የረጅም ዓመታት የሀገረ መንግሥትነት ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ በውጭ የጠላት ኀይል ባለመደፈር ታሪኳ ተከብራ ብትኖርም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተከሰቱ ያሉ የሰላም መናጋቶች ግን ውስጣዊ አንድነቷን እየፈተኑ መጥተዋል:: የሚያግባባ የጋራ ሐሳብ የጠፋ ይመስል ግጭት እና ጦርነት መገለጫዋ ሆነዋል ለአብነት ሁለት ዓመታት የቆየው የሰሜኑ ጦርነት፣ አሁን ደግሞ አማራ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተስተዋሉ ያሉ ግጭቶች ተጠቃሽ ናቸው::
እነዚህ መፍትሄ የራቃቸው ግጭቶች እና ጦርነቶች ከራሱ አልፎ ለሌላው የሚተርፈው አርሶ አደር እንዲፈናቀል፣ ሠራተኛው ሥራ አጥ እንዲሆን፣ ተማሪውም ከትምህርት ውጪ እንዲሆን… አድርጓል:: የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኢትዮጵያ መፍትሄ ባልሰጠቻቸው ግጭቶች እና በሌሎች ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ከ20 ሚሊዮን በላይ ወገኖች እጃቸውን ለእርዳት እንደዘረጉ ማስታወቁ አይዘነጋም::
ሀገሪቱ አሁን ለገባችበት ቀውስ ከግለሰብ እስከ መንግሥት እውቅና የተሰጣቸው ምክንያቶችን ማስታወስም ይገባል:: የተዛባ ትርክት፣ የሕገ መንግሥት ሁሉን በእኩልነት አቅፎ አለመነሳት፣ የወሰን እና የማንነት ጥያቄዎች ምላሽ አለማግኘት፣ ኢፍትሐዊ የሆነ የልማት ተጠቃሚነት መኖር እና ሌሎችም ለቀውሱ ምክንያቶች ሆነው ይነሳሉ:: እነዚህ ሐሳቦች እውነታነት ያላቸው መሆኑን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት 15ኛ መደበኛ ጉባኤ ጥር 28 ቀን 2016 ዓ.ም በተካሄደበት ወቅት ተናግረዋል::
ከአሚኮ ጋር ቆይታ የነበራቸው የኢፌዴሪ የሕገ መንግሥት እና የፌደራሊዝም አስተምሮ ማዕከል ያስተምሮ እና ስልጠና ዳይሬክተር አቶ ዘውዴ ደምሴ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የሕግ የበላይነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ መግባቱን አስታውቀዋል:: አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ ሕግን የመተላለፍ አካሄዶች፣ በሕግ ብቻ ተገዢ ሆኖ ያለመሥራት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ሌሎችን ለማሳያነት አንስተዋል::
የሕግ የበላይነት መረጋገጥ የዜጎች ደኅንነት እንዲጠበቅ ከማድረግ ጀምሮ በሀገሪቱ በሁሉም አካባቢዎች በነጻነት ተንቀሳቅሶ የመሥራት መብት እንዲረጋገጥ፣ ሕብረ ብሔራዊነት እንዲጎለብት፣ ልማት እና ዕድገት እንዲፋጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል:: ይሁን እንጂ የሕግ የበላይነት አለመረጋገጥ መንግሥት በዘፈቀደ ውሳኔዎችን እንዲወስን ከማስገደድ ጀምሮ የዕለት ከዕለት ሥራው የዜጎችን ሰብዓዊ መብት በሚጥስ መልኩ እንዲያከናውን የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል:: ይህም ስርዓት አልበኝነት ነግሶ ዜጎች ደኅንነታቸው ጥያቄ ምልክት ውስጥ እንዲገባ እንደሚያደርግ አስረድተዋል::
የአማራ ክልልን ለ522 ቢሊዮን ብር ጠቅላላ ጉዳት የዳረገው የሰሜኑ ጦርነት በሠላም ስምምነት ቢቋጭም ጦርነቱ ግን መልኩን ቀይሮ በአማራ ክልል ቀጥሏል:: ለዘመናት ሲጠየቁ፣ ነገር ግን ምላሽ ሳያገኙ የቆዩ ጥያቄዎች ባሉበት ሁኔታ ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ በሚደረግ ጉዞ ማንነትን መሰረት ያደረጉ እገታዎች መፈጸማቸው፣ ለታገቱት ማስለቀቂያም በሚሊዮን ብር መጠየቁ፣ ከአማራ ውጪ የሚኖሩ ዜጎች ለዘመናት ከኖሩበት እንዲፈናቀሉ መደረጋቸው፣ የክልል ልዩ ኀይል መዋቅር ፈርሶ ወደ ፌዴራል የፀጥታ ኀይሎች እንዲገቡ መደረጉ የሰላም ቀውሱ እንዲባባስ አድርገው ክልሉ ለ10 ወራት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ እንዲቆይ አስገድደዋል::
ዘጠኝ ወራትን በተሻገረው ግጭት በርካታ ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውሶች ደርሰዋል:: አጠቃላይ የጉዳት መጠኑም ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚገመት የክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ የካቲት 28 ቀን 2016 ዓ.ም አስታውቋል:: ይህም ጉዳት ተቋማት ላይ ብቻ የደረሰ መሆኑም ተመላክቷል:: ሰብዓዊ ጉዳቱም ከፍተኛ መሆኑን እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ያሉ ተቋማት በተለያዩ ጊዜያት አረጋግጠዋል::
ግንቦት ወር መጨረሻ የሚጠናቀቀው ለሁለተኛ ጊዜ የተራዘመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንጻራዊ ሠላም እያስገኘ መሆኑን የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በተደጋጋሚ ተናግረዋል:: ይህም አንጻራዊ ሠላም መንግሥት በሕዝብ የሚነሱ የልማት ጥያቄዎችን በአጭር ጊዜ ለመመለስ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል::
ርእሰ መስተዳድሩ የክልሉን ሰላም ማረጋገጥ ቅድሚያ ጉዳይ መሆኑን አስታውቀዋል:: መንግሥት ለታጠቁ ኅይሎች ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ እያስተላለፈ መሆኑንም አስታውቋል:: ይህም መንግሥት ግጭቶችን በሰላም ለመቋጨት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል:: የተጀመረው የሕግ ማስከበር ዘመቻም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እና ለዚህም ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን ሊሰለፍ እንደሚገባ የፌዴራል እና የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ሚያዚያ 25 ቀን 2016 ዓ.ም የባሕር ዳር ከተማን የልማት ሥራ እንቅስቃሴ በጎበኙበት ወቅት ተናግረዋል::
በባሕር ዳር ከተማ ታላቁ የዓባይ ወንዝ ድልድይ ግንቦት 4 ቀን 2016 ዓ.ም በተመረቀበት ወቅት የተገኙት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአማራ ሕዝብ ራሱን አልምቶ ከችግር እና ከድህነት እንዲወጣ ለሠላም በትብብር ሊሠራ እንደሚገባ ጠይቀዋል:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ግጭቱ ከመገዳደል እና ከሁለንተናዊ ጥፋት ያለፈ ትርጉም እንደሌለው ተናግረዋል::
ግጭቶች ወደ ዕድገት የሚደረግን ጉዞ የሚገቱ እና የኢትዮጵያን አንድነት የሚሸረሽሩ በመሆናቸው በሰላማዊ መንገድ መቋጨት እንደሚገባም ጠቁመዋል:: በመሆኑም ለአማራ መብት፣ ዲሞክራሲ፣ ልማት እና ጥቅም መከበር የሚታገል ማንኛውም ግለሰብ እና ቡድን ከክልሉ መንግሥት ጋር በመነጋገር ለክልሉ ሠላም እና ልማት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ አስገንዝበዋል::
የሕገ መንግሥት እና የፌዴራሊዝም አስተምሮ ማዕከል ያስተምሮ እና ስልጠና ዳይሬክተሩ አቶ ዘውዴ ደምሴ የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ ዘላቂ ሰላምን ማስፈን ይቻላል:: ለዚህም መንግሥት የዜጎችን መሠረታዊ ፍላጎቶች ሊመልሱ የሚችሉ፣ የሀገሪቱን ዴሞክራሲ ወደ ፊት የሚያራምዱ፣ ተቋምን የሚገነቡ፣ ፈጣን የሆኑ የሕግ አገልግሎቶችን ሊሰጡ የሚችሉ አሠራሮችን እና ማሻሻያዎች በማርቀቅ መተግበር ሲገባ እንደሆነ ገልጸዋል::
የጦርነት መልካም ውጤት የለውም። እንኳንስ የርስ በርስ ጦርነት ይቅርና በሀገራት መካከል የሚደረግ ጦርነት በርካታ ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያ እና ማኅበራዊ ጉዳት እና ምስቅልቅልን አሳልፎ የሚቋጨው በድርድር እና ንግግር ነው:: ለዚህ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት አብነት ነው::
አሁንም በአማራ ክልል ያለውን ችግር በአጭር ጊዜ ለመፍታት መንግሥት ወታደራዊ ዘመቻዎችን ለጊዜው በማቆም እና የተፋላሚ ኅይሎችን ፍላጎት በማጤን ልዩነቶችን በውይይት እና በምክክር ለመፍታት መንግሥታዊ ኃላፊነቱን በቁርጠኝነት ሊወጣ ይገባል። በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪ ጄ.ማሲንጋ ሐሳቡን ያጠናክራሉ:: በኢትዮጵያ ጊዜያዊ ሀገር አቀፍ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲፈጸም አምባሳደሩ መጠየቃቸውን ከኤምባሲው ድረ ገጽ የተገኘው ጽሑፍ አስረጂ ነው:: አምባሳደሩ የታጠቁ ቡድኖች ፖለቲካዊ ዓላማዎቻቸውን በዐመፅ ለማሳካት እየገፉ መሆኑን ገልጸዋል:: ይህም “ሰላማዊ ዜጎች በተለያዩ ኀይሎች ከሕግ ውጭ ግድያ፣ የዘፈቀደ እስራት፣ አስገዳጅ ስወራ፣ ከግጭት ጋራ የተያያዘ ጾታዊ ጥቃት እና ሌሎችም ጥቃቶች እንዲፈጸሙባቸው እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል::
አምባሳደር ኧርቪን ጄ.ማሲንጋ ውይይትን ወደ ጎን ያለው ግጭት የመብት ጥሰቶች እንዲቀጥሉ ማድረጉን ገልጸዋል:: በመሆኑም በኢትዮጵያ በትጥቅ ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት ግጭት አቁመው በንግግር ሰላምን እንዲያሰፍኑ እና የሰብአዊ መብቶችን እንዲያከብሩ አሳስበዋል:: “በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱት የፋኖ ታጣቂ ቡድኖች ፊታቸውን ወደ ድርድር እንዲያዞሩ አምባሳደሩ ሲጠይቁ፤ ህወሓትም በኀይል ወሰን ለማስመለስ ከሚደረግ እንቅስቃሴ እንዲቆጠብ እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትም የሰላም ውይይትን እንዲቀጥል” አሳስበዋል::
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በዘላቂነት ሰላም እና ደኅንነት የተረጋገጠባት ሀገር እንድትሆን መንግሥት ሕዝብ የሚያነሳቸውን መሠረታዊ ጥያቄዎች ጊዜ ሳይሰጥ በመመለስ፣ በአሁኑ ወቅት በልማት ሥራው እየታየ ያለውን እንቅስቃሴ በተዛባ ትርክት ምክንያት ለጎሪጥ እየታየ ያለውን ሕዝብ በማቀራረብ፣ የሕዝብን ሐሳብ መሠረት ባደረገ አግባብ ሕገ መንግስቱን በማሻሻል፣ ለማንነት እና ለወሰን ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ በመስጠት የተረጋጋ ፖለቲካ እና ዘላቂ ሰላም የማስፈን ሚናውን ሊወጣ ይገባል:: ልዩነቶችን እና የግጭት መነሻ ምክንያት ናቸው የተባሉ ምክንያቶችን በስር ነቀል ይፈታልኛል? ያለችውን የብሄራዊ ምክክር ኮሚሽን በፍጥነት ወደ ተግባር ማሸጋገር ላይም ማተኮር ይገባል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም