በኵር ጋዜጣ ታህሳስ ሰባት ቀን 1987 ዓ.ም የመጀመሪያዋን እትም እንደጀመረች ታሪክ ያስረዳል። ይህቺ ሳምንታዊ ጋዜጣ ቀዳሚ የክልል ጋዜጣ እንደሆነችም ይነገራል። በወቅቱ አራት ሺህ ቁጥር የጋዜጣ ህትመት እየታተመ በሁሉም የአማራ ክልል ቦታዎች ይሰራጭ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስነብባሉ።
ጋዜጣዋ ስትጀመር ስድስት አምዶች የነበራት ሲሆን ከእነዚህ መካከል በጋዜጣው የመጨረሻ ገጽ የሚገኘው የስፖርት አምድ ይገኝበታል። ስፖርት ጠንካራ ማህበረሰብ በመገንባት እና ሞራልን በማጎልበት ጤናማ ማህበረሰብን ለመፍጠር ያግዛል። የሀገር ኢኮኖሚ ለመገንባትም የማይናቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል።
ታዲያ ይህንን የተረዳችው በኵር ግዜጣ ባለፉት 30 ዓመታት የተለያዩ የስፖርት መረጃዎችን ወደ ማህበረሰቡ በማድረስ የስፖርት ዘርፉ እንዲያድግ እና ጤናማ ትውልድ እንዲፈጠር ዓይነተኛ ሚና ተጫውታለች፤ አሁንም እየተጫወተች ትገኛለች። በዘርፉ ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ነቅሶ በማውጣትም መፍትሔ እንዲሰጠው ሠርታለች፤ አሁንም እየሠራች ነው።
ባለፉት 30 ዓመታት በስፖርት አምዳችን ከባህላዊ እስከ ዘመናዊ ስፖርት ያልተዳሰሱ ርዕሰ ጉዳዮች የሉም። ለአማራ ክልል እና ለሀገራችን በስፖርቱ ዘርፍ አሻራቸውን ካስቀመጡ ከግለሰቦች እስከ ቡድኖች የዘገባ ሽፋን አግኝተዋል። ከአቶ ይድነቃቸው ተሰማ እስከ መንግስቱ ወርቁ፣ ከሻምበል አበበ ቢቂላ እስከ ታላላቅ የኢትዮጵያውያን አትሌቶች፣ ከስፖርት ጉዳት እስከ ስፖርት ህክምና፣ ከክለብ እስከ ብሄራዊ ቡድን፣ ከተጫዋች እስከ አሰልጣኝ፣ ከተመልካች እስከ ደጋፊ፣ ከክረምት ስልጠና እና ውድድር እስከ ታላላቅ ግዙፍ የሀገራችን ስፖርት ሁነቶች በአምዱ ተስተናግደዋል።
ከሰፈር የማዝወተሪያ ስፍራ እስከ ታላላቅ የሀገራችን ስቴዲየሞች የዜና ሽፋን ተሰጥቷቸዋል። ከአካባቢያዊ እስከ ሀገር አቀፋዊ ግዙፍ የስፖርት ሁነቶች ዘገባ ተሠርቷል። በኵር ጋዜጣ ታህሳስ ሰባት ቀን 1987 ዓ.ም በመጀመሪያ እትሟ ሁለት አጫጭር የሀገር ውስጥ የስፖርት ዘገባዎችን ከመጨረሻው ገጽ በማካተት ነበር ለንባብ የበቃችው።
በወቅቱም ይህንን ዘገባ ያዘጋጀው ጋዜጠኛ ስም ባይጠቀስም “የውኃ ላይ ኳስ ጨዋታ ተጀመረ” የሚል ርዕስ ነው የተሰጠው። ይህ ውድድር በጣና ሀይቅ ዳርቻ ላይ የተደረገ መሆኑን ከጽሁፉ አንብበን መረዳት ይቻላል። ስድስት ስድስት ተጫዋቾች በሁለት ቡድን ተከፍለው እየዋኙ በእጃቸው ግብ ለማስቆጠር የሚጫወቱ ጨዋታ መሆኑን ጽሁፉ ያትታል። ይህ ስፖርት አሁን ላይ ግን በሀገር አቀፍም ሆነ በሀገራችን ሕግ እና ደንብ ወጥቶለት እየተከናወነ አይደለም።
በስፖርት አምድ የተስተናገደው ሌላኛው ዜና ደግሞ “አዲስ ጋራዥ ስፖርት ክለብ- የመልካም ጅምር መሰረት” ይላል የተሰጠው ርዕስ። ከርዕሱ እንደምንረዳው አቶ ሀዲስ ገብረ ሚካኤል በተባሉ ግለሰብ የተቋቋመ የእግር ኳስ ቡድን እያሳየ ያለውን አስደናቂ ብቃት ያስነብባል። የበኵር የስፖርት አመድ በዚህ መንገድ የተገኘው ዜና እየተስተናገደ በአንድ ገጽ በዚህ መንገድ እስከ 1990ዎች መጀመሪያ ቀጥሏል። ጋዜጣዋ ከሀገር ውስጥ ዘገባ በተጨማሪ አልፎ አልፎ የውጪ ዘገባም እየተካተተባት መረጃዎችን ለአንባቢያን ታደርስ እንደነበር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ጋዜጣዋ መታተም ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ለጥቂት ሳምንታት የሀገር ውስጥ ዘገባ ብቻ ነበር ይስተናገድ የነበር።
ከ1987 እስከ 1990 ዓ.ም ባሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ አሁን ላይ በአሚኮ በኵር ዝግጅት ክፍል በከፍተኛ አዘጋጅነት እያገለገለ የሚገኝው ጌታቸው ፈንቴ እና የቀድሞው የአምዱ አዘጋጅ ዘውዱ ሞኝነቴ የስፖርት አምዱን በዋናነት በማዘጋጀት አገልግለዋል። እንዲሁም በአማራ ክልል የሚገኙ የበኵር ጋዜጣ አንባቢዎች የስፖርት ዘገባዎችን በማዘጋጀት ጭምር ይሳተፉ ነበር።
ባርክልኝ ከባሕር ዳር፣ አርዱልነጃ ከቻግኒ እና መስፍን አራጌ ከደሴ በስፖርት አምድ ዘገባዎችን በማዘጋጀት ጭምር ተሳትፈዋል። ለአብነት መስፍን አራጌ ከደሴ ይካቲት ዐስር ቀን 1987 ዓ.ም “ፔፕሲ ለምን ፈረሰ”? በሚል ርዕስ የሀገር ውስጥ ዘገባ አስነብቧል። በ1970ዎች ትልቅ ስም የነበረው የፔፕሲ እግር ኳስ ክለብ ለምን እንደፈረሰ በስፋት ጽሁፉ ያትታል። ሌላው የበኵር ጋዜጣ የስፖርት አምድ የአማራ ክልል የዜና ማዕከል የዜና ምንጩ ሲሆን የዜና ማዕከሉ ለስፖርት አምዱ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።
የስፖርት አምዱ በተለይ እስከ ኢትዮጵያ ሚሊኒየም ድረስ ወጥ የሆነ የዜና አጻጻፍ ስልት አልነበረውም። አንዳንድ ዘገባዎች ከስፖርት ዜናነት ይልቅ “ለሪፖርትነት ” የሚቀርቡ ይመስላል። ይካቲት ሦስት ቀን 1987 ዓ.ም በሀገር ውስጥ “የአሰልጣኙ ቆይታ በባሕር ዳር በሚል ርዕስ በወጣው ጽሁፍ ከአሰልጣኝ ወንድማገኝ ጋር የተደረገው ቃለ ምልልስ በእንግዳ አቀራረብ እንደወረደ ሰፍሯል። ሚያዚያ 13 ቀን 1987 ዓ.ም በወጣው እትም ደግሞ ከዜና ቅርጽነት የወጣ ጽሁፍ እናገኛለን። “በደብረ ማርቆስ ከተማ የስፖርት ውድድር ተጠናቀቀ” የሚል ርዕስ ባለው የጽሁፍ ሀተታ በዘጠኙም የስፖርት ዓይነቶች ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃን የያዙ ዞኖች እና ስፖርተኞች ስም ሰፍሮ እናገኛለን።
ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ በተሻገረው የጋዜጣዋ ታሪክ በስፖርት አምዷ ረዥም እና ዘና የሚያደርጉ የዘገባዎችን ርዕስም እናገኛለን። ለአብነት መስከረም ሁለት ቀን 1990 ዓ.ም በሀገር ውስጥ በተዘጋጀው ዘገባ “ወሲብ እና ስፖርት” የሚል ርዕስ እናገኛለን። ዘገባው ስፖርት እና ወሲብ ስላላቸው ዝምድና ፈገግ የሚያሰኝ ጽሁፍ ያስነብባል።
ጥር 12 ቀን 1987 ዓ.ም በወጣው ህትመት ደግሞ “የባሕር ዳር ክለቦች አንደኛ ዙር ውድድር ሊጠናቀቅ ነው፤ አምባሰል ሳያቋርጥ አይቀርም” የሚል ዘና የሚያደርግ እና ረዥም አርዕስት ያለው ጽሁፍ ተመልክቻለሁ። በኵር የስፖርት አምድ ትኩረት ሊሰጣቸው እና መፍትሔ የሚሹ ጉዳዮችም ከተሳታፊ የሚቀርቡ አስተያየቶችን ያስተናግድ እንደነበር ከሰነዱ ለማወቅ ችለናል።
መስከረም ሁለት ቀን 1990 ዓ.ም ከአዴት በተላከ ጥቆማ የትምህርት ቤቶች ስፖርት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ያስገነዝባል። የስፖርት አምዱ ከኢትዮጵያ ሚሊኒየም ወዲህ በተለይ ከ2005 ዓ.ም በኋላ ከአጫጭር ዘገባዎች በተጨማሪ አልፎ አልፎ ሰፊ የሀገር ውስጥ እና የውጪ ሰፋ ያሉ ትንታኔዎችን ማስነበብ የጀመረችበት ወቅት ነበር። ሚያዚያ ስድስት ቀን 2006 ዓ.ም እስካሁን ያልተተካውን ጀግናውን አትሌት “ማን ይተካው ቀነኒሳን” የሚል በሀገር ውስጥ ባስነበበችው ጽሁፍ ሰፋ ያለ ትንታኔ ይዛ ወጥታለች።
እነዚህን አነሳን እንጂ ለቁጥር የሚታክቱ ስፖርቱን የሚያነቃቁ፣ ለማህበረሰቡ ተገቢውን መረጃ የሚሰጡ፣ የሚያስተምሩ እና የሚያዝናኑ መረጃዎችን በኩር ጋዜጣ በስፖርት አምዷ አስተናግዳለች። ሁሉም በሚባል ደረጃ ሕግ እና ደንብ ወጥቶላቸው ለውድድር የቀረቡት ባህላዊ እና ዘመናዊ ስፖርቶች በስፖርት አምዳችን ሽፋን ማግኘታቸውን የጋዜጣዋ የ30 ዓመታት ታሪክ ያስረዳናል።
ብሄራዊ ቡድናችን በአፍሪካ መድረክ ያለው ተሳትፎ እና ችግሮቹ፣ የአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ፣ ውበቱ አባተ እና አሰልጣኝ ገበረ መድህን ኃይሌ በብሄራዊ ቡድኑ የነበራቸው የሥራ ዘመን፣ በ2016 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን ሴት አትሌቶች በዓለም አቀፍ መድረኮች ያስመዘገቡት አስደናቂ ውጤት፣ የታዳጊዎች ብክነት፣ የአሰልጣኝ ሰላም ዘራይ የአሰልጣኝነት ህይወት፣ የስፖርት ህክምና በሀገራችን፣ የትምህርት ቤቶች ስፖርት መዳከም፣ በአማራ ክልል የሚገኙ የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት ውጣ ውረድ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ የስፖርተኞች ስነ ምግባር እና አጭር ስፖርተኛ ለምን እንዳጣን በሀገር ውስጥ በትንታኔ ሽፋን ከተሰጣቸው ጉዳዮች ውስጥ ይገኙበታል። በአጠቃላይ ግን ሁለቱም የሰፖርት አምዶች ከ2010 ዓ.ም በኋላ በጥልቀት ሰፋ ባለ ትንታኔ ለመሸፈን ተሞክሯል።
ከአካባቢያዊ እስከ ሀገራዊ ትኩረት የሚሹ ዘገባዎች በአጠቃላይ ባለፉት 30 ዓመታት ሽፋን ተሰጥቷቸው በስፖርት አምድ ተዳሰዋል። ዛሬ ላይ ሆነን በዚህ የዲጂታል ዓለም እነዚህን የስፖርት ዘገባዎችን ስናስቃኛችሁ ምናልባትም ፈገግ ልትሉ ትችላላችሁ። ምክንያቱም በማይክሮ ሴኮንድ ተለዋዋጭ በሆነ የዲጂታል ዓለም እነዚህ የጋዜጣ ዘገባዎች የበረዱ ወይም ለቋንጣነት የቀረቡ ሊመስሏቹህም ይችላሉና ነው። ነገር ግን በወቅቱ በክልሉ ምንም ዓይነት የመገናኛ አውታር ባለመኖሩ በኵር ጋዜጣ ለአማራ ክልል ሕዝብ ብቸኛ የመረጃ ምንጭ እንደነበረች መዘንጋት የለበትም።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የታኅሳስ 7 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም