ከተማዋ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅቷን አጠናቃለች

0
118

በጎንደር ከተማ የጥምቀት በዓልን በታላቅ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ሥርዓት ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለፀ፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ስልጣናት ቆሞስ አባ ዮሴፍ ደስታ የሰጡትን  መግለጫ ዋቢ አድርጎ ኢዜአ እንደዘገበው የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ይዘቱን በጠበቀ አግባብ ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል።

በዓሉን ሃይማኖታዊ፣ ባሕላዊ እና ታሪካዊ ትውፊቱን በጠበቀ መንገድ ለማክበር ዐብይ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሠራ መሆኑንም ጠቅሰዋል። ለዚህም የጥምቀት በዓል የሚከናወንበት እና ታቦታቱ የሚያርፉበትን የፋሲለደስ የባሕረ ጥምቀት ስፍራ የጥገና ሥራ 95 በመቶ መጠናቀቁን ተናግረዋል።

የበዓሉን ስፍራ ውበትና ጽዳቱን የሚያስጠብቁ እና በዓሉን ለመታደም የሚመጡ ምዕመናን፣ ሊቃውንትን፣ ቀዳሾችንና አባቶችን እንዲሁም ሌሎች አንግዶችን ቦታ የሚያስይዙና ሰላሙን የሚያስጠብቁ ወጣቶች ዝግጅት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።

የጥምቀት በዓል ኢትዮጵያዊ መሠረቱን ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የመጣ መንፈሳዊ፣ ሃይማታዊና ባሕላዊ ትውፊታዊ ሥርዓት ያለው መሆኑን ጠቁመው፤ ዝግጁቱም ይህንን መሠረት ያደረገ ነው ብለዋል።

መንግሥት በኮሪደር ልማት በጎንደር ከተማ የሚገኘውን የመስቀል አደባባይ የቀደመ ታሪክ ጠብቆ በማልማት ለበዓሉ ልዩ ድምቀት ለማጎናጸፍ ያከናወናቸው ተግባራትንም አባ ዮሴፍ አመስግነዋል። ጥምቀትን ለማክበር ወደ ከተማዋ የሚመጡ እንግዶችና ጎብኚዎች ከበዓሉ በተጨማሪ በጎንደር ከተማና አካባቢው የሚገኙ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ቦታዎችን እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል።

በኲር የታኅሳስ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here