ከአመሳሰሉ አይቀር…

0
9

ጃፓናዊቷ ጠቢብ ኬይ ሜግሮ ጥላ እና ብርሃን በሚፈጥር የእርሳስ ቅብ የምትሰራቸው ስዕሎች ከጥቁር እና ነጭ ፎቶግራፍ የማይለዩ ወይም ልዩነቶችን ያጠበቡ መሆናቸውን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ከሳምንት በፊት ለንባብ አበቅቶታል፡፡

በዋና ከተማዋ ቶኪዮ የተወለደችው ኬይሜግሮ ገና በልጅነት እድሜዋ ስዕል መሳል እንደሚያስደስታት የተገነዘቡት ቤተሰቦችዋ የህይወት ጥሪዋን እንድትመረምር እና በተሰጥዓዋ እንድትገፋ ያበረታቷት ነበር፡፡

ውስጧን አዳምጣ ኬይ ሜግሮ በ2006 እ.አ.አ በኒውዮርክ በ”ፋይን አርት” ወይም የእይታ ጥበብ ትምህርት ቤት ገብታ በ2010 በ “ግራፊክ ዲዛይን” ዕውቀት ተክና ለመመረቅ በቅታለች፡፡

በ2012 እ.አ.አ በአሜሪካ የማስታወቂያ ስራ ድረጅት ውስጥ ተቀጥራም በግራፊክ ዲዛይነርነት ወይም በተመረቀችበት ሙያ ስትሰራ ቆይታ በ2016 አ.አአ ራሷን ችላ፣ በግሏ በስዕል ጠቢብነቷ ገፍታበታለች፡፡

ከሀሉም በላይ ኬይ ሜግሮ “የጨቅላ ስራ” ወይም “ቤቢ ወርክ” በሚል ርዕስ በእርሳስ የተሰሩ የወጣት ሴት ምስሎችን በግነተ ዕውነታ ስልት የሚያሳዩ ተከታታይ ስራዎቿ የላቀ ዕውቅና አሰጥቷታል፡፡ ወጣቷ የስዕል ውጤቶቿን በስፋት እውቅና ካላቸው አዶቤ፣ ኤች ቢኦ፣ ቲፋኒ እና መሰሎች ጋር በማህበራዊ ሚዲያ በትብብር ባቀረበቻቸው የጥበብ ውጤቶቿም ስኬታማ ሆናለች – ከተመልካች ባገኘችው ግብረመልስ፡፡

ኬይሜግሮ በጥበብ መስክ ባትሰማራ ኖሮ የእንስሳት አፍቃሪነችና ምናልባትም የእንስሳት ሐኪም   ልትሆን እንደምትችል ነው የተናገረችው፡፡

በመጨረሻም በቅርቡ በመገናኛ ብዙሃን ባደረገችው ቃለ ምልልስ ለስዕል ስራዎቿ መነሻ ምንጮች የግል ልምድ ወይም ገጠመኝ፣ ተፈጥሮ፣ የሰው ምስል፣ ስሜቶች እና ህልሞችን የምስሎችዋ ጭብጥ ወይም ዋነኛ ይዘት አድርጋ እንደምታንፀባርቅ ነው ያመላከተችው፡፡

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here