የሰሜኑ ጦርነት እየተባለ የሚጠራው እና በትግራይ ኀይሎች እና በፌዴራል መንግሥቱ መካከል ይደረግ የነበረው ጦርነት ከወራት በኋላ የመኸር ወቅቱን ተከትሎ ጦርነቱ እንደ አዲስ አገረሸ። አድማሱንም ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች አሰፋ። ይህ ጦርነት በተለይ በአማራ ክልል ብቻ በሁሉም ዘርፍ ከ522 ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት ማድረሱን የክልሉ መንግሥት ይፋ አድርጓል::
ጦርነቱ በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት፣ በመሰረተ ልማት እና በሌሎች የሕዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ ዘርፈ ብዙ ውስብስብ ችግሮችን ፈጥሯል:: በተለይ በትምህርት ዘርፉ ላይ የደረሰው ጉዳት ግን የትውልድ ክፍተት እንዲፈጠር በማድረግ የሀገር የወደፊት እጣ ፈንታ አጣብቂኝ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል። በርካታ የትምህርት ተቋማት ፈጥነው ወደ መማር ማስተማር እንዳይገቡ ወድመዋል፤ የውስጥ ግብዓታቸው ተዘርፏል፤ እንዲሁም ለጉዳት ተዳርገዋል። እነዚህ ችግሮች እና ሌሎች የጸጥታ ስጋቶች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ለዓመታት ከትምህርት እንዲርቁ አድርጓቸዋል። ጦርነቱ በሰላም ከተቋጨ በኋላ ተቋርጦ የቆየውን መማር ማስተማር ለመመለስ ጥረት ቢደረግም በዘርፉ ላይ የደረሰው ጉዳት ትምህርትን በተሟላ ሁኔታ ለመስጠት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ባለመኖሩ የሚጠበቁ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዳልመጡ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥናቶች ያመላክታሉ።
“በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሚባለው ሆነና በአማራ ክልል ከ2015 ዓ.ም ሐምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ በክልሉ ታጥቀው በሚንቀሳቀሱ ኀይሎች እና በመንግሥት የጸጥታ አካላት መካከል የተፈጠረው ግጭት በ2016 ዓ.ም ወጥነት ያለው መማር ማስተማር እንዳይኖር አድርጓል። አሁንም ድረስ ወደ ትምህርት ቤት ያልመጡ ተማሪዎች መኖራቸው ለዚህ ማሳያ ነው።
በዘጠኝ ዞኖች፣ በ43 ወረዳዎች እና በ419 ቀበሌዎች የተከሰተው ድርቅም በርካታ ተማሪዎች በምግብ ፍላጎት አለመሟላት ምክንያት ከትምህርት እንዲርቁ፣ ያቋረጡትን ትምህርትም እንዳይቀጥሉ አስገድዷቸዋል። ድርቁ እና የሰላም እጦቱ የትውልድ ክፍተት እንዳይፈጥር ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ በተደጋጋሚ አስታውቋል። በጦርነት የወደሙ የትምህርት ተቋማትን በመልሶ ግንባታ ቀድሞ ከነበሩበት በተሻለ መንገድ መገንባት፣ በሰላም መናጋት ምክንያት የተቋረጠውን ትምህርት አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን በማረጋገጥ ወዲያው ማስጀመር እና በድርቅ ምክንያት ከትምህርት የራቁትን የትምህርት ቤት ምገባን ተግባራዊ በማድረግ ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ማድረግ የትኩረት ነጥቦች ሆነው እየተሠራባቸው ነው።
በክልሉ በተለይ ድርቅ በስፋት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ተግባራዊ የተደረገው የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም በርካታ ተማሪዎችን ከማቋረጥ እየታደገ መሆኑን ተማሪዎች እና የትምህርት ባለድርሻ አካላት እየገለጹ ነው።
ገብሬ ኪሮስ በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር አበርገሌ ወረዳ የማርነት አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ነው:: ገብሬ እንደሚለው በሁለተኛው መንፈቅ ዓመት የተማሪ ምገባ በትምህርት ቤቱ መጀመሩ እሱን ጨምሮ በርካታ ተማሪዎች በሰዓቱ በትምህርት ገበታቸው እንዲገኙ፣ ትምህርታቸውን በንቃት እንዲከታተሉ፣ ያቋረጡት እንዲመለሱ፣ አዘውትረው ትምህርት ቤት እንዲገኙ እና ትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ አስችሏቸዋል።
ምገባ ከመጀመሩ በፊት የነበረውን ሁኔታ ገብሬ ሲያስታውስ ትምህርት በሚሰጥበት ወቅት በክፍል ውስጥ ማንቀላፋት እንደነበር እና ጠዋት ወደ ትምህርት ቤት ቢሄዱም ረሀብ በሚሰማቸው ጊዜ ክፍለ ጊዜውን አቋርጠው ይወጡ እንደነበር ነው። ምገባ መጀመሩ ከተማሪዎች ባለፈ ቤተሰብም “ምን አብልቼ ልላካቸው፣ ምሳ ምን ላቆያቸው” ከሚለው ሐሳብ እንዲወጣ ያደረገ መሆኑን ገብሬ አክሎ ተናግሯል:: ድርቁን ምክንያት አድርጎ የተጀመረው የተማሪ ምገባ ከድርቁ እና ከሰላም እጦቱ ማክተም በኋላም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ገብሬ ጠይቋል::
በማርነት አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 1ሺህ 725 መደበኛ፣ 355 የቅድመ አንደኛ እና 20 የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መሆኑን የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር አለነ ገሠሠ በስልክ አስታውቀዋል:: ይሁን እንጂ ኢኮኖሚው በጦርነት እና ድርቅ በመጎዳቱ 200 ተማሪዎች ማቋረጣቸውን ተናግረዋል::
ትምህርት ቤቱ ሁሉንም የመዘገባቸውን ተማሪዎች ለማብቃት የተማሪ ምገባ እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል:: ምገባው ሲጀመር ከምገባ አዳራሽ ጀምሮ ምግብ የማዘጋጃ ቤት፣ የመመገቢያ ቁሳቁስ፣ የውኃ ማጠራቀሚያ ጄሪካን እና ሌሎችም ያልነበሩ በመሆኑ ትምህርት ቤቱ የአካባቢውን ነዋሪ በማስተባበር አሟልቶ መጀመሩን ተናግረዋል:: የምገባ ሥርዓቱ ተማሪዎች ተረጋግተው እንዲማሩ ትልቅ አበርክቶ መጫወቱንም ገልፀዋል::
የሰሜኑ ጦርነት ቀጥተኛ ሁለንተናዊ ጉዳት ካሳደረባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳድር ሥር የሚገኘው የአበርገሌ ወረዳ ነው። በብሄረሰብ አስተዳድሩ የሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ኀይል እና በባለፈው የክረምት ወቅት የተከሰተው የዝናብ እጥረት የፈጠረው ድርቅ ተማሪዎችን በሚፈለገው መጠን መዝግቦ ለማስተማር እክል መፍጠሩን የወረዳው ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገብረሀና ኪሮስ በስልክ ተናግረዋል።
እነዚህ ችግሮች ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዳይመጡ፣ በትምህርት ላይ የነበሩትም ትምህርታቸውን በንቃት እንዳይከታተሉ ከማድረግ ባሻገር እንዲያቋርጡ ይገደዱ እንደነበሩ ኃላፊዉ ገልጸዋል። ተማሪዎች ከትምህርት መራቃቸውም ያለ ዕድሜያቸው ተገደው ወደ ትዳር እንዲገቡ፣ ላልተገባ የጉልበት ብዝበዛ እንዲዳረጉ እና ላልተገባ ዓላማ መጠቀሚያ እንዲሆኑ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሁሉ ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ እና ሳያቋርጡ ትምህርታቸውን እንዲያስቀጥሉ የተማሪ ምገባ በመፍትሄነት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል። በወረዳው 38 አንደኛ እና መካከለኛ እንዲሁም ሦስት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚገኙ ያስታወቁት ኃላፊዉ፣ እስካሁን ከአንድ የአንደኛ ደረጃ እና ከሁለት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውጪ ሁሉም በማስተማር ሥራ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
እንደ ኃላፊዉ ማብራሪያ የተማሪ ምገባው ከሰባት ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ አድርጓል:: የክልሉ ትምህርት ቢሮ በመደበው በጀት የተጀመረው የምገባ መርሀ ግብር ተማሪዎች ተረጋግተው ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ እና በምግብ እጥረት የሚመጡ በሽታዎችን ቀድሞ ለመከላከል ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑንም ተናግረዋል::
የምገባ ፕሮግራሙ ከተጀመረ በኋላ በመሸኛ ወደ ሌሎች ትምህርት ቤቶች ይዘዋወሩ የነበሩ ተማሪዎች ቁጥር እና የማቋረጥ ምጣኔ መቀነስ እንዲሁም በረሀብ ምክንያት ትምህርት አቋርጠው ይወጡ የነበሩ ተማሪዎች በአሁኑ ወቅት ተረጋግተው እንዲማሩ ማስቻሉን አመላክተዋል:: የተማሪ ምገባ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ያነሱት ጽ/ቤት ኃላፊዉ፣ በቀጣይ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ባለሐብቶች እንዲሳተፉ ጠይቀዋል::
በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በ64 ትምህርት ቤቶች የተማሪ ምገባ እየተካሄደ መሆኑን የብሔረሰብ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ፍታለሽ ምህረቴ አስታውቀዋል። ከ38 ሺህ በላይ ተማሪዎች የምገባው ተጠቃሚ መሆናቸውንም ለአሚኮ ገልጸዋል።
ምገባ መጀመሩን ተከትሎ ትምህርታቸውን እያቆራረጡ ሲከታተሉ የነበሩ ተማሪዎች ቁጥርም መሻሻሉን አስታውቀዋል። ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ እና ሙሉ ጊዜያቸውን ንቁ ሆነው ትምህርታቸውን እንዲከታታሉ ማስቻሉንም ጠቁመዋል። ምገባ የሚካሄድባቸው ትምህርት ቤቶች ምገባ ከሌለባቸው ትምህርት ቤቶች የበለጠ ተማሪዎች እንዳሏቸውም ተናግረዋል::
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ እየሩስ መንግሥቱ የክልሉ መንግሥት በመደበው 75 ሚሊዮን ብር በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች የትምህርት ቤት ምገባ ሥርዓት እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል። ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ምገባ ሲጀመር አቋርጠው የነበሩ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት መመሰላቸውን፣ ምገባ ያለባቸው ትምህርት ቤቶች ከሌለባቸው የበለጠ ተማሪዎች እንዳሏቸው ተናግረዋል::
የምገባ ጉዳይ ለአንድ አካባቢ ብቻ ሳይሆን በሁሉም መጀመር እንዳለበት ያምናሉ:: በመሆኑም በዚህ ዓመት በክልሉ በ454 ትምህርት ቤቶች የተጀመረውን የተማሪዎች ምገባ በቀጣይ ዓመት በማስፋት አሁን ያለውን 224 ሺህ 563 የተመጋቢ ተማሪዎች ቁጥር ለማሳደግ ይሠራል ብለዋል።
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም