዋል። ከምቾት ክልል መውጣት ምርታማነትን ይጨምራል። አዳዲስ ነገሮች ጋር እንድንተዋወቅ ያግዛል። ዕይታችንን ወደ እድገት መስመር ያዞረዋል።

እውቁ የመሪነት መጽሐፍት ደራሲ ጆን ማክስዌል  እንደሚለው ተመሳሳይ ነገር  በተመሳሳይ መንገድ መስራት፤ ተመሳሳይ ሰዎች ተመሳሳይ ውጤት በማግኘት የሚኖሩበት፣ እንደገናም ለምን ብለው የሚጠይቁበት ስፍራ የምቾት ክልል ይባላል።

ማክስዌል ከዚህ አደገኛ ስፍራ ለመውጣት ውጥረቱን አታቁም ይላል። ውጥረት በሌለበት ስፍራ እድገት የለም። ፕላስቲኮች ጥቅም የሚሰጡት ሲወጠሩ፣ ሲዘረጉ ነው። ለዚህም ውጥረቱን አታቁም። ሁልጊዜ እንቅስቃሴ ውስጥ ሁን። ጎማ ከተነፈሰ አይጓዝም፣ አይሽከረከርም። የሰው ልጅ አዕምሮም ውጥረት ከሌለው መስራት፣ መንቀሳቀስ አይችልም ይላል። ውጥረት ሲኖር በትናንት እና በዛሬ መካከል ቦታ ይፈጠራል። ለነገ ደግሞ ከፍታ ላይ ለመውጣት መንጠራራት እና መሳብ አለ። ይህም ከምቾት ቅጥራችን በጥሰን እንድንራመድ ያግዘናል።

በምክንያት መስፋት ሌላው ማክስዌል የሚመክረው የመውጫ  ሐሳብ ነው። እድገት በምክንያት መስፋት እና መለጠጥን ይጠይቃል። ተገደን ከሆነ አቅጣጫ ልንስት እንችላለን። በፍላጎት ከሆነ መንገዳችን የተጠና ይሆናል። ብዙ ሰው ምቾት ከመውደዱ የተነሳ ድክመቱን ለማሻሻል ይሞክራል። ትንሽ ነገርን ማስፋት እና ፈተና መቀነስን ይመርጣል። ጠንካራ ነገራችንን መፈተን ይኖርብናል። የማይደፈረውን መንካት ይኖርብናል። ያን ጊዜ የበለጠ እንፈተናለን፤ እንነቃለን። ደግሞም እንጠነክራለን። የሚያድግ ነገራችንን ፈተና ውስጥ ማስገባት ወደ እድገት ይመራናል፤ ጥንካሬና ጉልበት ይፈጥርልናል።

ጠቃሚ ምርጫዎችን ማድረግ ሌላው ምክሩ ነው። ምርጫችን በቀጥታ ወደ ምንፈልገው ውጤት ይመራናል። ቀጣይነት ሲኖር መልካም ውጤት ይመጣል። የሚለውጡ እና የሚያሳድጉ ምርጫዎችን መወሰን ከምቾት ክልላችን ሰንኮፋችንን ነቅሎ የሚያወጣልን መንገድ ነው። በሕይወቴ የሚያስፈልገኝ ቅድሚያ የምሰጠው ጉዳይ ጊዜያዊ ምቾት ወይስ እድገት? ተገቢውን መምረጥ ከባርነት ያወጣል። ፍርሀት ሲመጣ  ይህን ጥያቄ በመመለስ ምርጫን ማስተካከል ተገቢ ነው።

ከትንሽ መጀመር አዋጪ ነው። ብዙ ሰው በትልቅ መጀመር ይፈልጋል። ግን ሳይጀምር ይቀራል። “ጠብታ ውኃ አለት ትሰብራለች” እንደሚባለው የዛሬ ሕይወታችን ትናንት በትንሹ ያለማቋረጥ ያደረግናቸው ጉዳዮች ድምር ውጤት ነው። ከምቾት ክልላችን ሊያወጣን የሚችል ትንሽ ተግባርን መከወን አለብን። የተጋነነ ነገር መሆን የለበትም። የሚያስፈራንን፣ የሚፈትነንን እናም ጥሩ ውጤት ሊያስገኝልን የሚችልን ጉዳይ መምረጥ አለብን።

በዓላማ መኖር ይኖርብናል። በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ የመታወስ እና ያለመታወስ ጉዳይ በዓላማ ከመኖር ጋር ይገናኛል። በምድራዊ ሕይወታቸው ዓላማ የነበራቸው ሰዎች ዛሬም ድረስ ስማቸው ጎልቶ ይነሳል። የንግግር፣ የኑሮ፣ የጥናት እና ምርምር መነሻዎች ናቸው። ያስቀመጡት አሻራ ለትውልድ ተላልፎ እያገለገለ ነው።

በሕይወት ውስጥ ዓላማ ሲኖር  ለመኖር፣ ለማደግ እና ለመለወጥ እንደ ነዳጅ ያገለግላል። የሰው ልጆች የሚኖሩለት ምክንያት ሲኖራቸው ሕይወት ጣፋጭ ነው። የምትኖርለት ዓላማ ሲኖርም ከሞቀ አልጋህ ላይ አትውልም፤ በጠዋት ተነስተህ ብርድ እና ዝናብን ትጋፈጠዋለህ እንጂ። ዓላማ ይኑርህ፤ አሳካዋለሁ፤ አደርገዋለሁ የምትለው ዓላማ ያስፈልግሃል።

በመጨረሻም ከስኬት በላይ ለአስፈላጊነት መኖርን ማክስዌል ይመክራል። የአንተ አስፈላጊነት ሲገባህ ስኬት ማለት ምንም እንዳልሆነ ትረዳለህ። ስኬትህ ለሰዎች መኖርን፣ የአንተን አስፈላጊነት ይዞብህ ይመጣል። ለራስህ ከአንድ እንጀራ በላይ አትበላም። በመብላት አትደሰትም። ለሌሎች ሰዎች በመስጠት እና በማድረግ የምትደሰትበት ጊዜ ይመጣል። ሌሎች ሰዎች ሕልማቸውን እንዲያሳኩ ምክንያት ትሆናለህ። ሌሎችን መርዳት ስትፈልግ ምቾት ውስጥ መቀመጥን አትመርጥም። ለዚህ ነው ከራስህ ባሻገር ለሌሎች ሰዎች ስትል መኖር ያለብህ። ሌሎችን ሰዎች በአንተ የስኬት ጉዞ ውስጥ ማካተትህ ከስንፍና የምቾት ክልል ያወጣሃል።

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የሚያዝያ 6 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here