በባሕር ዳር ከተማ የሚገኘውን አዲሱን የዓባይ ድልድይ ተከትሎ ወደ አየር ጤና በሚያስኬደው የአስፋልት ዳር በግራ በኩል ሰፋፊ የከብቶች ቤት ይታያል:: ከዋናው አስፋልት እና በፎቆች መካከል በሚገኘው በዚህ ቦታ በጥቃቅን እና አነስተኛ ተደራጅተው ከብቶችን የሚያረቡ ሰዎች የሚሠሩበት አካባቢ ነው::
እኛም ከሰሞኑ በወተት ሀብት ከተሰማሩት ወ/ሮ ብዙሀረግ ታደሰ ጋር ቀጠሮ ስለነበረን ወደዚሁ ቦታ አቅንተን ነበር:: ከወይዘሮ ብዙሀረግ የሥራ ቦታ እንደደረስንም ወቅቱ የክረምቱ መግቢያ በመሆኑ የእነሱም ሆነ የከብቶች መውጫ እና መግቢያ ውኃ እንዳያቁርና ጭቃ እንዳይሆን ሲደለድሉ፤ ጣራው ላይ ካለው ቆርቆሮ የሚያፈስ እንዳለው በባለሙያ ሲያስፈትሹ አገኘናቸው::
ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ እያከናወኑት ስላለው ሥራ፤ “ካሉኝ ከብቶች አብዛኞቹ የወተት ላሞች ናቸው:: በክረምት ርጥበት ከተሰማቸው ደግሞ ጡታቸው ስለሚቆስል የተሻለ መቆሚያ፣ መውጫ መግቢያ እንዲሁም መተኛ ቦታ ስለሚያስፈልጋቸው ያን እያደረግን ነው” በማለት ገለጹልን:: ግቢውን በዐይናችን ስናማትር የጥጆች ማቆያ፣ የከብቶች የሳር መከመሪያ፣ ማደሪያ እና መመገቢያቸው ለየብቻ ተሠርቶ ተመለከትን::
በባሕር ዳር ዙሪያ የተወለዱት ወይዘሮ ብዙሀረግ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት በባሕር ዳር ከተማ ነው:: ወይዘሮዋ በ1982 ዓ.ም የተሻለ ኑሩ ፍለጋ ወደ አረብ ሀገራት በመሄድ ለሁለት ዓመት በሥራ ቆይተዋል:: በኋላ ወደ ሀገራቸው በመመለስ በጊቤ የኀይል ማመንጫ በወጥ ቤት ሠራተኝነት ተቀጠሩ:: በዚህ የሕይወት አጋጣሚ ከልጆቻቸው አባት ጋር በመተዋወቅ ትዳር መሰረቱ::
ወይዘሮዋ በትዳራቸው ሦስት ልጆችን ለማፍራት ቢታደሉም በ2003 ዓ.ም ባለቤታቸውን ሞት ነጠቃቸው:: በወቅቱ ከሀዘኑ ጋር ልጆቻቸውን በብቸኝነት የማሳደጉ ኃላፊነት ተደማምሮ ሌላ የሕይወት ፈተና ተጋረጠባቸው::
ባለታሪካችን ከሀዘናቸው ሳይወጡ ወደ ኖ”””ሩባት ባሕር ዳር ከተማ በመምጣት የነበራቸውን ጥሪት እየቆጠቡ ከልጆቻቸው ጋር መኖር ጀመሩ:: ኑሮ ፈተና ሆነባቸው፤ ልጆቻቸውን እንደበፊቱ ማብላት፣ ማልበስ… አቃታቸው:: ችግራቸውን የተረዱ ሰዎች “ልጆችሽ በጥሩ ሁኔታ እንዲያድጉ ለአሳዳጊ ወደ ውጭ ላኪያቸው“ በማለት መከሯቸው:: እርሳቸው ግን “ችግር ያልፋል:: ያን ጊዜ ደግሞ የሰውን ልጆች እያየሁ አላብድም!“ በማለት የሚችሉትን ሁሉ ሠርተው ልጆቻቸውን ለማሳደግ እንደወሰኑ ያስታውሳሉ::
ሠርው የመለወጥ ጠንካራ ዓላማ ያላቸው ወ/ሮ ብዙሀረግ የቀራቸው ገንዘብ ሳያልቅ ቤት ተከራይተው በዶሮ ማርባት ሥራ ለመሰማራት ወሰኑ:: ልጆቻቸውን ለማሳደግ በቁርጠኝነት የተነሱት ወ/ሮ ብዙሀረግ አንድ ዶሮ በአንድ ብር አራት ሺህ የ45 ቀን ጫጩቶችን ገዝተው በተከራዩት ቤት ማርባት ጀመሩ:: በወቅቱ የሥራቸውን እንቅስቃሴ የተመለከተው ጥቃቅን እና አነስተኛ ጽ/ቤት በወቅቱ የመሥሪያ ቦታ ሰጣቸው::
መኖሪያቸውንም መሥሪያቸውንም እዛው በማድረግ ሥራውን በየቀኑ በልምድ በማዳበር የገቢ ምንጫቸው ሆነ:: እንዳሰቡት መቀጠል ግን አልቻለም፤ የዶሮ በሽታ ሲነሳ ሙሉ በሙሉ ሞቱ:: ወይዘሮዋ በገጠማቸው ኪሳራ ሳይደናገጡ እንደገና ለመቀጠል መነሻ ገንዘብ ለማግኘት ሌላ ሥራ ለመሥራት ወሰኑ::
በወቅቱ / 2004 ዓ.ም/ ቀበሌ 14 ያለው አረጋዊያን ሕንጻ ይሠራ ስለነበር በቀን ሥራ በ30 ብር ሂሳብ መሥራት ጀመሩ:: ሥራው ግን አቅማቸውን ፈተናቸው:: ሁኔታቸውን የተመለከቱ ሌሎች ሠራተኞች ከሸክሙ ይልቅ ግንባታው በሚከናወንበት አካባቢ ሻይ እና ቡና እንዲያቀርቡ ገፋፏቸው::
በሰዎች ግፊት መጀመሪያ ሻይ እና ቡና ቆየት ብለው ደግሞ ቀለል ያለ ምግብ ለተጠቃሚው ማቅረብ ጀመሩ፤ ገቢያቸውም ጥሩ ሆነላቸው:: አብዛኞቹ ደንበኞቻቸው በተለይ ደግሞ ሹፌሮች ምግባቸው ጥሩ እንደሆነ በመረዳታቸው የተሻለ ገቢ የሚያገኙበትን ቦታ ጠቆሟቸው:: ጃዊ ካለው የስኳር ፋብሪካ ግንባታ በሥራ ስለሚመላለሱ የምግብ አቅርቦት ፍላጎት ቢኖርም ጥሩ ምግብ አቅራቢ ስለሌለ ወደዛ እንዲሄዱ ምክር ለገሷቸው:: እርሳቸውም ሥራ ሳይመርጡ የተወሰነ ጥሪት ከቋጠሩ በኋላ ወደ ቀደመው የዶሮ ርባታ የመመለስ ሀሳቡ ስለነበራቸው ሀሳቡን ተቀብለው የተወሰነ ጊዜ ከቆዩ በኋላ ወደ ጃዊ ሄደው ለመሥራት ወሰኑ::
በወቅቱ ልጆቻቸው ትልቋ ሁለተኛ ክፍል፣ መካከለኛዋ ቅድመ መደበኛ/ኬጂ ሦስት/ እና መጨረሻው ኬጂ አንድ ተማሪ ነበሩ:: ልጆችን ለቤተሰብ እና ጓደኛ አደራ ሰጥተው በ150 ብር ተመላላሽ አብሳይ በመቅጠር ወደ ጃዊ ከተማ ሄዱ::
ጃዊ በሚሠራው የስኳር ፋብሪካ አካባቢ ምግብ ቤት ከፈቱ:: ገበያቸው ከጠበቁት በላይ ሆነ:: ልጆቻቸውን እየተመላለሱ በማየት ለተከታታይ ሦስት ዓመታት በመሥራት 80 ሺህ ብር በመያዝ ወደ ባሕር ዳር ከተማ ተመለሱ::
በወቅቱ ልጆቹ በዕድሜ እያደጉ በመሆኑ ብዙ ጊዜን በአካል ተለይቶ መቆየቱ ለሌላ ችግር ያጋልጣቸዋል በሚል ስጋት ከጎናቸው ሆነው ለመሥራት ወሰኑ:: ልጆች መሰረታዊ የሆነው ነገር ተሟልቶላቸው እና ጥሩ በሚባል የግል ትምህርት ቤት እየተማሩ እንዲቀጥሉ ለማድረግ ደግሞ ያገኙትን ገንዘብ በባሕር ዳር ከተማ በሥራ በመሰማራት ገቢያቸውን ለማሳደግ ጊዜ አላባከኑም::
ወይዘሮዋ በፊት እንዳሰቡት በዶሮ ርባታ አልተሰማሩም:: ጥቃቅን እና አነስተኛ ዶሮ ለማርባት በሰጣቸው ቦታ ላይ ሁለት ጥጆችን በመግዛት በ2008 ዓ.ም በከብት ርባታ ተሰማሩ:: በወቅቱ እያንዳንዳቸው ዘጠኝ ሺህ ብር ያወጡ ሁለት የውጭ ዝርያ ያላቸውን ጊደሮች ገዙ:: ጥሩ ውጤት እንደሚኖራቸው በመተማመንም ነበር ወደ ሥራ የገቡት::
“የተወለድኩት ገጠር አካባቢ ስለሆነ ለእንስሳት ቅርበት አለኝ፤ ሥራውም ጥሩ ነው:: ነገር ግን ሥራውን ሥጀምር በልምድ ያዳበርኩት ነገር ይበዛል” በማለት ሥራው ብዙም እንዳላስቸገራቸው ያስታውሳሉ::
በአሁን ወቅት የ17 ከብቶች ባለቤት ናቸው:: ከእነዚህ ውስጥ አሁን ላይ የወተት ምርት የሚሰጡ (የሚታለቡት) አራቱ ብቻ ናቸው:: ቀሪዎቹ ደግሞ ሦስቱ ወይፈን ስለሆኑ ለሽያጭ እንደሚቀርቡና ሌሎች ደግሞ ክበድ (ለመውለድ የሚጠብቁ) መሆናቸውን በእጃቸው እየደባበሱ ነግረውናል::
ከብት ርባታ በፍቅር የሚሠሩት እንዲሁም ሙሉ ክትትልን እና ንጽህና የሚፈልግ ቢሆንም ለሠራ ደግሞ ለልፋት ተመጣጣን ዋጋ የሚከፍል እንደሆነ አስረድተዋል:: አሁን ከሚታለቡት ላሞች በቀን 40 ሊትር ወተት ለወተት ልማት እንደሚያስረክቡ ነግረውናል:: በሥራው ከራሳቸው አልፈው ለሁለት ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል::
ያ ሁሉ ችግር፣ ያ ሁሉ ውጣ ውረድ አልፎ በጥረታቸው ባፈሩት ሀብት ከልጆቻቸው በተጨማሪ የዘመድ ልጅም አብራ ማሳደግ እንደቻሉ ወ/ሮ ብዙሀረግ ነግረውናል:: አሁን ላይ የመጀመሪያ ልጃቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዲግሪ ተመርቃለች:: ሁለተኛዋ ደግሞ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በክሊኒካል ፋርማሲ ቀጣይ ዓመት ተመራቂ ናት፣ ሦስተኛው ደግሞ ቪዲዮግራፊ በመሠልጠን አሁን አዲስ አበባ ከተማ በሥራ ላይ ይገኛል::
በቪድዮግራፊ ሥራ ላይ የሚገኘው ልጃቸው እዮብ በላቸው እናቱ እነሱን ለማሳደግ ተነግሮ የማያልቅ ችግሮችን እንዳሳለፉ ያስታውሳል:: አሁንም ድረስ ልጆቻቸው መሥመራቸውን እንዳይስቱ በማስተካከል እና በመደገፍ ትልቅ አስተዋፅኦ እያደረጉ ያሉ ጀግና እናት እንደሆኑ ነው የሚገልፀው::
በቀጣይ በማድለቢያቸው ትልቁን የመብራት ቆጣሪ በማስገባት ከብቶችን ከማርባት በተጨማሪ የከብት መኖ ማቀነባበሪያ ለመክፈት ሃሳብ አላቸው:: ልጆቻቸውም ቢሆን ትምህርታቸውን በአግባቡ ካጠናቀቁ በኋላ የእርሳቸውን ሙያ በአግባቡ እንዲመሩ ፍላጎት እንዳላቸው ነው የገለፀልን::
ሥራውን በጀመሩ በ10 ዓመት ውስጥ ኑሮን በአግባቡ ከመምራት በተጨማሪ ተደራጅተው የመኖሪያ ቤት ቦታ የማግኘት ዕድል አግኝተዋል:: ሙያቸውንም ወደ ቀጣይ ትውልድ የማስተላለፍ እቅድ ለማሳካት በበለጠ እንደሚሠሩ ጠቁመዋል::
እናት እና አባቷን ከ10 ዓመት በፊት ያጣችው ወ/ሮ ሙሉእመቤት ይልማ ወ/ሮ ብዙሀረግ ከሦስት ልጆቻቸው በተጨማሪ አራተኛ ልጅ ሆና በጥሩ እንክብካቤ ማደጓን ትመሰክራለች:: ወ/ሮ ሙሉእመቤት ትምህርቷን ከመከታተል በተጨማሪ የሽመና ሙያ በመሰልጠን ወደ ሥራ ገብታለች:: አሁን ላይ ትዳር መስርታ ልጅ አፍርታለች:: ይህ ሁሉ የሆነው ደግሞ በአክስቷ ድጋፍ እንደሆነ ገልጻለች:: ከአክስቷ ሥራን ሳይንቁ ትንሽ ትልቅ ሳይሉ መሥራት እንደሚቻል መገንዘብ መቻሏንም ነው የምትገልፀው::
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም