የባሕር ዳር ከተማ በጎርፍ እንዳትጠቃ ለማድረግ የተፋሰስ ቦታዎችን የማፅዳት ሥራ እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል። በተለይም የጎርፍ መፋሰሻዎችን፣ ካለቦታቸው የሚጣሉ የፕላስቲክ ቆሻሻዎችን ፅዱ ለማድረግ እየተሠራ ስለመሆኑ ነው የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ እና ውበት መምሪያ ያስታወቀው።
ሐሳባቸውን የሰጡ ነዋሪዎች በበኩላቸው ለከተማዋ ውበት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ነው ለበኩር የተናገሩት።
የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ አቶ ፍቃዱ አለባቸው እንዳሉት በየአካባቢው ባሉ መፋሰሻዎች ውስጥ የሚጣሉ የፕላስቲክ ጠርሙሶች በቀላሉ የማይጠፉ ናቸው። ለጎርፍ የመጋለጥ ስጋት ቢኖርም በየአካባቢው ያሉ የሴፍቲኔት ጽዳት አገልግሎት ሠራኞች ስለሚያጸዱት ትልቅ እፎይታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል። ከዚህ ባለፈ ግን በቆሻሻ አወጋገድ ዙሪያ ለነዋሪው ስልጠና መስጠት እንደሚገባ ነው የገለፁት።
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ እና ውበት መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ፅጌረዳ አበበ በከተማዋ ባሉ 27 የፅዳት ማሕበራት እና ሌሎች አቅሞችን በመጠቀም መፋሰሻዎችን (ቦዮችን) በማጽዳት አረንጓዴ ባሕር ዳርን ለመፍጠር ሲሠራ እንደቆየ ገልፀዋል፡፡
ዋና ዋና የአስፋልት መንገዶችን ከመንገዶች ባለስልጣን ጋር በመተባበር ከተማዋ በጎርፍ እንዳትጠቃ ሰፊ ሥራ እንደተሠራ ኃላፊዋ ገልፀዋል፡፡
ከተማዋን ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ ሁሉም የሚጠበቅበትን እንዲወጣ ጥሪ ያቀረቡት ኃላፊዋ ሕብረተሰቡ ከቤቱ እስከ 20 ሜትር፣ ተቋማት ደግሞ እስከ 50 ሜትር ድረስ ያለውን አካባቢ የማጽዳት ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
የኮሪደር ልማቱ የሚሠራቸው የማፋሰሻ ቦዮች ዝግ በመሆናቸው ፍሳሽ ቆሻሻን ለመጣል የማይችል መሆኑን ያነሱት ወ/ሮ ፅጌረዳ ነባሮቹ በማፋሰሻ ቦዮች ውስጥ ቆሻሻ በሚጥሉት ላይ ከማስተማር በዘለለ (የንግድ ማሕበራትን ጨምሮ) አስፈላጊውን ቅጣት በመተግበር ችግሩን ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግ ነው የገለፁት፡፡
የፕላስቲክ ጠርሙሶች በከፍተኛ ደረጃ የከተማን ውበት ያሳጣሉ። በሌላ በኩል እንደገና አገልግሎት እንዲሰጡ በመሸጥ ገቢ ያስገኛሉ። በመሆኑም ይህንን በመገንዘብ ተጠቃሚነትም በማሳደግ፣ በዚያውም የከተማዋን ውበት መጠበቅ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ከሐምሌ 01 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ጽዱ ባሕር ዳርን ለመፍጠር ከሕብረተሰቡ ጋር የፅዳት እና ችግኝ ተከላ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ነው ኃላፊዋ ወ/ሮ ፅጌረዳ የገለፁት፡፡
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም