ከብራናዉ እስከ ዲጂታሉ ማዕበል 

0
35

ስፖርት የዓለማችን ሁለንተናዊ ቋንቋ ነው። የሀገር ድንበር፣ የቋንቋ እና የባህል ልዩነት   ሳይገድበው በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በአንድ ስሜት ያስተሳስራል። የደስታ ጩኸት፣  የሲቃ እንባ እና የድል ፌሽታ… እነዚህ ሁሉ የስፖርት መገለጫዎች ናቸው። ነገር ግን እነዚህን ስሜቶች ከስታዲየም ጓዳ አውጥቶ በአራቱም የዓለም ማዕዘን በቢሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች   ዐይን እና ጆሮ የሚያደርስ አንድ ወሳኝ ሙያ አለ፤ የስፖርት ጋዜጠኝነት። ይህ ሙያ ውጤት መዝጋቢ ብቻ ሳይሆን፣ የታሪክ ጸሐፊ፣ የባህል አንጸባራቂ እና የማህበረሰብ ድምፅ ጭምር ነው።

ስፖርት ቢሊዮን ዶላሮች የሚንቀሳቀስበት ኢንዱስትሪ ሲሆን ጋዜጠኝነት የዚህ ኢንዱስትሪ የደም ሥር እና አንቀሳቃሽ ሞተር ነው። የስፖርት ጋዜጠኝነት ተጽዕኖ በጨዋታ ውጤት ብቻ ተወስኖ የሚቀር ዘረፍ አይደለም።  ከሜዳ አልፎ የህብረተሰቡን አስተሳሰብ፣ ባህል እና ማህበራዊ ግንኙነት በመቅረጽ ረገድ ከፍተኛ ኃይል አለው።

መንግሥታት እና የፖለቲካ ቡድኖችም ስፖርትን ለተለያዩ ዓላማዎች ይጠቀሙበታል። በዚህ ሂደት ውስጥ ጋዜጠኝነት ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ሀገራት እንደ ኦሎምፒክ እና ዓለም ዋንጫ ያሉ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ሲያስተናግዱ አዎንታዊ ገጽታቸውን ለዓለም ለማሳየት እና  የፖለቲካ ተጽዕኗቸውን ለማሳደግ ይጠቀሙበታል።

በሌላ በኩል  አምባገነናዊ መንግሥታት የህዝብን ትኩረት ከውስጥ ችግሮች ለማስቀየር እና የሀገር ፍቅር ስሜትን ለመጨመር ስፖርትን እንደ ፕሮፓጋንዳ መሳሪያ ይጠቀማሉ። በዚህ ጊዜ ታዲያ ነጻ የሆነ የስፖርት ጋዜጠኝነት የዚህን ፕሮፓጋንዳ ትክክለኛ ገጽታ የማጋለጥ ኃላፊነት ይጣልበታል።

የስፖርት ጋዜጠኝነት እንደ ዛሬው የተደራጀ እና የሰለጠነ ሙያ ሆኖ አልጀመረም። ታሪካዊ ጉዞው ከጥንታዊ ዘመን ሥልጣኔዎች ይጀምራል። በጽሑፍ የሰፈሩትን ስፖርታዊ ክንዋኔዎች ስንመረምር የሆሜር ሥራዎች ቀዳሚ መሆናቸውን የታሪክ ድርሳናት ያስረዱናል። ከሆሜር ጥንታዊ ሥራዎች ውስጥ አንዱ በሆነው ኢሊያድ (Iliad) በፓትሮክለስ የቀብር ስነ ስርዓት (Funeral Games for Patroclus) ላይ ከነበሩ ሁነቶች መካከል የስፖርት ውድድሮች ይገኙበታል::  የኢሊያድ  ድርሳን የሠረገላ ውድድር፣ ቡጢ፣ ትግል፣ ሩጫ እና ሌሎችም የስፖርት ውድድሮች መደረጋቸውን ያትታል።

ይሁን እንጂ “የስፖርት ጋዜጠኝነት” እንደ ሙያ መታየት የጀመረው ከብዙኃን መገናኛ (በተለይ ከመጽሔቶች እና ጋዜጦች) መወለድ ጋር ተያይዞ ነው። በዓለም ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የስፖርት ዜናዎችን ይዞ የወጣው የህትመት ውጤትም “ዘ ስፖርቲንግ ሜጋዚን” (The Sporting Magazine) እንደሆነ የግሎባል ኢንሳይት መረጃ አስነብቧል:: መጽሔቱ መታተም የጀመረው በእንግሊዝ ምድር ሲሆን እ.አ.አ. በ1791 ነው::

ይህም የስፖርት ጋዜጠኝነት  ራሱን የቻለ ዘርፍ እንዲሆን ትልቅ መሰረት ጥሏል። በ19ኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ ለስፖርት የተለየ ዓምድ መሰጠት የተጀመረበት ወቅት ነው። “ኒውዮርክ ሄራልድ” ጋዜጣ በተከታታይ የስፖርት ዘገባዎችን በማቅረብ  የመጀመሪያ  መሆኑን የሂስትሪ ላየን ዶት ኮም መረጃ ያስነብባል። ጽሑፎች ግን በአብዛኛው የውድድርን ውጤት ከመዘገብ የዘለለ ሚና አልነበራቸውም።

እ.አ.አ በ1883 የ”ኒውዮርክ ወርልድ” ጋዜጣ የስፖርት ክፍል በማቋቋም እና በተከታታይ የስፖርት ዘገባዎችን እና መጣጥፎችን በመሥራት ዘርፉ ትኩርት እንዲሰጠው አስተዋጽኦ አድርጓል። ታዲያ የቴሌግራፍ ፈጠራ ደግሞ ዘርፉን ይበልጥ አነቃቅቶታል:: ጋዜጠኞች የጨዋታ ውጤቶችን በቅጽበት ከሩቅ ቦታ ወደ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍሎች እንዲልኩ አስችሏቸዋል። ይህም ህዝቡ የጨዋታ ውጤቶችን ለማወቅ ቀናትን መጠበቅ ሳያስፈልገው በማግስቱ ጋዜጣ ላይ እንዲያነብ አደርጎታል።

በሃያኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ጋዜጦች በስፋት መሰራጨት ሲጀምሩ የስፖርት ዘገባዎች ከውጤት ዘገባነት አልፈው ወደ ትረካ (Narrative) ተሸጋገሩ። በዚህ ወቅት ጋዜጦች ለስፖርት የሚሰጡት የገጽ ሽፋን ሃያ በመቶ ከፍ እንዳለም መረጃዎች ይጠቁማሉ። የፈረንሳዩ ጋዜጣ  “ሎቶ”  የመጀመሪያው የስፖርት ጋዜጣ በመሆን እ.አ.አ በ1903 ሥራ መጀመሩን መረጃዎች አመልክተዋል:: ጋዜጣው በኋላ ላይ ስያሜውን ወደ ሌኪፕ (L’Equipe) ቀይሮታል::

እ.አ.አ በ1920ዎቹ ራዲዮ ለመጀመሪያ ጊዜ የውድድርን ድምፅ እና ስሜት በቅጽበት ወደ እያንዳንዱ አድማጭ ቤት ይዞ በመግባት አዲስ አብዮት ፈጠረ። የመጀመሪያው የራዲዮ የስፖርት የቀጥታ ስርጭት የተላለፈው እ.አ.አ. በ1921 ሲሆን የቡጢ ስፖርት ውድድርን ነበር ያስተላለፈው። የቀጥታ ስርጭት (Live streaming) ቴክኖሎጂዎች አነስተኛ ተመልካች ያላቸው ስፖርቶች እንኳን ዓለም አቀፍ ተደራሽነት እንዲኖራቸው አስችሏል።

የቴሌቪዥን መምጣት ደግሞ የስፖርት ጋዜጠኝነትን ከፍ ባለ ደረጃ እንዲቀመጥ አስችሎታል። የመጀመሪያው የቴሌቪዥን የስፖርት ስርጭት የተላለፈውም እ.አ.አ. በ1936 በበርሊን ኦሎምፒክ ወቅት ነበር። የቴሌቪዥን ምስላዊ ይዘት ከድምጽ ጋር ተዳምሮ ለተመልካቾች ይበልጥ ማራኪ እና የተሟላ እንዲሆን አስችሏል። እንደ ኢኤስፒኤን (ESPN) ያሉ ሙሉ በሙሉ በስፖርት ላይ ያተኮሩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች መመስረት ደግሞ የስፖርት ሽፋን ቀኑን ሙሉ እንዲሆን አስችሏል

ባለፉት ጥቂት ዐስርት ዓመታት ውስጥ የቴክኖሎጂ እድገት የስፖርት ጋዜጠኝነትን ገጽታ ከመሰረቱ ለውጦታል። ከወርሃዊ መጽሔት እስከ ዕለታዊ ጋዜጣ፣ ከዚያም ወደ ራዲዮ እና ቴሌቪዥን የተጓዘው ሙያ ዛሬ በዲጂታል አብዮት ማዕበል ውስጥ ይገኛል።

የኢንተርኔት መምጣት በህትመት ውጤት፣ በራዲዮ እና በቴሌቪዥን  ላይ መወሰን እንዲያከትም አድርጓል። ይህም በዘመናችን የታየው ትልቁ የስፖርት ጋዜጠኝነት ለውጥ ቢሆንም ዘርፉን ግን  መስቀለኛ መንገድ ላይ እንዲቆም አድርጎታል። በማህበራዊ የትስስር ገጽ ማንኛውም ሰው መረጃን ማሰራጨቱ ሀሰተኛ እና ያልተረጋገጡ ዜናዎች እንዲፈበረኩ ምክንያት ሆኗል።

የዲጂታል ሚዲያ መስፋፋት ይበልጥ ጋዜጦች እና መጽሔቶች ላይ የህልውና አደጋ ፈጥሯል።  እንደ “ስፖርትስ ኢላስትሬትድ” ያሉ አንጋፋ ተቋማት ከፍተኛ የሠራተኛ ቅነሳ ማድረጋቸው እና “ኒውዮርክ ታይምስ” የስፖርት ክፍሉን መዝጋቱ ዘርፉ የገጠመውን ፈተና በሚገባ ያሳያል።

ይሁን እንጂ የወደፊቱ ጊዜ ጨለማ ብቻ አይደለም። የጋዜጠኞች ሚና ከዜና ዘጋቢነት ወደ ጥልቅ ተንታኝነት እና አውድ አስረጂነት እየተሸጋገረ ነው። የመረጃ ትንታኔ (Data analytics) እና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ከውጤት በስተጀርባ ያሉ ታሪኮችን ማቅረብ አዲስ እድል ይዞ መጥቷል።

የስፖርት ጋዜጠኝነት ሁሌም በለውጥ ላይ ያለ ሙያ ሲሆን ዛሬ ላይ የዲጂታል አብዮቱ እያናወጠው ይገኛል። የጋዜጠኛው መሣሪያ ከብዕር እና ወረቀት ወደ ዘመናዊ ስልክ እና የረቀቀ ቴክኖሎጂ  ቢለወጥም የሙያው ዋና ዓላማ እና ነፍስ ግን አይለወጥም::

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የነሐሴ 12 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here