ከተረጂነት ለመላቀቅ….

0
162

ግብርና ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት እድገት ዋነኛ  ዘርፍ ነው:: ያለግብርና የሰው ልጅ ህልውና ቀጣይነቱ አስተማማኝ አይሆንም:: ለዚህም  ነው ኢትዮጵያ ያላትን አቅም ሁሉ አሟጣ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን እና ምርትን በሚፈለገው መጠን ለማቅረብ ጥረት እያደረች የምትገኘዉ:: ኢትዮጵያ ለግብርናዉ ዘርፍ ትልቅ ቦታ ሰጥታ እየሰራች ትገኛለች:: በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለበጋ መስኖ ስንዴ ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ትገኛለች::  በስንዴ ልማት ላይ የተሻለ ሥራም እያከናወነች ነው:: ባለፉት ሦስት ዓመታት በበጋ ስንዴ ልማት የሚሳተፉ አርሶ አደሮች ቁጥር እና የክላስተር እርሻዎች በማስፋፋት የበጋ ስንዴ ምርቷን እየጨመረች መሆኑን መንግስት  እየገለፀ ነው:: ከአጠቃላይ በጀቷ ቀላል የማይባለውን መዋዕለ ነዋይ ከውጭ ስንዴ ለማስገባት እና ለማጓጓዝ የምታውለውን ወጭ ለመቀነስ ከፍተኛ ጥረት እያደረገች ትገኛለች:: ከተረጅነት እና ከጥገኝነት ለመዉጣት ሥራዎችን እያከናወነችም ነው::

በምግብ ሰብል ራስን ለመቻል፣ ለኢንዱሰትሪ ምርት ግብዓት  እና የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ከመኸር ሰብል ልማት በተጨማሪ በበጋ መስኖ ስንዴ ሰብልን ማልማት እንደ ሀገር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል:: የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በስፋት ከተጀመረ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በሽፋን እና ምርታማነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የግብርና ቢሮ መረጃ ያመለክታል:: የበርካታ አርሶ አደሮች ሕይወትም እየተቀየረ እንደሚገኝ አርሶ አደሮቹ ይናገራሉ::

አርሶ አደር ሲሳይ ግርማ በሰሜን ሸዋ ዞን የአንጎለላና ጠራ ወረዳ ቡራ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው:: አርሶ አደር ሲሳይ በበጋ ስንዴ ማምረት ከጀመሩ ዓመታትን አስቆጥረዋል:: በልፋታቸው ልክ ማግኘት የጀመሩ ግን የግብርና ባለሙያ ምክረ ሐሳብ መተግበር ከጀመሩ ወዲህ ነው:: አርሶ አደር ሲሳይ ስንዴ በበጋ  በማምረታቸው ቤተሰባቸውን ከመመገብ አልፈው ለገበያ እያቀረቡ ነው::  በ2015 የምርት ዘመን  60 ኩንታል ስንዴ እንዳገኙ በስልክ ለበኩር ተናግረዋል:: ወደ ሥራው ሲገቡ ስጋት የነበረባቸው ቢሆንም ከጀመሩት በኋላ ግን  የተሻለ ጥቅም እንዳገኙ ይናገራሉ:: በ2016 የምርት ዘመን በሁለት ሄክታር መሬታቸው ከ80 ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት አቅደው እየሰሩ ይገኛሉ:: ከመኸር ምርት በተጨማሪ ስንዴን በማምረቴ ተጨማሪ ጥቅም እያገኘሁ ነው ብለዋል::

ባለፈው ዓመት የምርት መሰብሰቢያ ኮምባይነር ተጠቅመው የሰበሰቡት አርሶ አደሩ በዚህ ዓመትም ከወረዳው እንደሚመጣላቸው እና ምርታቸውን እንደሚሰበስቡ ተስፋ አድረገዋል:: የውሃ መሳቢያ ሞተር ፓምፕ እየተከራዩ እንደሚያመርቱ ይናገራሉ:: በዘር ወቅት የአፈር ማዳበሪያ ችግር እንዳልገጠማቸው የተናገሩት አርሶ አደር ሲሳይ ለቀጣይ  መኸር እርሻ ሥራ በቂ የአፈር ማዳበሪያ እንዲቀርብ ጠይቀዋል::

ሌላው በስልክ ያነጋገርናቸው የሰሜን ሸዋ ዞን የአንጎለላና ጠራ ወረዳ ጨቄ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ገብሬ በቀለ አንድ ሄክታር ተኩል መሬታቸውን አርሰው በበጋ መስኖ ስንዴ ሸፍነዋል:: አርሶ አደሩ ስንዴ ፣ገብስ እና ባቄላ በስፋት እንደሚያመርቱ ነግረውናል:: ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ የበጋ መስኖ ስንዴ ማምረት  የጀመሩ ሲሆን የተሻለ ጥቅም እያገኙ  እንደሆነም ይናገራሉ:: በ2015 የምርት ዘመን ከ60 ኩንታል በላይ ስንዴ ያገኙ ሲሆን በዚህ ዓመትም የተሻለ ምርት ይጠብቃሉ:: የተሻለ የምርት ውጤት ለማግኘትም የተዘራውን ሰብል ከግሪሳ ወፍ በመጠበቅ እና ተባይን በመከላከል ላይ ይገኛሉ:: እንደ አርሶ አደር ገብሬ ገለፃ ባለፈው ዓመት ምርታቸውን በኮምባይነር በመሰብሰባቸው የባከነ ምርት አለመኖሩን ነግረውናል::

ከአረም ቁጥጥር እና ከኬሚካል አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ባለሙያ ክትትል እና ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው አስረድተዋል:: ተጨማሪ ድጋፍ ሲፈልጉም ለግብርና ባለሙያዎች በስልክ ደውለው እንደሚያማክሩ ነግረውናል::

የአንጎለላ እና ጠራ ወረዳ ግብርና  ፅ/ቤት የአትክልት እና ፍራፍሬ መስኖ ውሃ አጠቃቀም ቡድን መሪ ፀሐይ ገብረ ስላሴ ለበኩር ጋዜጣ በስልክ እንደተናገሩት በ2016 የምርት ዘመን አንድ ሺህ 775 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለመሸፈን ታቅዶ አንድ ሺህ 619 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈን እንደተቻለ አስረድተዋል:: ይህም የተሻለ አፈፃፀም እንደተከናወነ ያሳያል ብለዋል:: ሰብሉ ያለበት ቁመናም በጥሩ ሁኔታ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል:: ከዚህም ከ71 ሺህ በላይ ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል:: ለውጤታማነቱም በየደረጃው ያሉ አካላት ስራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ::

በወረዳው አርሶ አደሩ የበጋ መስኖ ስንዴ ጠቀሜታን ተረድቶ  ከመኸሩ የእርሻ ሥራ ባልተናነሰ እየሰራ ይገኛል ብለዋል:: ኋላ ቀር አሰራርን በመቀየር የእርሻ፣ የአጨዳ እና የመውቂያ መሳሪያ በዘመናዊ ቴክኖሎጅ በመተካት ትኩረት ሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል:: ወረዳው ቀድሞ የንቅናቄ መድረክ በማዘጋጀት የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እንደሰራም ይናገራሉ:: አርሶ አደሩም የካናል ጠረጋ ወይም የመስኖ ቦይ ጠረጋ ሥራዎችን እንዲሰራም ተደርጓል:: በአንጎለላ እና ጠራ ወረዳ ከስድስት መቶ በላይ የሞተር ፓምፕ እንዳለም ተመላክቷል::

የሰሜን ሸዋ ዞን የበጋ መስኖ ስንዴ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ የአትክልት እና ፍራፍሬ መስኖ ውሃ አጠቃቀም ቡድን መሪ አስካለ ይፍሩ ናቸው:: በዞኑ በበጋ መስኖ ስንዴ 39 ሺህ 646 ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ 30 ሺህ 140 ሄክታር ወይም 76 በመቶ በዘር መሸፈን መቻሉን ለበኩር ተናግረዋል:: አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎም ይጠበቃል:: ለዚህም አገልግሎት የሚውል 79 ሺህ 292 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እንደሚያስፈልግም በዕቅድ ተይዟል:: 30 ሺህ 84 ኩንታል ጥቅም ላይም ውሏል:: 29 ሺህ 804 ኩንታል ምርጥ ዘር መጠቀም እንደተቻለም ተናግረዋል::

የበጋ መስኖ ስንዴን በተመለከተ በዞኑ ለሚገኙ ወረዳዎች የንቅናቄ መድረክ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱን  አስረድተዋል:: ባለሙያዎቹ ለአርሶ አደሮች ክትትል እና ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል:: በአንዳንድ ወረዳዎች የአፈር ማዳበሪያ እጥረት እንደነበር ገልጸዋል:: እንደ ቡድን መሪዋ ገለጻ ከ85 በላይ ትራክተር በበጋ መስኖ ስንዴ ሥራ ላይ መዋላቸዉን ነግረዉናል:: አርሶ አደሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሥራዉ ለመግባት የተቸገረ ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥቅሙን እየተረዳ በራሱ ተነሳሽነት እያመረተ መሆኑን አስረድተዋል::

በአማራ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት ከ333 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ለማልማት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል:: በክልሉ በ2016 የምርት ዘመን 250 ሺህ ሄክታር መሬት  በስንዴ በመሸፈን ዘጠኝ ነጥብ አራት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል:: ለበጋ መስኖ ስንዴ 449 ሺህ 906 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ጥቅም ላይ እንደሚውል የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ያሳያል::

የክልሉ ግብርና ቢሮ ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር እና የውሃ መሳቢያ ሞተር ፓምፕ ለአርሶ አደሮች ለማቅረብ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል:: የከርሰ ምድር እና የገፀምድር ውሃን በመጠቀም አርሶ አደሩ ከዝናብ ጥገኝነት እንዲወጣ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራም እየተሰራ ነው:: በክልሉ ባለፉት ሦሥት ዓመታት በተካሄደው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት አበረታች ውጤት እየታየ መሆኑ በተለያዩ መድረኮች ይነገራል::

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር ግንቦት 5 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here