ከስህተት የመማር ጥቅም

0
177

በሀገራችን በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኖረው ኢትዮጵያዊ ቅዱስ ያሬድ ወድቆ የመነሳት፣ የመጽናት እና የማደግ ተምሳሌት ነው። በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ስሕተት ብርቅ አይደለም። ከመጀመሪያው የሰው ልጅ አዳም ጀምሮ መሳሳት ሰውኛ ባሕሪ ነው።  ለዚህ ነው አልበርት አንስታይን “ስሕተት ያልሰራ ሰው ምንም ነገር አልሞከረም” ሲል የተናገረው።

የዜማ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ትውልዱ  አክሱም ነው።  ግዕዝ፣ እዝል እና አራራይ የተሰኙ ዜማዎችን የደረሳቸው እሱ ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እነዚህን ዜማዎች ዛሬም ድረስ ትጠቀምባቸዋለች።

በሰባት ዓመቱ አባቱ ሲሞትበት ጌዴዮን ከሚባል አጎቱ ጋር ይኖር ዘንድ እናቱ ወሰደችው። ያሬድ ከአጎቱ ጋር ሆኖ መዝሙረ ዳዊት ሲማር ይቆጣው እና ይገርፈው ነበር። በዚህ የተከፋው ያሬድ ማይኪራህ በምትባል ቦታ ተደብቆ ተቀመጠ። የአጎቱ ቁጣ መንስኤም ያሬድ ትምህርት በቀላሉ የማይረዳ በመሆኑ ነበር።

አንድ ቀን ያሬድ በአንድ ዛፍ ስር ተቀምጦ ሳለ አንዲት ትል በዛፍ ላይ ወጥታ ምግብ ለመብላት በተደጋጋሚ ስትሞክር፣ ስትወድቅ፣ አሁንም ስትሞክር እና ስትወድቅ ያያል። በኋላም ከስድስት ጊዜ  ሙከራ በኋላ  ያች ትል ዛፍ ላይ ወጥታ ምግቧን በሰባተኛው ሙከራ ስትመገብ  ይመለከታል።

ከዚህ በኋላም ቅዱስ  ያሬድ ከትል እንዴት አንሳለሁ ብሎ በማሰብ፣ ወደ አጎቱ ተመልሶ በመማር የሦስቱ ዜማዎች ደራሲ ሆኖ ስሙ ሲታወስ ይኖራል።

ድል ካርኒጌ ስኬታማ ሰው ከስሕተቶቹ የሚያተርፍ፤ እናም እንደገና በተለየ መልኩ የሚሞክር ነው” ሲል ተናግሯል። ቶማስ ኤዲሰንም እንዲሁ “አልተሳሳትሁም፤ አስር ሺህ አምፖል የማይሰራባቸውን መንገዶች ነው ያወቅሁት” ሲል ለሙከራዎቻችን እና ለስሕተታችን የምንሰጠውን ትርጉም እንድንቀይር ያደርገናል።

ስህተት መስራት የሙከራ ማረጋገጫ ነው። መሳሳት የመማሪያ መንገድ ነው፤ አዲስ አቅጣጫ እና ያልታዬ መስመር እና ፈጠራ ማግኛ መንገድ ነው።

ስለመውደቅ እና መሳሳት ስናነሳ ሕጻናትን መርሳት የለብንም። ሕጻናት ከተወለዱ ጀምሮ መጀመሪያ ለመቀመጥ፣ ቀጥሎ ለማንቧቸት (ማንቧቸች) ፣ ከዚያም ለመራመድ፣ ከርምጃ በኋላ ለመሮጥ የሚያደርጉትን ሙከራ እና መውደቅ መነሳት ልብ ማለት ያስፈልጋል።

ስንት ቀን ወድቀው ተነስተው ይሆን፤ ስንት ቀን ተፈንግለው ይሆን፤ ስንት ቀን መሬት እና ወንበር ጋር ተጋጭተው ይሆን፤ ስንት ቀን ወላጆች ደግፈዋቸው ይሆን? ተፈጥሮ በራሱ ሕጻናትን እንዲቆሙ፣ እንዲራመዱ ይገፋፋቸዋል። ሕጻናት ወደቅሁ ብለው ባሉበት አይቀሩም። ከወደቁበት እንዲነሱ ጥረት ያደርጋሉ፤ ውስጣቸው የመነሳት፣ የመራመድ እና የመጓዝ ጉጉት አለባቸው።

ጆን ማክስዌል “ፌሊንግ ፎርዋርድ” በሚለው መጽሐፉ መሳሳት እና መውደቅ ለእድገት መረማመጃ  የመሰረት ድንጋዮች ናቸው ይላል። በዚህም መውደቅ የመጥፊያ ድርጊት ሳይሆን ወደ ፊት መራመጃ ስልት ተደርጎ መወሰድ አለበት ይላል። ብዙ የስኬት ጫፍ ላይ የደረሱ ድርጅቶች እና ግለሰቦች በመሳሳታቸው ያልፈሩ፣ ወደ ኋላ ለመመለስ ያልሞከሩ እና በስሕተታቸው ውስጥ አንዳች መውጫ መንገድ መፈለግ የቻሉት ናቸው።

ደካማዎች ብዙ ጊዜ ከሁለት እና ሦስት በላይ ላይሞክሩ  ይችላሉ። ሲሳሳቱ እና ሲወድቁ በእድላቸው፣ በሰው፣ በጊዜ፣ በዘመን፣ በቤተሰብ ወይም ሌሎች ነገሮች በማሳበብ ተስፋ ይቆርጣሉ፤ የጀመሩትንም ተግባር ያቋርጣሉ።

ልዩነት የሚፈጠረው የመውደቅ እና የመሳሳት እድል ጠንካራ ሰዎች ዘንድ ሲደርስ ነው። ጀግኖች በችግሮቻቸው ውስጥ ሆነው መውጫ ቀዳዳ ይፈልጋሉ። ችግሩ ውስጥ ሆነው ማልቀስ ባልጠፋቸው ነበር። እነሱ ግን ማደጊያ እና የስኬት ማማ መውጫ መንገዶችን ማማተር ያውቃሉ።

በተዘጋ በር፣ በጨለማ ቀን፣ በጦርነት፣ በስደት፣ በርሃብ፣ በኪሳራ ውስጥ ሆነው ከዓመታት በኋላ ስለሚደርሱበት ስኬት ያልማሉ፣ ይተጋሉ። በኪሳራ ምክንያት የጀመሩትን ንግድ አያቋርጡም። አኩሪ አተር ቢረክስ፣ ተልባ መነገድ ይጀምራሉ። በሽንኩርት ቢከስሩ በሰሊጥ ለማትረፍ ያቅዳሉ፤ ያሳኩታል።

በአማራ ክልል ጦርነት ብዙ ተቋማት እና ግለሰቦች ኪሳራ ገጥሟቸው በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ይገኛሉ። ብዙ የንግድ ድርጅቶች ተዘግተዋል ወይም ወደ አዲስ አበባ ተዛውረዋል። ጀግኖች ግን ዛሬም በጦርነት መሀል ትናንት ያልነበረ የንግድ ዓይነት ጀምረዋል። ትናንት ያልተጀመረ ሕንጻ አጠናቀዋል።

ሰዎች የማይደፍሩትን ስራ ጀምረው ተለውጠውበታል። በትንሽ ንግድ ጀምረው ትልቅ ድርጅት መስርተዋል። የጦርነት ሁኔታው እስኪለወጥ እጃቸውን አጥፈው አይቀመጡም፤ በሁኔታው ውስጥ ለመቀጠል አስተሳሰባቸውን ይለውጣሉ እንጂ። ጆን ማክስዌል “ስሕተት ወይም መውደቅ አይቀሬ ነው፤ ወደ ፊት መስፈንጠሪያ አድርገው” የሚለው ለዚህ ነው። ስኬት የውድቀት ተቃራኒ አይደለም። ይልቅስ ውድቀት የስኬት አካል ነው እንጂ።

መሳሳት እንቅፋት አይደለም፤ የማይሰሩ መንገዶችን መማሪያ ነው። በሙከራዎች መሀል የሚደረጉ ስሕተቶች የሚሰጣቸው ትርጉም እና አረዳድ የጥንካሬ እና የድካምን ፍሬ ይወስኑታል። አሸናፊዎች ጥሩ ባለሙያዎች ሆነው ሳለ ምን ያህል ትምህርት መማር እንዳለባቸው፤ ራሳቸውን በማሳደግ እና ማብቃት ላይ ያተኩራሉ። ተሸናፊዎች ደግሞ ምንም እውቀት ሳይኖራቸው መቼ ጎበዝ ባለሙያዎች ተብለው እንደሚጠሩ በማሰብ ይራባሉ። ለውጪው ዓለም ብዙ ትኩረት ይሰጡና ውስጣቸውን የሸክላ ኳኳታ ይሞሉታል።

ጆን እንደሚለው በሰዎች መካከል ልዩነት የሚፈጥረው የቤተሰብ ሁኔት፣ሀብት፣ ትምህርት፣ እድል፣ሳይሆን ለውድቀት ያላቸው እምነትና ግምት ነው። ጠንካራ እና ደካማ ሰዎች ሁለቱም በሕይወታቸው ይወድቃሉ፤ ይሳሳታሉ። ልዩነቱ ደካማው ወደ ኋላ፤ ጠንካራው ወደ ፊት መውደቁ ነው። መውደቅህ ካልቀረ ትንሽም ርምጃ ብትሆን ወደ ፊት ውደቅ ይላል ጆን።

ደካማዎች ሌሎችን ይወቅሳሉ፤ ጠንካራዎች ኀላፊነት ይወስዳሉ። ደካማዎች ተመሳሳይ ስሕተት ሲሰሩ ጠንካራዎች ከስሕተቶቻቸው ይማራሉ። ደካማዎች ላለመሳሳትእና ላለመውደቅ ሲጠነቀቁ ጀግኖች መሳሳት እና መውደቅ የጉዟቸው አንዱ ክፍል እንደሆነ ያምናሉ።

ኋላ ቀር ልምምዶችን የሙጥኝ ማለት የደካማዎች መገለጫ ነው። ከሺሕ ዓመታት በፊት የተሄደበት መንገድ፤ ችግሮች የተፈቱበት ስልት፤ ከዘመናት በፊት የነበረ እውቀት ለዛሬ ችግሮቻቸው ሁሉ መፍትሔ ይሆናል ብለው ያስባሉ። ማሰባቸው ብቻ አይደለም፤ የአሁኑን ዘመን ከመረዳት ስለሚከለሉ አዳዲስ እውቀቶችን አይቀበሉም። ያረጁ እና ጎታች ልማዶችን መለወጥ ጀግኖች የሚያደርጉት ስራ ነው። ደካማዎች ትናንት በገጠማቸው አደጋ ይታሰራሉ፤ ጀግኖችማ አዲስ ፈተናዎች ውስጥ ራሳቸውን ያስገባሉ። አይሳካልኝም ብለው ስለሚጀምሩ ደካማዎች የከንፈራቸውን ፍሬ ይበላሉ፤ ጀግኖች ይህ ነገር በዚህ መልኩ አይሰራም ብለው ያምናሉ። አዲስ መንገድ ይፈልጋሉ። ሰዎች ለዓመታት ባላሰቡት መልኩ ያስባሉ። እብደት የሚመስሉ ተግባራትን ይጀምራሉ። ማንም ሰው ያልተራመደበትን መንገድ በበረዶ ግግር መሀል ብቻውን እንደሚጓዝ ተኩላ፤ ብቻቸውን ይጓዛሉ። በጊዜው ሰው አይረዳቸውም። አይደግፋቸውም። በኋላ ግን ፍሬያቸውን በማየት ሁሉም ሰው እነሱን ለማየት ይጓጓል።

ብዙዎች በሕይወት ጉዞ ብዙ ተግባራትን ጀምረዋል። አንድ ርምጃ፣ አንድ ኪሎ ሜትር፣ አርባ ሁለት ኪሎ ሜትር የተጓዙ አሉ። ጀግኖች በጽናት ያሰቡትን ይቋጫሉ። ደካማዎች ዋናው መገለጫቸው ጀምሮ ማቋረጥ ነው። ከዚህ ዕይታ በመነሳት ጆን ማክስዌል ሰው ከሆንህ መሳሳትህ እንደማይቀር መቀበል አለብህ ይላል።

በሰዎች ውስጥ ያጋጠሙ ውድቀቶች ምናልባትም ተጓዦች ምን ያህል ርቀት  እንደቀራቸው ካለመረዳት የስኬት ደጃፍ ሲደርሱ ተስፋ በመቁረጣቸው የተከሰቱ ስለመሆናቸው ጆን ጽፏል። ሰዎች ሁልጊዜ የሚያደርጉትን ነገር የሚደጋግሙ ከሆነ የሚያገኙትም ውጤት ያንኑ ነው። ተመሳሳይ ነገር በማድረግ የተለየ ውጤት መጠበቅ እብደት ነው እንደሚለው አልበርት። ሽንብራ ዘርቶ ስንዴ እንደመጠበቅ ዓይነት ቅዠት ውስጥ ያስገባናል።

በአጠቃላይ መውደቅ የፈጠራ ምንጭ ነው። ብዙ የፈጠራ ውጤቶች የተገኙት ከድግግሞሽ ሙከራ በኋላ ነው። በየ መሀል መውደቅ ነበር። መውደቅን ከማሸነፍ የተነሳ ውጤቱ ግን ስኬት ሆኗል። መውደቅ ጥንካሬንም ይሰጣል። በተደጋጋሚ የሚሞክሩ ሰዎች በተደጋጋሚ የመውደቅ እና የመነሳት አቅም ያዳብራሉ። አንድ ቀን የወደቀ ሰው ምናልባትም ለምን ወደቅሁ ብሎ ተስፋ መቁረጥ እና መደናገጥ ሊሰማው ይችላል። ሒደቱ ሲደጋገም ግን ጥንካሬን ማግኘቱ አይቀርም።

መውደቅ የሚሰጠን በራስ የመቆም የኀላፊነት ጉልበት አለ። ሕጻናት ደግፉኝ ልቁም፣ እቀፉኝ፣ አግዙኝ አይሉም። ወላጅ የአንጀት ነገር ሆኖ ያግዛቸዋል እንጂ። ሁሉም ሰው ውስጥ ድብቅ አቅሞች አሉ። በልምድ ካልመጣ በቀር ሰው ተፈጥሮው በራሱ የመቆም እና ነጻነት የማግኘት ነው። ሕጻናት ብቻቸውን ሲወድቁ ተመልከቷቸው አያለቅሱም። ከወንበር ጋር ሲጋጩ ግንባራቸውን አሻሽተው ዝም ይላሉ። ሰው እንዳላቸው፣ እንደተመለከታቸው ካወቁ ግን እንባቸው ይወርዳል፣ እሪ ይላሉ። እንደማይደግፉት፣ ብቻውን እንዳለ የተረዳ ሰው በውድቀቱ ምክንያት ራሱን ለመቻል፣ በራሱ አቅም ለመኖር መፍጨርጨር ይጀምራል። ለራሱ ሕይወት የማንንም ርዳታ አይጠብቅም። ራሱን በራሱ ለማኖር ኃላፊነት ይወስዳል።

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here