ከርሞ’ማ

0
12

አዲስ ዓመትን በደስታ፣ ተስፋ እና ጥሩ መንፈስ  መቀበል የኢትዮጵያዊያን ባህል ነው። ከአዲሱ ዓመት ጋር ብዙዎች መለወጥ ይፈልጋሉ። ያለፈው አሮጌ ዓመት ርሀብ፣ ችግር ስቃይ መፈናቀል፣ ጦርነት እና አስቸጋሪ ጊዜያት ዘመን ሲለወጥ አብረው እንዲያልፉ መመኘት አለ። ማመንም አለ።

የጳጉሜን ውኃ እንደ ፈዋሽ ጸበል ይቆጠራል። የቤት ቀለም መቀባት፣ ማጽዳት፣ ማደስ እና ቁሳቁስ ማሟላት ለአዲሱ ዓመት የሚደረጉ ዝግጅቶች ናቸው። እናቴ ለዓመት የተቀመጡ እቃዎችን በጳጉሜን ወራት ስታጸዳ እና ስታጥብ አስታውሳለሁ።

ከዚህ በመነሳት ይመስላል በሀገራችን አዲስ ዓመትን ለመለወጥ፣ ለመሻሻል እና ለአዲስ ሕይወት የእቅድ መጀመሪያ ያደረግነው። ከርሞ’ ማ እንላለን። አዲስ ዓመትን ለነገሮች መጀመሪያ እናደርጋለን። ባላገሩ ከሚስቱ ቢጣላ እንኳን መስከረም ይጥባ ብሎ አብሮ ይከርማል።ውኃ ይጉደል ይላል።

መስከረም ጨፍጋጋው ፊት ፈታ፣ ደመናው ቀለል፣ ዝናቡ ጋብ የሚልበት ብርሃናማ ወር ነው። የቸገረው ሰው ክረምቱን በጎመን አልፎ ገብስ የሚያገኝበት ጊዜ ነው። እሸቱ ይደርሳል። ገብሱ ይደርሳል።

በአዲሱ ዓመት ለማግባት፣ ለመውለድ፣ ለመጀመር፣ ለማቆም፣ ለመሻሻል እና ለሌሎች ነገሮች በሚሊዮን የሚቆጠር ሰው በየቤቱ ያቅዳል። በአዲሱ ዓመት’ማ የሚለው ብዙ ነው።

አዲሱ ዓመት በራሱ ሁሉን ነገር  እንደሚለውጥ፤ ነገሮች እንደሚያስተካክል እና መልካም መንፈስ እንዳለው ማሰባችን በእቅዶቻችን ላይ ይስተዋላል።

ዘመን በራሱ ከእኛ የበለጠ ጉልበታም ሆኖ  ይታያል። ዘመን የበለጠን እንመስላለን። ጊዜ ጉልበታም ሆኖ ራሱ ነገሮችን እንዲለውጥ እንፈልጋለን፡፡ ጊዜን ዳኛ፣ ፈራጅ፣ አድራጊ ፈጣሪ ማድረግ በኪነ ጥበብ ሥራዎች እና ቃላዊ ንግግራችን ውስጥ ይታያል። ሁሉም ዓለም ያሉ ሰዎች ያቅዳሉ። አውሮፓውያን ጥር አንድን ሲያከብሩ በአዲስ ያቅዳሉ። እነሱ ተሳክቶላቸዋል። እኛስ?

እኛ የሚጎድለን ምክንያት ነው። “ለምን” የሚለው  የሕይወት ጥያቄ አልተመለሰም። ይህ አለመመለሱ በየመስከረሙ እንድናቅድ ያደርገናል። በመስከረም አቅደን ጥቅምት ላይ ከርሞ’ማ እንላለን። ሲሰለቸን ሁሉንም ትተነው በዘፈቀደ መኖርን እንመርጣለን።

የሰብእና እና አመለካከት ለውጥ አሰልጣኙ ጂም ሮን አንድ ዝነኛ አባባል አለው፡፡ “ለምን የሚለውን ከመለስህ እንዴት የሚለው ቀላል ነው” የሚል፡፡ ለምን የሚለው የህይወት ጥያቄ ለነገሮች ሁሉ ቁልፍ ሆኖ ይጠቀሳል፡፡

ለምን የሚል ቃል የስኬትን በር የሚከፍት ሚስጥራዊ ቁልፍ ይመስላል። የሰው ልጆች ዓላማቸውን ለማግኘት ብዙውን ጊዜ በጣም ይፈተናሉ። ምን እንደሚያነሳሳን ለማወቅ እንቸገራለን። ነገር ግን ይህን ‘ለምን’ የሚል ቁልፍ ካገኘን በኋላ ወደ ‘እንዴት’ የሚወስደው መንገድ በሚገርም ሁኔታ ይገለጣል።

ለምን የሚለው ጥያቄ እውነተኛ ዓላማችንን እንድናገኝ ያደርገናል። ዓላማን ማግኘት ደግሞ የሰሜን ኮከብን እንደማግኘት ነው፤ የብርሃን አቅጣጫ እየሰጠ ወደ ድርጊታችን ይመራናል።

ለምን ነው የምማረው የሚል ሰው ትምህርት አይከብደውም፡፡ ቢከብደው ይጠይቃል እንጂ ከበደኝ ብሎ አይቀመጥም፡፡ እጅ አይሰጥም፡፡ ከኋላው ያስቀመጠው ምክንያት አለ፡፡ ጎበዝ ተማሪ ሆኜ የእናቴን ሕይወት መቀየር አለብኝ ይላል፡፡ ፓይለት መሆን እፈልጋለሁ ይላል፡፡ ጎበዝ ተማሪ መሆን እንዳለበት ያውቃል፡፡ አለማንበብ አይችልም፡፡ ለምን ቢባል እናቱ የምትኖረው በድህነት ነው፡፡ መስነፍ በእናቱ ላይ የድህነትን ሕይወትን ማስቀጠል እንደሆነ ይሰማዋል፡፡ ጠንክሮ ያጠናል፡፡ ‘ለምን’ የሚለው ቃል ምክንያት ነው፡፡ ዓላማን የሚጠቁም ኮምፓስ ነው፡፡

ፍላጎትን የሚያቀጣጥል፣ ቁርጠኝነትን የሚያነሳሳ እና በጽናት እንድንቀጥል አንቀሳቃሽ ኃይል ነው። ‘ለምን’ የሚለውን ስንረዳ ማንኛውንም ‘እንዴት’ መቋቋም እንችላለን። ፈተናዎች አይመልሱንም፡፡ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ አንገኝም፡፡

እቅዶቻችን ምንድን ነው የሚጎድላቸው? ብዙውን ጊዜ ምክንያታዊነት የጎደለው እና ተጠያቂነት በሌለበት ሁኔታ ነው የምናቅደው።

ብዙ ሰዎች እውን ያልሆኑ ወይም ከመጠን በላይ ትልቅ የሆኑ ግቦችን ያወጣሉ። ይህም በአንድ ጊዜ ብዙ ነገር ለማድረግ መሞከርን ይጨምራል። ይህ ደግሞ ተስፋ በማስቆረጥ ወደ ውድቀት ያመራል።

በሞቅታ ማቀድ ሌላው እቅዶች እንዲወድቁ ሊያደርግ የሚችል ችግር ነው። ስፖርት እሠራለሁ የሚልን የመሰሉ ድፍን ያሉ እቅዶች መቼም አይሳኩም። ለምን? ዝርዝር ነገሮች በሚገባ አልተቀመጡላቸውምና። ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያስፈልጉ ግልጽ  እና ተግባራዊ እርምጃዎች ይጎድላቸዋል።

ማቀድ ተዓምር አይደለም። ሁሉም ሰው ያቅድ ይሆናል። ከግብ የሚያደርሰው ዲሲፕሊን ከሌለ ከንቱ ድካም ነው። እውነተኛ እድገት ዘላቂ ልማዶችን በመገንባት ነው የሚመጣው።

እቅዶች ተጠያቂነት ከሌላቸው ይከሽፋሉ። ማበረታቻ እና ተጠያቂነት የሚሰጡ ጠንካራ የጓደኞች፣ ቤተሰብ ወይም የአጋሮች  ድጋፍ ስርዓት ከሌለ ግለሰቦች ግስጋሴያቸውን ሊያጡ እና ሊቋረጡ ይችላሉ።

በጉዞው አለመደሰት እቅድን እንዳይሳካ ያደርገዋል። በመንገድ ላይ ትናንሽ ድሎችን ከማክበር ይልቅ የመጨረሻው ውጤት ላይ ብቻ ማተኮር ተስፋ አስቆራጭ ሊሆን ይችላል። መጠነኛ እድገትን አለማድነቅ ብስጭት ይፈጥራል። እያንዳንዷን ጉዞ ማድነቅ እና ለወደ ፊት እድገት ነዳጅ ማድረግ ያስፈልጋል። በሒደቱ መደሰት እንጂ ውጤቱ ስንደርስበት ምንም ነው።

የእቅድ እና ሰብዕና ግንባታ አሰልጣኝ ትሬሲ ኬኔዲ እቅዶች እንዴት እንደሚሳኩ ጽፏል። ግቦች በበቂ ሁኔታ በዝርዝር መቀመጥ አለባቸው።

ለምሳሌ አንድ ሰው “በ2018 ዓ.ም ጤናማ መሆን እፈልጋለሁ” የሚል ታላቅ እቅድ ሊኖረው ይችላል። ድፍን ያለ እቅድ ነው። ነገሮች በበቂ ዝርዝር ካልሆኑ፣ ወይም የምንፈልገውን በግልጽ ካላሳዩ፣ አእምሯችን ስኬት ምን እንደሚመስል አያውቅም። ትኩረታችን ይከፋፈላል። ተነሳሽነት እናጣለን። ጉልበታችንም ይሟጠጣል።

መፍትሔው ዝርዝር ሐሳቦችን ማስቀመጥ ነው። የምንፈልገውን እና ስኬት ምን እንደሚመስል ግልጽ ዕይታ ያስፈልገናል። ጤናማ መሆን ምን ማለት ነው? በሳምንት ስንት ጊዜ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ያስፈልገናል? ምግባችን ምን ዓይነት ነው? የስኳር አጠቃቀማችን ምን ይመስላል? እንዲሁም ስጋ በምን መጠን ነው የምንመገበው? የሚሉ ጥያቄዎችን በዝርዝር ማስቀመጥ አለብን።

ግቦችዎን SMART ማድረግ አለብን። Specific (የተለዩ)፣ Measurable (የሚለኩ)፣ Attainable (የምንደርስባቸው)፣ Relevant (አግባብነት ያላቸው)፣ Timely (በጊዜ የተገደቡ) ማድረግ ያስፈልጋል።

ሌላው በአዲስ ዓመት እቅድ ውስጥ መካተት ያለበት ቁም ነገር ዲሲፕሊን የሚል ጽንሰ ሐሳብ ነው። ይህ ቃል በቀጥታ ቢተረጎም ያያዙትን መስመር “ግግም” ብሎ መጓዝ ማለት ነው። ለምሳሌ በ2018 20 ኪሎ ግራም ክብደት እቀንሳለሁ ያለ ሰው ወደ ተግባር ሲገባ ብዙ የሚያሰናክሉ የውጪም የውስጥም ፈተናዎች ይገጥሙታል።

እነዚያ ፈተናዎች የቱንም ያህል ቢበዙ ሥራን አለማቋረጥ ማለት ነው። እናት ወይም አባቱ መሞቱን ሰምቶ ሬዲዮ ወይም ቴሌቪዥን ዜና የሚያነብ ሰው የዲሲፕሊን ማሳያ ነው። ሰበብ መደርደር አይጠቅምም እንጂ ሁሉም አሸናፊ ሰዎች ለመስነፍ ብዙ ምክንያቶች ነበሯቸው።

ይህ ዲሲፕሊን ደግሞ የሚመጣው ለመለወጥ በምን ያህል መጠን ፈልገናል ከሚለው እና ለምንድን ነው ክብደት መቀነስ የፈለግሁት የሚለውን ጥያቄ ከመመለስ ነው። ይህ ጥያቄ የውስጣችንን እምነት ያሳድገዋል። እምነታችን ደግሞ የለውጥ ጉልበታችን ይሆናል። ባንችልም እንኳን እንደምንችል ማሰባችን ትክክል ነው። አዕምሯችን የምንደጋግመውን ነገር እውነት አድርጎ ይወስዳል።

ልጆችን ጎበዝ፣ ቆንጆ እያልን ማሳደጋችን በሰብእናቸው ላይ ዋጋ ያለው ነገር ነው። ቆንጆ እንደሆኑ ያምናሉ። ጀግና እንደሆኑ ያምናሉ። ባይሆኑም እንኳን አምነው መሆንን ይቀበሉታል። በለውጥ ሒደትም እንደዚሁ ነው። ለእቅዳችን ያለን እምነት ለመሳካት ያለውን አቅም ይወስነዋል። የማናምንበት ነገር ሊሳካ አይችልም።

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር ጳጉሜን 3 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here