“… ከስድስት ሰዎች አንዱ…”

0
304

ዓለም አቀፉ የአካል ጉዳተኞች መብት ኮንቬንሽን በአንቀጽ አንድ እንዳመላከተው አካል ጉዳተኝነት ለረጅም ጊዜ የአካል፣ የአዕምሮ ወይም የስሜት ሕዋሳት እክል የሚፈጠር ነው::  አካል ጉዳተኝነት በማህበረሰቡ የተሳሳተ አመለካከት ምክንያት  ሙሉና ትርጉም ያለው ተሳትፎ  ማድረግ የማይችሉ ሰዎችን ያጠቃልላል።

አካል ጉዳት ማለት  የአካል ክፍልን ማጣት ወይም የተግባር መገደብን የሚያመላክት ፅንሰ ሀሳብ ነው። አካል ጉዳተኝነት ማለት ደግሞ ከሌሎች ሰዎች ጋር እኩል ተሳትፎ እንዳያደርጉ የሚያስችል የአካል ጉዳት፣ የአመለካከት ችግርና አካባቢያዊ መሰናክሎች ድምር ውጤት ነው። በዓለም ላይ የተለያየ አይነት አካል ጉዳተኝነት የሚያጋጥም ሲሆን  ዐይነ ስውርነት፣ መስማት መሳን፣ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት፣ ማየትና መስማት መሳን እንዲሁም ተደራራቢ የአካል ጉዳት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

የዓለም ጤና ድርጅት እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር 2023 ያወጣው መረጃ እንደሚያመላክተው አንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን  ሕዝብ የተለያየ አይነት የአካል ጉዳት አጋጥሟቸዋል። ይህ አሃዝ 16 በመቶ የሚሆነውን የዓለም ሕዝብ ቁጥር የሚወክል ነው። ይህም የአካል ጉዳት ከስድስት ሰዎች በአንዱ ላይ አለ ማለት ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በታሕሳስ ወር 1993 እ.አ.አ ባጸደቃቸው 22 ደንቦች እና ድንጋጌዎችን ስንመለከትም አካል ጉዳተኞች ምንም ልዩነት ሳይደረግባቸው በህብረተሰቡ ውስጥ ባሉ ሁሉም እድሎች እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግም በተለያዩ በሕግ ማእቀፎች የአካል ጉዳተኞች ተደራሽነትን ማካተቱንና ለጉዳዩ አጽንኦት መስጠቱን እንመለከታለን::

የፌደራል ሴቶች እና ማህበራዊ ሚኒስቴር መረጃ መሠረት ከ20ኛው ክፍለ ዘመን ጀምረው ከወጡና ልዩ ልዩ የአካል ጉዳት ያለባቸውን ሰዎች ምርታማና ብቁ ዜጎች ለማድረግ አስተዋጽዖ ካደረጉ ሕጎችና ደንቦች መካከል እኤአ በ1973 ዓም የወጣው የተሐድሶ ሕግ ነው:: በዚህ ሰነድ ውስጥ ማንም አካል ጉዳት ያለበት ሰው በሁሉም ህብረተሰባዊ አገልግሎት የመሳተፍ መብት እንዳለው ሰፍሯል:: ለአካል ጉዳተኞች መብቶች ከሚደረግ ጥበቃ ጋር በተያያዘም ከማንኛውም አገልግሎት ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ማድረግ ወንጀል መሆኑ ተደንግጓል:: ይህ ድንጋጌ በተባበሩት መንግስታት አባል ሃገራት ዘንድ ስራ ላይ እንዲውል ተደርጓል። እኤአ ከ1950 ዎቹ ጀምሮ ሕጎች፣ ደንቦችና ፖሊሲዎች ወጥተው በጦር ሜዳ አካላዊ ጉዳት ለደረሰባቸው ጀግኖችና የተለያዩ አይነት አካል ጉዳት ላለባቸው ሰዎች ሃገር አቀፍ የምክር፣ የሥራ ስምሪትና ህጋዊ የተሃድሶ አገልግሎት በመስጠትና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ በማድረግ ምርታማ ዜጎች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል። እኤአ በ1980  የአሜሪካ የአካል ጉዳተኞች መብት ጥበቃ ተቋም ማንኛውም ዜጋ አካል ጉዳተኛ በመሆኑ ማንኛውንም ህዝባዊ አገልግሎቶች እንዲያገኝና አቅሙ የፈቀደውን ሥራ መስራት እንዲችል እንዲሁም ከመገለልና መድልዎ የጸዳ የአሠራር ስርዓት እንዲዘረጋና ህገወጥ ድርጊቶችን የሚፈጸሙ ተቋማትን መከላከል የሚያስችል ሕግ አውጥቷል::

የአካል ጉዳተኞችን ተደራሽነት ከሚመለከቱ ዓለም አቀፍ የሕግ ማዕቀፎች መካከል የሕፃናት መብቶች ኮንቬንሽን (አንቀጽ 23) ፣ የአፍሪካ የሰብአዊ መብቶች ቻርተርና የ “ILO” ስምምነት የኢንተር አሜሪካን ኮንቬንሽን ተጠቃሾች ናቸው:: የማዕቀፎቹ ዋና የትኩረት አቅጣጫ በአካል ጉዳተኞች ላይ የሚደርስ ሁሉንም አይነት መገለልና አድልዎ ማስወገድ ነው። ከእንቅፋት የጸዳ አካባቢን ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ ማድረግ ስንል ሁሉንም አይነት መሰናክሎች በማስወገድ የአካል ጉዳተኞችን መብት እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን በተጨባጭ ማረጋገጥ ነው::

ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽነት ማለት ከአመለካከት ለውጥ ጀምሮ አካል ጉዳተኞች እኩል እድል እንዲያገኙና ፍላጎቶቻቸውንና እኩል ተጠቃሚነታቸውን በተለየ ሁኔታ በመመልከትና ትኩረት በመስጠት በተለያዩ ምርቶችና አገልግሎቶች አቅርቦቶች፣ በህንጻዎችና የመንገዶች ኮንስትራክሽን፣ በአካል ጉዳት አይነት ሊቀርቡ በሚገባቸው ልዩ ልዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችና በየተቋማቱ በሁሉም አቅም ሰዎች ሊጠቀሙባቸው የሚገቡ መገልገያዎችን በመገንባት በማሻሻል ምቹ የሥራ አካባቢን መፍጠር ማለት ነው:: የሥራ አካባቢን ምቹ በማድረግ የአካል ጉዳተኞችን የመብት ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት አኳያ የሚያስፈልገው ራምፕ እና ሊፍት/ሊፍት ብቻ ነው የሚል የተዛባ አመለካከት ይስተዋላል:: እነዚህን የቴክኖሎጂ ውጤቶች በሁሉም ተቋማት አሟልቶ መገኘት መልካም ጅምር ቢሆንም ከመሰናክል  ነጻ የሆነ ምቹ የሥራ አካባቢ በማዘጋጀት በአገልጋይነት መንፈስ የተገልጋይ እርካታን መፍጠር ያስፈልጋል::

ከመሰናክል  ነጻ የሆነ ምቹ የሥራ አካባቢ ማለትም ከበር እና ከመተላለፊያ ስፋቶች እስከ ወለል ፣ ከመብራት ቆጣሪ ቁመቶች እስከ በር እጀታዎች እንዲሁም እንደ አካል ጉዳቱ አይነት ልዩ ልዩ የድምጽና ሌሎች መረጃ ሰጪ ምልክቶችን አሟልቶ መገኘት የተገልጋይንና አገልጋዮችን የስራ ግንኙነት ውጤታማ በማድረግ ረገድ የጎላ ድርሻ አለው:: ለአንድ ትንሽ ልጅ፣ ለአንድ አረጋዊና ለአንድ ነፍሰ ጡር ሴት የምናደርገው ድጋፍ የተለያየ ቢሆንም ሁሉም ለአደጋ የተጋለጡ መሆናቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት ከእንቅፋት ነፃ የሆነ አካባቢ ሊፈጠርላቸው ይገባል::

በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለ ኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ምጣኔ የተጠኑ ጥናቶች ግን 17.6 በመቶ ሕዝቧ ከአካል ጉዳት ጋር እንደሚኖሩ ያሳያል::

የአማራ ክልል ሴቶች ህፃናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የአረጋዊያን እና አካል ጉዳተኞች ዳይሬክተር አቶ መንበሩ የወርቅ የመንግስት ሠራተኞች ማዕቀፍ ውስጥ የአካል ጉዳተኞች አመታዊ ድጋፍ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1/2013 ተፈፃሚ ያርጋል::

መሥሪያ  ቤቶች በዕቅድ ዝግጅት፣ ፓሊስ፣ ስትራቴጂ እያደረጉ  ያሉትን ትግበራ ክትትል እና ድጋፍ ያደርጋል:: እያንዳንዱ አገልግሎት አሠጣጥ እና ምርት ማምረት ላይ የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ ታሳቢ ያደረገ ነው:: ለምሳሌ ግንባታ ሲደረግ፣ ንድፍም ሲሠራ ታሳቢ ማድረግ፤ በተቋም የሚገኙ ለምሳሌ የእንቅስቃሴ ችግር ላለበት ቢሮ ከምድር ላይ ተመቻችቶላቸዋል ወይ ? ፣ አይነስውራን አናባቢ አላቸው ወይ? ፣ የሥራ ቁሳቁስ በሬል አለ ወይ ? ከውጭ ለሚመጡ ሠራተኞች (አካል ጉዳተኛ ከሆነ) አመቺ ሁኔታ መኖር እንደሚገባው ነው የሚያስቀምጠው::

በርዕሰ መስተዳደር ምክር ቤት የወጣውን መመሪያ የማስፈፀም ኃላፊነት የተሠጠው ቢሮ ሁሉምን ቢሮዎችን ከተቀመጠው አለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ሕግ አንፃር ምን እየሠራ እንደሆነ እና መሥራት እንደሚገባው  መቆጣጠር እንዳለበት ይደነግጋል::

 

የሕግ አንቀጽ

  • በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 9 ንኡስ አንቀፅ /4/ ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሀገሪቷ ሕግ አካል እንዲሆኑ ይደነግጋል።
  • የሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 25 ስለእኩልነት መብት ሲዘረዝር ሁሉም ሰዎች በዘር፣ በብሔር፣ በቀለም፣ በፆታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ አመጣጥ፣ በሃብት፣ በትውልድ ወይም በሌላ አቋም ምክንያት ልዩነት ሳይደረግባቸው እኩልና ተጨባጭ የሕግ ዋስትና የማግኘት መብት እንዳላቸው ይደነግጋል። በዚህ አንቀፅ በአካል ጉዳት ምክንያት ልዩነት መደረግ እንደሌለበት በግልፅ ባያስቀምጥም “በሌላ አቋም ምክንያት” የሚለው ሐረግ አካል ጉዳትንም እንደሚጨምር ታሳቢ ይደረጋል ማለት ነው።
  • በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 41 ንዑስ አንቀፅ /5/ ስለአካል ጉዳተኞች መብት በግልፅ ያስቀመጠ ሲሆን፤ አንቀፁ “መንግሥት የአካልና የአዕምሮ ጉዳተኞችን ለማቋቋምና ለመርዳት የአገሪቷ ኢኮኖሚ በሚፈቅደው መጠን እንክብካቤ ያደርጋል” ይላል።
  • በኢትዮጵያ ሕንፃ አዋጅ ቁጥር 624/2001 በሀገሪቷ የሚገነቡ ሕንፃዎች ማሟላት ስለሚገባቸው አጠቃላይ ግዴታዎች ያስቀመጠ ሲሆን፤ በአንቀፅ 36 ስር የሚገነቡ ሕንፃዎች ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ ሊሆኑ እንደሚገባ አስፍሯል።
  • የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮንቬንሽን ስምምነት አዋጅ ቁጥር 676/2002 ላይ እንደተመላከተው ፣ የስምምነቱ ዋነኛ ዓላማ ሁሉም አካል ጉዳተኞች በሁሉም ዓይነት ሠብዓዊ መብቶችና መሠረታዊ ነፃነቶች ረገድ ሙሉ እና እኩል ተጠቃሚነት ያላቸው ስለመሆኑ ማረጋገጥ፣ ማሳደግና ለነዚሁ ጥበቃ ማድረግ፣ ብሎም ተፈጥሯዊ ክብራቸውን ከፍ ማድረግ ነው።

ምንጭ-  ፌደራል አቃቢ ሕግ

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የህዳር  1  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here