በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋለ የሚገኘው የሰላም እጦት ብዙዎችን ለሞት እና አካል ጉዳት እየዳረገ ነው:: ይህንንም እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ እና ሌሎች የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በተለያዩ ጊዜያት በማረጋገጥ ለሕዝብ ይፋ አድርገዋል::
የተለያየ መነሻ ምክንያትን ተንተርሰው እየተቀሰቀሱ ያሉ ግጭቶች መንገዶች እንዲዘጉ በማድረግም የሰዎች እና የምርት እንቅስቃሴ እንዲገታ አድርገዋል:: ይህም የምርት ዝውውር መገታት በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የማኅበረሰብ ክፍል ክፉኛ ፈትኗል:: የሥራ መስክ መፍጠሪያ የሆኑ ተቋማት ሥራቸውን በአግባቡ እንዳያከናውኑ በማድረጉ በርካታ የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸው የነበሩ ዜጎች ከሥራ ውጪ እንዲሆኑ አድርጓል:: ይህም በአንድም ይሁን በሌላ ሥርዓት አልበኝነቱ እንዲባባስ ተጽዕኖ ይፈጥራል::
በተደጋጋሚ እየተከሰቱ ያሉ መፍትሄ የራቃቸው ግጭቶች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖችን ከቀያቸው እያፈናቀሉ ናቸው:: የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኢትዮጵያ ከ20 ሚሊዮን በላይ ዜጎች እጃቸውን ለእርዳታ እንደዘረጉ አረጋግጧል:: የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ “የምግብ ርዳታ ያስፈልጋቸዋል ብዬ የለየኋቸው ከ15 ሚሊዮን አይበልጡም” ማለቱም የሚታወስ ነው::
በአሁኑ ወቅትም ስድስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው በመረጋገጡ የተቀናጀ ድጋፍ ተደራሽ እያደረገ መሆኑን የፌዴራል አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል:: እነዚህ አኃዞች በዋናነት የሚያመላክቱት ኢትዮጵያ ያጋጠማት የሰላም መናጋት አሳሳቢ በመሆኑ ዜጎች እንደፈለጉ ተንቀሳቅሰው የመሥራት መብታቸው እዚህም እዚያም በሚከሰቱ ግጭቶች እና ማንነትን መሰረት ባደረጉ ጥቃቶች መገደቡን ነው:: የዜጎች በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ተንቀሳቅሶ የመሥራት ሕገ መንግሥታዊ መብት መገደቡ ደግሞ በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዳያበቁ ያደርጋቸዋል:: ይህም በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ በሀገር ዕድገት ላይ ተጽእኖ መፍጠሩ አይቀርም::
ለመሆኑ ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ ለገባችበት የሰላም መናጋት ገዥ ምክንያቶች ምንድን ናቸው? የሚለውን መረዳት አስፈላጊ ነው:: የወሰን እና የማንነት ጥያቄዎች ምላሽ አለማግኘት፣ የሕገ መንግሥቱ ሁሉን አካታች አለመሆን፣ ለዘመናት የተሠራው የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት፣ ፍትሐዊ የልማት ሥራዎች በሁሉም አካባቢዎች አለመኖር፣ የተቀዛቀዘ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የመንግሥት ተቋማት ሠራተኞች የሚከፈላቸው ደመወዝ ዝቅተኛ መሆን እና መረን የለቀቀው የኑሮ ውድነት የግጭቶች መነሻ ምክንያቶች ናቸው::
የዓለም አቀፍ ሕግ እና የግጭቶች አፈታት ባለሙያው ባይሳ ዋቅወያ እ.ኤ.አ ጥር 2021 ኤስ ቢ ኤስ ለተባለ የአውስትራሊያ ሚዲያ (https://www.sbs.com.au) ድረ ገጽ ባጋሩት ጽሑፋቸው የግጭት መነሻ ምክንያቶችን በግልጽ ዘርዝረዋል:: የኢሕአዴግ የ27 ዓመታት አገዛዝ ኢትዮጵያዊነትን አመንምኖ የብሔር ማንነትን ያገዘፈ እንደነበር ያስታውሳሉ:: “ይህም ዛሬ የአብዛኛው ብሔር አክቲቪስት ወይም የፖሊቲካ ድርጅት ተቀዳሚ የቤት ሥራ የማንነት ጥያቄ እንጂ ኢትዮጵያዊነት አይመስለኝም” ሲሉ ተናግረዋል። የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አብዛኞቹ ብሔር ተኮር መሆናቸውንም እንደ መንስኤ አንስተዋል::
ክልሎች እንደ አንድ ነጻ ሀገር እና የክልል ድንበራቸውን እንደ አንድ ሀገር ዳር ድንበር እየቆጠሩ መምጣታቸው ሀገር አጣብቂኝ ውስጥ እንድትገባ ስለማድረጉም ያነሳሉ:: ይህም ለዘመናት በመልካም ጎረቤትነት አብሮ ይኖር የነበረውን የሌላ ብሔር ተወላጅን በአሰቃቂ ሁኔታ ማፈናቀል እና መግደል እየሰፋ እንዲሄድ በማድረግ ሕብረ ብሔራዊነት ከቃል ያለፈ ትርጉም እንዳይኖረው አድርጓል::
አንድ ብዙ ብሔሮችን ያቀፈ ሀገር የአስተዳደር ሥርዓቱን ሲያዋቅር በምሥረታው ወቅት የነበሩ ሕዝብ (ብሔሮች) በሙሉ በሀገሪቱ ፖሊቲካዊ እና ማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ የእኩልነት መብት እንዲኖራቸው ተደርጎ መሠራት እንዳለበት ያነሳሉ:: አለበለዚያ ይላሉ ጸሐፊው፣ አንዳንድ ብሔሮች በተለይም በሕዝብ ቁጥር ብዛት ወይም በተጽዕኖ አሳዳሪነታቸው ብቻ ከሌሎች የላቀ መብት ለራሳቸው ሲሰጡ ያንን እኩልነት የተነፈጉ ደግሞ ጊዜያቸውን ጠብቀው ወደ ግጭት ሊያደርስ የሚችል የማንነት ጥያቄ ማንሳታቸው አይቀርም። በሕዝብ ስምምነት ላይ ያልተመሠረተ አገር በቀላሉ ለርስ በርስ ግጭቶች ሰለባ ሊሆን እንደሚችልም ያምናሉ::
በእርግጥም የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ሲረቀቅ ሁሉንም ሕዝብ በእኩልነት ያሳተፈ አለመሆኑ ኢትዮጵያ ዛሬ ለገባችበት ቀውስ ተዳርጋለች:: የመወሰን እና የማንነት ችግር የሚነሳባቸው የራያ አላማጣ እና የወልቃይት ጉዳይ ከስምምነቱ በኋላ በአጭር ጊዜ እልባት ያገኛሉ የሚለው ጉዳይም የበርካቶች ነበር:: በእርግጥ እነዚህ ችግሮች በምን አይነት መንገድ ምላሽ ያገኛሉ? የሚለው በራሱ ሁለቱን ክልሎች ሳያግባባ ቆይቷል::
በአማራ ክልል በኩል እነዚህ አካባቢዎች ወትሮውንም የተወሰዱት ሕገ መንግሥቱ ከመረቀቁ በፊት በኀይል ነው፤ የሁለቱ ክልሎች ተፈጥሯዊ ድንበር ተከዜ ሆኖ እያለ በምንም ተዓምር ራያ እና ወልቃይት የትግራይ አካል ሊሆኑ እንደማይችሉ ሐሳብ ይነሳል:: ሌላኛው አካል ደግሞ ወደ ትግራይ መመለስ አለባቸው የሚል ሐሳብን ያንጸባርቃል::
የፌዴራል መንግሥቱ ከእነዚህ አካባቢዎች የተፈናቀሉ የሁለቱ ክልል ዜጎች ወደነበሩበት እንዲመለሱ፣ ጥያቄውም በሕዝበ ውሳኔ እንደሚመለስ ቢያሳውቅም እስካሁን መፍትሄ አላገኘም:: ይህም ለዳግም ጦርነት ምክንያት እንዳይሆን ተሰግቷል::
የሕዝብ ቁጥር እና ተምሮ ሥራ ያጣው ወጣት መጨመር ለኢትዮጵያም ሆነ ለቀጣናው አለመረጋጋት ስጋት ይዞ መምጣቱን ጸሐፊው በማከል ያስረዳሉ:: እንደ ጸሐፊው ገለጻ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት በተለየ መልኩ 65 በመቶ ወይም 72 ሚሊዮን የሚጠጋው ሕዝቧ ዕድሜው ከ24 ዓመት በታች ነው። ይህም ኢትዮጵያ የወጣቶች ሀገር መሆኗን የሚያረጋግጥ ነው:: በአንጻሩ ተምረው ሥራ ያጡት ቁጥር አሥራ አምስት ሚሊዮን የሚጠጋ መሆኑ ደግሞ የኢትዮጵያን የወጣት ትውልድ ምድርነት ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል::
ኋላ ቀር የፖለቲካ ባህል መኖር እና የተዛባ ትርክትም ለኢትዮጵያ አሁናዊ ቀውስ ምክንያት መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዱዓለም ናቸው:: መጋቢት 3 ቀን 2016 ዓ.ም የተቋሙን የስድስት ወራት አፈጻጸም አስመልክቶ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያለው የውይይት ባህል ደካማ መሆንን ለግጭቶች አለመብረድ እንደተጨማሪ ምክንያት አንስተዋል::
ታዲያ እነዚህ ሁሉ ከግለሰብ እስከ መንግሥት ለዘመናት በዝምታ የታዩ ጉዳዮች ዛሬ ላይ ኢትዮጵያውያን ለጎሪጥ እንዲተያዩ አድርገዋል:: ተደጋጋሚ ግጭት እና ይፋዊ ጦርነቶችም እየተደረጉ ነው:: ለአብነት የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት መቶ ሺዎችን ለሞት እና ለአካል ጉዳት ዳርጓል:: ይህ ጦርነት ምንም እንኳ በሰላም ስምምነት የተቋጨ ቢሆንም አሁንም ጦርነቱን እንደ አዲስ ለመጀመር እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን የአማራ ክልል መንግሥት አስታውቋል::
በሌላ በኩል የአማራ ክልል በቀውስ ውስጥ ይገኛል:: ቀውሱ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት አስቀድሞ ለመከላከል በሚል ለሁለተኛ ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል:: ይህም ሆኖ ክልሉን ወደ አንጻራዊ ሰላም ከማሸጋገር ባለፈ ዘላቂ ሰላም ግን ማረጋገጥ አልቻለም:: በርካታ ንጹሀን ዜጎች አሁንም እየታገቱ እና እየተገደሉ መሆኑ ለዚህ ማሳያ ነው:: ይህም በአንድ ሕዝብ መካከል የሚደረግ ጦርነት የሚያስከፍለው ዋጋ ከፍተኛ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው::
ዓለም ዓቀፍ የሕግ ባለሙያው የርስ በርስ ጦርነት አሸናፊ እና ተሸናፊ የሌለበት ከጦርነት ዓይነቶች ሁሉ እጅግ በጣም አስከፊው መሆኑን አብነት በማንሳት አስረድተዋል:: አንድ ሕዝብ፣ ቋንቋ እና ሃይማኖት ባላቸው ሶማሊያ፣ ሊብያ፣ ኢራቅ እና ሶርያ የተከሰተውን አብነት ያነሳሉ:: በ1992 ዓ.ም የያኔው የዩጎዝላቪያ ፕሬዚዴንት ሚሎሸቪች “ችግሮቻችንን በሠለጠነ መንገድ እንፈታለን እንጂ እንደ አፍሪካውያን አንገዳደልም” ብሎ እንዳልነበር በአንጻራዊ ሰላም ለዘመናት አብሮ ይኖር የነበረው አንድ የዩጎዝላቪያ ሕዝብ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አንዳችም የጋራ ታሪክ እንዳልነበር ሆኖ እጅግ በጣም አሰቃቂ በሆነ መንገድ ተገዳደለ። ሀገሪቷም በሰባት ቦታ ተከፋፈለች። አንድ ሃይማኖት እና የጋራ ባህል ኖሮት፣ አንድ ቋንቋ እያወራ ለዘመናት እንደ አንድ ማኅበረሰብ የኖረው የሶማሌ ሕዝብም ከርስ በርስ ግጭት ለመዳን አለመቻሉን ለቀውሱ አሳሳቢነት ማሳያ አድርገው አንስተዋል::
ታዲያ ከዚህ አስከፊ ጦርነት እንዴት መውጣት ይቻላል? የሚለው ገዥ ይሆናል:: የሕግ ባለሙያው የርስ በርስ ጦርነት መጨረሻው ሁለንተናዊ ጥፋት መሆኑን በጽሑፋቸው አንስተዋል:: በመሆኑም ዛሬ በተደቀኑ ጊዜያዊ ችግሮች ላይ ብቻ ከማተኮር ከችግሮች እንዴት ወጥቶ ሰላማዊ ሁኔታን መፍጠር እንደሚቻል ማሰብ፣ ራስንም ለንግግር ዝግጁ ማድረግ እንደሚገባ መክረዋል:: በታሪክ ውስጥ የተፈጠሩ የታሪክ ስህተቶችን ፈልጎ ማግኘት ሌላው መፍትሄ መሆኑንም ጠቁመዋል:: “ተበድያለሁ!” የሚለውን ሕዝብ ስሞታ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ከማለፍ በአግባቡ በማዳመጥ ፈጣን እና ዘላቂ መፍትሄ መስጠት እንደሚገባም ጠቁመዋል::
መንግሥት በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን በተደጋጋሚ አስታውቋል:: ይሁን እንጂ እስካሁን ግጭቶችን በሰላም ለመቋጨት የተለየ እንቅስቃሴ አልተደረገም:: በመሆኑም መንግሥት ግጭቶች በሰላም እንዲቋጩ በተደጋጋሚ ከማስታወቅ ባለፈ በቁርጠኝነት ሊሠራ ይገባል:: በግጭት ውስጥ ያሉ አካላትም ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ልምድን በማዳበር እና በማስቀደም የርስ በርስ ጦርነት ከሚፈጥረው ሁለንተናዊ ጥፋት መውጣት ይገባል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም