ከሦስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን በላይ ሕጻናት ይከተባሉ

0
55

የኩፍኝ በሽታ ክትባት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከግንቦት 06 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ እየተሰጠ ይገኛል። ዕድሜአቸው ከዘጠኝ ወር እስከ አምስት ዓመት የሚሆኑ ሕጻናት ክትባቱን እንደሚከተቡ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አበበ ተምትሜ ተናግረዋል። የበሽታው ምልክቶች በአማራ ክልል አንድ አንድ ቦታዎች መታየታቸውን የገለጹት ምክትል ኃላፊው በዚህ ዘመቻ በክልሉ ከሦስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን በላይ ሕጻናት ክትባቱን ለመስጠት ወደ ሥራ ተገብቷል።

ክትባቱ በሁሉም የአማራ ክልል ቦታዎች በሚገኙ የጤና ተቋማት እና በተንቀሳቃሽ የክትባት ጣቢያዎች እየተሰጠ ይገኛል። ታዲያ እናቶች በክትባት መከላከል የሚችሉትን እንደ ኩፍኝ መሰል በሽታዎች ለመከላከል ልጆቻቸውን ማስከተብ እንዳለባቸው የቢሮው ምክትል ኃላፊ አሳስበዋል። ከዚህ ክትባት ጎን ለጎን የታመሙ ሕጻናት ሕክምና የሚያገኙበት እና የመለየት ሥራም ይሠራል ብለዋል – አቶ አበበ።

በክልሉ በተፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት አንድ ዓመት ሆኗቸው ክትባት ያላገኙ ወይም ክትባት ያቋረጡ ሕጻናት ሌሎችንም ክትባቶች እንዲያገኙ ተመቻችቷል። ይህ ሲሆን ደግሞ መደበኛው ክትባት አይቋረጥም ተብሏል። በተጨማሪም የአንጀት ጥገኛ ትላትል መድኃኒቶች፣ ቪታሚኖች ለሕጽናት ይሰጣሉ ነው የተባለው። በክልሉ በሚገኙ ሁሉም የጤና ተቋማት ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተደርጎ ክትባቱ መጀመሩን አቶ አበበ ተናግረዋል።

የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እና  ክትባቱን ለሚሰጡ ባለሙያዎች ስልጠና ተሰጥቶ ነው የኩፍኝ ክትባት ዘመቻው የተጀመረው። ለክትባቱ የሚያገለግሉ ግብአቶችም በተመሳሳይ በሁሉም ቦታዎች በበቂ መጠን ተደራሽ ሆነዋል ነው ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው።

በክትባት ዘመቻው የኩፍኝ በሽታን ቅድመ መከላከል ብቻ ሳይሆን ሌሎች ክትባቶችም እየተሰጡ ይገኛሉ። በሕጻናት ዕድገት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳርፉ አጣዳፊ የሥርዓተ ምግብ እጥረት ልየታ እና ሕክምና የሚያገኙበት መንገድ እየተሠራ ነው። በተፈጥሮ የላንቃ እና የከንፈር መሰንጠቅ ያለባቸው ሕጻናትንም በመለየት ሕክምና እየተሰጠ መሆኑ ተገልጿል። ከሕጻናት በተጨማሪ በእናቶች ጤና አገልግሎት ላይም እየተሠራ መሆኑን አቶ አበበ ተምትሜ አስታውቀዋል።

ለኩፍኝ በሽታ ክትባት ዘመቻ ሁሉም አካላት የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው ያሉት አቶ አበበ በተለይ አመራሩ እና ባለሙያው በቅንጅት መሥራት ይኖርበታል ብለዋል። ለማሕበረሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር እና ተደራሽ በማድረግ የሕጻናትን ህይወት መታደግ አለባቸው ነው ያሉት።

በማስጀመሪያው መርሀ ግብር ያገኘናት እናት ወ/ሮ አዲሴ ግርማው የኩፍኝ በሽታን ቀድሞ መከላከል እየተቻለ ብዙ ጉዳቶችን እያደረሰ ነው፤ ታዲያ እናቶች ከአጉል ልማድ ወጥተው ልጆቻቸውን እንዲያስከትቡ ስትል ትመክራለች።

የኩፍኝ ክትባት እንደ ሀገር 17 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሕጻናትን ለመክትብ ዕቅድ ተይዟል ያሉት ደግሞ የጤና ሚኒስቴር የክትባት ፕሮግራም አማካሪዋ ወይዘሮ ማስተዋል ቀረብህ ናቸው። የኩፍኝ በሽታ በመደበኛነት የሚሰጥ ሲሆን በየሁለት ዓመቱ ደግሞ በዘመቻ እየተሰጠ ይገኛል። “በክትባት መከላከል የምንችላቸውን በሽታዎች ቀድመን ልጆቻችንን በማስከተብ ከሞት፣ ከሕመም እና ከአካል ጉዳት መታደግ አለብን” ሲሉ ወይዘሮ ማስተዋል ለእናቶች ጥሪ አቅርበዋል።

ሕጽናት የኩፍኝ በሽታ ክትባትን እንዲያገኙ ወላጆች እና ባለሙያዎች  ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ መልዕክት አስተላልፏል።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የግንቦት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here