ከችግር በላይ ለመሆን

0
23

በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ 251 ሚሊዮን ሕጻናት የመማር መብታቸውን ተነጥቀዋል ሲል ያሳወቀው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ ያሳያል:: ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች ደግሞ ተማሪ እና መምህራን በትምህርት ተቋማት እንዳይገኙ ያደረጉ ምክንያቶች ናቸው ሲልም ይዘረዝራል:: የእርስ በርስ ግጭቶች፣ አስታራቂ ያጡ ጦርነቶች፣ ድርቅ፣ ጎርፍ፣ የመሬት መንሸራተት እና ሌሎች ተፈጥሯዊ ምክንያቶች ለተማሪዎች ከትምህርት መራቅ በመንስኤነት ይጠቀሳሉ::

ከዚህ ውስጥም 100 ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎች በአፍሪካ ይገኛሉ:: ግጭት፣ አለመረጋጋት፣ የትምህርት መሠረተ ልማት መጓደል፣ የትምህርት ጥራት ማነስ በአህጉሪቱ የትምህርት ሥርዓት ላይ ያንዣበበው ፈተና ቀዳሚ ምክንያቶች ናቸው::

በኢትዮጵያም ከሰባት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸውን የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል:: በአማራ ክልል ብቻ ባለፉት ሁለት ዓመታት ሰባት ሚሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት እንዲርቁ ሲደረግ በዚህ ዓመትም መዝግቦ ለማስተማር የታቀደውን ማሳካት እንኳ አልተቻለም:: የሰላም እጦት ደግሞ ቀዳሚው የዘርፉ ፈተና ነው::

እንደ ጦርነት የመሰሉ ማኅበራዊ አለመረጋጋቶች ሰዎችን ለጭንቀት እና ለድባቴ በመዳረግ ለሕይወታቸው ልዩ ትርጉም እንዳይሰጡ ይልቁንም ለተስፋ ቢስነት ተገዥ እንዲሆኑ ይደርጋቸዋል:: ለችግሮች መፍትሔ ከማፈላለግ ይልቅ ከጭንቀት ለመውጣት ሱስን ብቸኛ አማራጭ ያደርጋሉ:: ይህ ሱስ ደግሞ ነገ በሽታ እና ሕመም ሆኖ ሰዎች እንዳይንቀሳቀሱ አስሮ ያስቀምጣቸዋል::

ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ በሚሆኑበት ወቅት የሚያጋጥማቸው አዕምሯዊ መረበሽ እና የሐሳብ መበተን በሕይወታቸው ተስፋ ካደረጉበት ቦታ እንዳይደርሱ ያደርጋቸዋል:: የሰው ልጅ ስለ ነገ ኑሮው የሚያደርገው ተስፋ በዚህ ምክንያት ሲገታ አዕምሯቸው አሉታዊ ነገሮችን ያስተጋባል:: ይህም ለድብርት፣ ለጭንቀት እና ለተለያዩ ሱሶች ተገዥ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል:: በተለይ ችግሩ ከሁለት ሳምንት በላይ የሚዘልቅ ከሆነ የመኖር ጉጉት ማጣት እና ተስፋ ቢስነት ስሜት እየጎለበተ እንደሚሄድ የስነ ልቦና ባለሙያዎች ያስገነዝባሉ:: ስለ መኖር አለማሰብ፣ ራስን መውቀስ፣ ከሰው የመነጠል ስሜትም ያጋጥማል::

በሌላ በኩል ልጆች የደረሰባቸውን ችግር ተናግረው መፍትሔ ለማግኘት ሰው ላይጠይቁ ይችላሉ:: በዚህ ወቅት መምህራንን ጨምሮ የትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ ተማሪዎች ስሜታቸውን አውጥተው እስከሚናገሩ ከመጠበቅ ይልቅ አካላዊ ስሜታቸውን በዕይታ በማወቅ መርዳት እንደሚገባቸው የስነ ልቦና ባለሙያዎች ይመክራሉ::

ተማሪዎች ከጦርነት በኋላ ወደ ትምህርት በሚመለሱበት ወቅት ያሳለፉት የችግር ወቅት ከአዕምሯቸው ስለማይጠፋ ወጣ ያሉ ባህሪያትን ሊያሳዩ ይችላሉ:: የመረበሽ፣ በቀላሉ የመቆጣት፣ ብቸኛ መሆን፣ የትምህርት አፈጻጸማቸው መቀነ እና ወዘተርፈ በሥነ ልቦና ከተጎዱ ተማሪዎች የሚታዩ ያልተጠበቁ ውጤቶች ሊሆኑ ይችላሉ::

ከግጭት ወይም ጦርነት መልስ ተማሪዎች ለትምህርት ቤት ሕግና ደንብ ተገዥ ላይሆኑም እንደሚችሉ ሥነ ልቦናዊ ሐሳቦች ያስረዳሉ:: በዚህ ወቅት መምህራን እና የትምህርት አመራሩ ተማሪዎችን በጥፋተኝነት ከመፈረጅ ይልቅ አቅርቦ ሕመማቸውን መረዳት እንደሚገባ ባለሙያዎቹ ይመክራሉ:: እያንዳንዱ መምህራን የሥነ ልቦና ባለሙያ ሆኖ ተማሪዎች ከገቡበት ያልተገባ ባህርይ እንዲወጡ ማገዝም ግዴታ የሚሆንበት ጊዜ መኖሩን ማመን ይገባል ይላሉ::

ትምህርት ቤት ለተማሪዎች የዕውቀት መገንቢያ ብቻ ሳይሆን ከጥቃት መከላከያም ጭምር ነው:: ጓደኝነት ለመመሥረት፣ ከመምህሮቻቸው ጋር ለመገናኘት እና የዕለቱን ተግባራት በተሳካ ሁኔታ ለማጠናቀቅ በጎ ምኞት ይዘው ወደ ትምህርት ቤት ሊመጡ ይችላሉ::

የሕይወት ክህሎት ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚሠራው ‘ግሬተር ጉድ ማጋዚን’ መረጃዎችን መሠረት አድርጎ እንዳስታወቀው በአማካይ በእያንዳንዱ የመማሪያ ክፍል ውስጥ ቢያንስ አንድ የተለያዩ ጉዳቶች ደርሶበት ያለፈ (trauma) ተማሪ ይኖራል::

ተማሪዎች ተደራራቢ ችግሮችን አሳልፈው ወደ መደበኛ ሕይወታቸው ለመመለስ በሚሞክሩበት ወቅት ቀጣይነት ላለው ሀዘን፣ ተስፋ የመቁረጥ፣ የመገለል እና የቸልተኝነት ስሜት፣ ለማያቋርጥ ጭንቀት፣ ፍርሃት እና ለድብርት ይዳረጋሉ:: እነዚህም አሉታዊ አስተሳሰቦች በአዕምሮ የማሰብ አቅም ላይ ጫና በመፍጠር በወደፊት ሕይወት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ::

በትምህርት ላይ ያሉ ተማሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ መደገፍ ይገባል:: ወቅቱን መሠረት ያደረገ የመማር ማስተማር ሂደትን መከተል አንደኛው መንገድ መሆኑን የግሬተር ጉድ ጽሑፍ ያሳያል:: በጉዳት ላይ የተመሠረተ ትምህርት (trauma-informed learning) መስጠት ይመከራል:: መምህራን የተማሪዎችን ስነ ልቦና በመረዳት ወደ ፊት ብቻ ተስፋ እንዲያደርጉ መርዳት ይኖርባቸዋል:: ከተለመደው የመማር ማስተማር ስነ ዘዴ ወጣ ብሎ በሚያዝናና መንገድ ትምህርቱን መስጠትም እንደሚመከር ጽሑፉ አስፍሯል::

በክፍል ውስጥ ተማሪዎች መረጋጋት እንዲኖራቸው ማገዝ፣ ከሌሎች ጋር ያላቸውን ተግባቦት እንዲያሳድጉ መርዳት እና ትምህርታቸው ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያደርጉ የመምህራን እና የትምህርት ማኅበረሰቡ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጽሑፉ ጠቁሟል::

በተማሪዎች ላይ የደረሰ ስነ ልቦናዊ ጉዳትን በማከም ወደ መደበኛ ሕይወት ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ተማሪዎች በችግር ውስጥ ያለፉበትን መንገድ መረዳት ለውጤት ያበቃል:: ተማሪዎች በምን ውስጥ አልፈዋል? አቅማቸው ላይ ለመድረስ ምን ያስፈልጋቸዋል? የሚሉ ጥያቄዎች ተማሪዎችን ከችግር አውጥቶ ውጤታማ ለማድረግ አጋዥነታቸው ከፍተኛ ነው::

ጥንካሬዎቻችንን ለመገንባት ሁልጊዜ አንድ ነገር እስኪስተካከል ድረስ መጠበቅ አያስፈልገንም። በእርግጥም በችግር የተጎዳ ተማሪን ሥነ ልቦናዊ ጥንካሬ ለመመለስ እና ለማሳደግ ሥነ ልቦናዊ ችግሮቻቸውን መፈወስ ዋና አካል ይሆናል።

በችግር ውስጥ ያለፉ ተማሪዎች ማኅበራዊ ግንኙነታቸው እንዲጠናከር ማገዝም በትምህርት ውጤታማ እንዲሆኑ ትልቅ አቅም እንደሚሆን መረጃው ያሳያል:: በየትኛውም ቦታ ሁሉ ደኅንነት እንዲሰማቸው ማድረግ ለግንኙነት መጠናከር አበርክቶው ሰፊ ነው:: መተማመንን መገንባት ደግሞ ከትምህርት ማኅበረሰቡ የሚጠበቅ ዋና ሥራ መሆን እንዳለበት ተመላክቷል:: ትምህርቱ በሚሰጥበት ወቅት አዎንታዊ ምስሎችን እና ጥቅሶችን ማስቀመጥ፣ የፈጠራ አስተሳሰብን እና የቡድን ሥራን ማበረታታት ይመከራል::

በአጠቃላይ ተማሪዎች ከተስፋ መቁረጥ ወጥተው በተስፋ አሻግረው ወደሚመለከቱት መዳረሻ እንዲጓዙ የሚያደርጉ በጎ ነገሮችን እንዲያዳብሩ ከመምህራን፣ ከወላጆች እና በአጠቃላይ ከማኅበረሰቡ ይጠበቃል:: ሰዎች አንድ ቦታ ላይ የሚደርሱት ከዜሮ ሲጀምሩ በመሆኑ ጀምረን ያልጨረስነውን ከማየት ይልቅ ዳግም በጀመርነው ላይ ትኩረት በማድረግ የሕይወት ግብን ማሳካት ይገባል::

መረጃ

ለግደኛ – አላጋጭ፤

አሹዋፊ

ለዋሳ – አቅመ ቢስ፤ ደካማ

ለመገገ  – ጎፈነነ፤ ጎመዘዘ

ልግጫ  –  ፌዝ

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የሕዳር 22 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here