ከተረት በስተጀርባ

0
189

በኢትዮጵያ ባህል ውስጥ ተረት ተረት ሲባል “የላም በረት” የሚል መልስ እንሰጣለን:: ይህ የላም በረት ግን የከብቶች ማደሪያ ብቻ ሳይሆን የጥበብ ጎተራ፣ የፖለቲካ ትችት መድረክ እና የስነምግባር ትምህርት ቤት ነው:: ብዙዎቻችን ተረቶችን ለህጻናት እንቅልፍ ማምጫነት ብቻ እንወስዳቸዋለን:: ነገር ግን እንደ  ከበደ ሚካኤል (በታሪክና ምሳሌ)፣ ዶክተር ፈቃደ አዘዘ (በስነ-ቃል ጥናት) እና ሌሎች ምሁራን እንደሚያስረዱት የኢትዮጵያ ተረቶች የህዝብን ስነልቦና፣ የፖለቲካ ንቃተ-ህሊና እና የማህበራዊ ህይወት ውስብስብነት የሚፈቱ ቁልፎች ናቸው:: ዛሬ የተወሰኑ ተረቶችን ከፋይዳቸው  አንጻር እንመለከታለን::

በኢትዮጵያ የቃል ስነ ጽሑፍ ውስጥ እንስሳት የሰዎች ባህሪ እና የስልጣን መገለጫዎች ናቸው:: በአብዛኛው ተረቶች ውስጥ አንበሳ (ገዢ/ንጉሥ)፣ ጅብ (ስግብግብ/ተላላኪ) እና ቀበሮ (ብልጥ/ፖለቲከኛ) ሆነው ይቀርባሉ::

ቀጥሎ የቀረበውን ተረት ለአብነት እንመልከተው:: በአንድ ወቅት አንበሳ፣ ጅብ እና ቀበሮ በአንድነት አድነው አንድ ወይፈን ይጥላሉ:: አንበሳው ጅቡን “እስኪ ስጋውን አካፍለን” አለው:: ጅቡም እንደ ልማዱ ለሶስት እኩል ቦታ ከፈለ:: በዚህ ጊዜ አንበሳው ተቆጥቶ ጅቡን በጥፊ ሲለው አይኑ ፈጠጠ:: ቀጥሎ አንበሳው ቀበሮን “አንቺ አካፍይን” አላት:: ቀበሮም ምርጥ ምርጡን ስጋ ለአንበሳው ሰብስባ፣ ለራሷና ለጅቡ አጥንትና ሆድቃውን ብቻ አስቀረች:: አንበሳውም ተደስቶ “እንዲህ መካፈልን ማን አስተማረሽ?” ሲላት፣ “የጅቡ ዓይን መፍጠጥ ጌታዬ!” ብላ መለሰች::

ይህ ተረት የሚያሳየው ስለ ስጋ ክፍፍል ብቻ አይደለም። ፋይዳው “የፖለቲካ ሪያሊዝም” ነው:: በህብረተሰብ ውስጥ ፍትህ ሁልጊዜ በኀይል ሚዛን ላይ እንደምትወሰን፣ ጉልበት ያለው አካል ህግን እንደፈለገው ሊተረጉም እንደሚችል እና ደካማው ለመኖር ሲል በብልሃት (ዲፕሎማሲን) ካልተጠቀመ እንደሚጠፋ ያስተምራል:: ተረቱ ፍፁም አምባገነንነትን በዘዴ የሚተች  ሆኖ ነው የቀረበው::

ከበደ ሚካኤል ታሪክና ምሳሌ በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ በግጥም ያቀረቡት፣ እንዲሁም በኦሮሞ እና በወላይታ ፎክሎር ውስጥ በሰፊው የሚገኝ ተረት አለ:: ተረቱ ስለ ሀገራዊ አንድነት ወሳኝ መልዕክት አለው::

የሰውነት አካላት እጅ፣ እግር፣ አፍ፣ ጥርስ ተሰብስበው ሆድ ላይ አድማ አደረጉ:: እኛ እየደከምን እሱ ዝም ብሎ ይውጣል፣ ከዛሬ ጀምሮ አንሰራም አሉ:: እጅ አላጎርስም አለ:: እግር አልሄድም አለ:: አፍም አልከፈት አለ:: ከጥቂት ቀናት በኋላ ግን እጅ መንምኖ መንቀሳቀስ አቃተው:: እግር ዛለ፣ ሁሉም አካላት እየሞቱ መጡ:: ችግሩ የሆድ ብቻ ሳይሆን የሁሉም መሆኑ የገባቸው በጣም ዘግይቶ ነበር::

ይህ ተረት የስርዓት ጽንሰ-ሀሳብ ማስተማሪያ ነው:: በአንድ ሀገር ወይም ተቋም ውስጥ ያለ አንድ አካል (ለምሳሌ ገበሬው፣ ወታደሩ ወይም አስተዳዳሪው) የራሱን ድርሻ ካልተወጣ ወይም ከተገለለ፣ ጉዳቱ ለሁሉም ነው::  እርስ በርስ መደጋገፍን እና የአንዱ መኖር ለሌላው ዋስትና መሆኑን ተረቱ ያስተምራል::

ማሞ ቂሎ በኢትዮጵያ ተረቶች ውስጥ የሞኝ ሰው ተምሳሌት ነው:: ነገር ግን የእሱ ተረቶች ፋይዳ ከሳቅ ባሻገር ከባቢያዊ እውቀት ነው::

ማሞ ቂሎ በአንድ ወቅት ለቅሶ ደርሶ ሲመለስ ሰዎች የሰርግ ድግስ ጥለው ያያል:: የለቅሶ ቤት ዜማ እየጠራ እግዚኦ! እያለ ይገባል። ሰዎች ደብድበው “ከዚህ ይልቅ፣ እንኳን ደስ አላችሁ፤ ይውለዱ ይክበዱ አይባልም?” ብለው ይመክሩታል:: ማሞ ይህንን ይዞ ሲሄድ ዘመድ የሞተበት ሰው ቤት ይደርሳል:: እዚያም “እንኳን ደስ አላችሁ፣ ይውለዱ ይክበዱ” ብሎ ተደብድቦ ይባረራል::

ይህ ታሪክ አንድ እውነት በሁሉም ቦታ እንደማይሰራ ያስተምራል:: ትክክለኛ ነገርን በተሳሳተ ቦታ ማድረግ ስህተት መሆኑን ያስረዳል:: በተለይ ወጣቶች ነገሮችን እንደየ ሁኔታው መመርመር እንዳለባቸው የሚያስተምር፣ የመተጣጠፍ (የመላመድ) ክህሎትን የሚገነባ ድንቅ ተረት ነው::

አንድ ሀብታም ገበሬ ሊሞት ሲል ሰነፍ ልጆቹን ይጠራና “ልጆቼ በጓሮው እርሻ ውስጥ የተቀበረ ወርቅ አለና ቆፍራችሁ አውጡት” ብሎ ይሞታል:: ልጆቹ ወርቁን ለማግኘት እርሻውን በሙሉ ቆፋፈሩት:: ወርቁን አጡት:: ነገር ግን የተቆፈረው መሬት ለዘር ዝግጁ ስለነበር ዘሩበት:: በዚያው ዓመት ምርቱ እጥፍ ሆነ:: አባታቸው የተናገረው ወርቅ ምርቱ መሆኑን ዘግይተው ተረዱ::

ይህ ተረት በአቋራጭ መበልጸግን የሚጠላ ነው:: ሀብት የሚገኘው ከድካም እና ከስራ እንጂ ከተቀበረ ውርስ እንዳልሆነ ለትውልድ ያስተምራል:: ዛሬ ላይ ላለው “ቶሎ ልክበር” አስተሳሰብ ፍቱን መድኃኒት ነው::

አራቱ ሳንቲሞች እና የህይወት ሂሳብ በሚል ርዕስ በመስፍን ሀብተማሪያም በተሰበሰቡ የኢትዮጵያ ተረቶች ስብስብ ውስጥ የሚገኝ ተረት አለ:: በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በትንሽ የይዘት ልዩነት በስፋት የሚነገር የቃል ቅርስ ነው::

በአንድ ወቅት አንድ ንጉሥ ግዛታቸውን እየጎበኙ ሳለ በጠራራ ፀሐይ በግንባሩ ላብ እያረሰ የሚተዳደር አንድ አዛውንት ገበሬ ይመለከታሉ። ንጉሡም ወደ ገበሬው ቀርበው ጠየቁ::

ንጉሥ ይህን ያህል ደክመህ በቀን ስንት ታገኛለህ? ይሉታል:: ገበሬውም ንጉስ ሆይ በቀን አራት ሳንቲም አገኛለሁ ብሎ መለሰ:: ንጉሡም በመደነቅ “ታዲያ ይሄ ሁሉ ድካም ለአራት ሳንቲም ነው? በል እስኪ አራቱን ሳንቲም ምን እንደምታደርጋቸው ንገረኝ?” አሉት::

ገበሬውም በተረጋጋ መንፈስ እንዲህ ሲል መለሰ “ንጉሥ ሆይ ከአራቱ ሳንቲሞች አንዱን እበላዋለሁ፣ አንዱን እዳ እከፍልበታለሁ፣ አንዱን አበድረዋለሁ፣ አንዱን ደግሞ እጥለዋለሁ” አላቸው::

ንጉሡ ነገሩ ስላልገባቸው “በደንብ አብራራልኝ” አሉት:: ገበሬውም እንዲህ ሲል የህይወትን ምስጢር ፈታላቸው:: አንዱን እበላዋለሁ ያልኩት ለራሴ እና ለባለቤቴ የምንበላው የዕለት ጉርሳችን ነው:: እዳ እከፍልበታለሁ ያልኩት አርጅተው እቤት ለሚውሉ ወላጆቼ የምሰጠው ነው:: እነሱ በልጅነቴ ተንከባክበው አሳድገውብኛልና ያንን “የወላጅነት እዳ” እየከፈልኩ ነው::

አበድረዋለሁ ያልኩት ደግሞ ለልጆቼ የማወጣው ወጪ ነው:: ዛሬ ባበላኋቸውና ባስተማርኳቸው መጠን ነገ እኔ ስደክም መልሰው ይከፍሉኛል (ይጦሩኛል) እና ለእነሱ የማወጣው “ብድር” ነው:: አንዱን እጥለዋለሁ ያልኩት ደግሞ ለክፉ ቀን ሳይሆን ዝም ብዬ ደስታ እና ለመዝናናት የማጠፋው ነው፤ ይህ ተመልሶ የማይገኝ ወጪ ነውና የተጣለ› አልኩት:: ብሎ መለሰላቸው:: ንጉሡም በገበሬው ጥልቅ ማስተዋል እና የህይወት ፍልስፍና ተደንቀው ሽልማት ሰጡት ይባላል::

ይህ ተረት ለሞራል ግንባታ እና ለማህበራዊ ህይወት ያለው ፋይዳ እጅግ ከፍተኛ ነው:: የተፈጥሮ ዑደት እና ኃላፊነትን ያሳያል:: ተረቱ በሶስት ትውልዶች (አባት፣ አያት፣ እና ልጅ) መካከል ያለውን መስተጋብር በግልጽ ያስቀምጣል:: ልጆች የወላጆቻቸውን ውለታ እንደ እዳ እንዲቆጥሩ፣ ወላጆች ደግሞ ልጆቻቸውን ማሳደግ እንደ ኢንቨስትመንት (ብድር) እንዲያዩት በማድረግ ጠንካራ የቤተሰብ ትስስር እንዲኖር ያስተምራል። ዘመናዊው ትውልድ ወላጆቹን መርዳት እንደ ግዴታ/እዳ እንዲቀበል ያደርጋል::

ገቢን እንዴት ማስተዳደር እንዳለብን የሚያሳይ ቀለል ያለ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ነው:: ገቢ ለዕለት ጉርስ፣ ለወላጅ/ማህበራዊ ግዴታ፣ እና ለወደፊት ኢንቨስትመንት መከፋፈል እንዳለበት ያስተምራል::

አንዱን እጥለዋለሁ የሚለው ሀሳብ ሰው ማሽን አለመሆኑንና አልፎ አልፎ ለመዝናናት ወይም ለነፍሱ እርካታ የሚያወጣው ወጪ እንዳለ (ምንም እንኳን ብክነት ቢመስልም) የሚያሳይ እውነታ ነው:: ይህ ተረት፣ ማስተዋል ማለት የዩኒቨርሲቲ ዲግሪ መጫን ሳይሆን የህይወትን ዑደት እና የማህበራዊ ግዴታን ቅደም ተከተል ጠንቅቆ ማወቅ እንደሆነ ያስረግጣል::

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ተረቶች የትናንት አያቶቻችን የህይወት ፍልስፍናቸውን የቋጠሩባቸው ሰነዶች ናቸው:: ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው በስነጽሑፍ መሠረታውያን መጽሐፋቸው እንደገለጹት ስነቃል የማህበረሰቡ እስትንፋስ ነው:: ተረቶቻችንን ስንመረምር ስለ ዴሞክራሲ፣ ስለ ፍትህ፣ ስለ ስራ እና ስለ አንድነት የተሰሩ ረቂቅ ትንታኔዎችን እናገኛለን:: እነዚህን ተረቶች እንደገና አቧራቸውን አራግፎ ለትውልድ ማቅረብ የጠፋውን የሞራል እና የማህበራዊ እሴት መመለሻ ትልቁ መንገድ ሊሆን ይችላል::

 

ማረፈያ

አባባሎች

“የወደቅህበትን ቦታ አትመልከት፤ የተሰናከልህበትን እንጂ።” (ብልህ ሰው ውጤቱ ላይ ብቻ አያተኩርም፤ የስህተቱን መነሻ ምክንያት ያስተውላል እንጂ።) ላይቤሪያዊያ

“አይጥ በድመት ስትስቅ፣ በአቅራቢያዋ ጉድጓድ እንዳለ እርግጠኛ ሁን።” (ጠላትህ ወይም አቅም የሌለው ሰው ሲደፋፈርህ፣ የያዘውን ድብቅ አቅም ወይም መሸሸጊያ አስተውል/ጠርጥር።)  ናይጄሪያዊያን

“የማታውቀውን አዞ፣ በድንጋይ አትምታ።” (የማታውቀውን ወይም አቅሙን ያልገመትኸውን አካል አትፈታተን።) ታንዛኒያዊያን

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የታህሣስ 27 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here