እንደ አብዛኛዎቹ ታዳጊ ሀገራት የኢኮኖሚያችን መሰረት ግብርና ነው፡፡ ይህንኑ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ የምንተገብርበት ብዙም ያልዘመነ ስልተ ምርት አሁን ድረስ ከበሬ ቀንበር ያልወረደ እና ኋላ ቀር መሆን ኢኮኖሚያችንን ከእ³ ወደ አፍ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
በዚህ የስልተ ምርት ኋላ ቀርነት ሳቢያ የምናገኘው አነስተኛ ገቢ እያስከተለ ያለው ድህነት ሳያንስ እየተፈጠሩ ያሉ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ ችግሮችም መጻኢ እጣ ፋንታችንን ስጋት ላይ እየጣሉት ናቸው፡፡
ያለፈው ዓመት የግብርና ምርት ዘመን በርካታ ችገሮች ተጋርጠውበት ማለፉ አይዘነጋም፡፡ የግብአት አቅርቦት እጥረት እና የዋጋ ግሽበት መከሰቱን ተከትሎ አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያን እንዲጠቀም ከፍተኛ ንቅናቄ ቢፈጠርም በዓመቱ ሊመረት ከሚገባው ምርት ውስጥ የ20 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ከመቀነስ አልታደገውም፡፡
ያ ያለፈው ዓመት የግብአት አቅርቦት እጥረት እና የዋጋ ግሽበት ለአሁኑ የ2016/17 የምርት ዘመንም ፈተና እንዳይሆን ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል፡፡ ስጋቱን ከፍተኛ የሚያደርገው ደግሞ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ በግጭትና እና በተፈጥሮ የአየር ንብረት መዛባት ሳቢያ በተከሰተው ድርቅ ዜጐች መቸገራቸው እና እንስሳት ማለቃቸው ነው፡፡
እነዚህን ስጋቶች ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ታዲያ የሚመለከታቸው የፌዴራል እና የክልል አካላት የግብርና ግብአቶችን በተገቢው ጊዜ፣ በበቂ መጠን እና በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ርብርብ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በእርግጥ የፌዴራሉ ግብርና ሚኒስቴር እና የክልሉ ግብርና ቢሮ ለዓመቱ በቂ የሚሆን የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ተፈጽሞ ወደ ሀገር ውስጥ እያገባ እና የደረሰውም እየተከፋፈለ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ይሁንና በክልሉ የተከሰተው ግጭት ለስርጭቱ አንቅፋት እንዳይሆን በሚያስችል መንገድ ለሰላም እና ውይይት ቅድሚያ በመስጠት እስካልተሰራ ድረስ የአምናው ችግር መፈጠሩ እንደማይቀር ሊሰመርበት ይገባል፡፡
ባለፈው ዓመት በአንድ ዞን ብቻ /ሰሜን ጐንደር/ ከ86 ሺህ በላይ እንስሳት አልቀው ከ173 ሺህ በላይ መኖ ወዳለበት እንዲሄዱ መደረጉን የተባበሩት መንግሥታት ለሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በጥር ወር ያወጣውን ሪፖርት ልብ ብሎ ከ80 በመቶ በላይ ነው የሚባለው የሀገራችን አርሶ አደር ምን ያህል አደጋ ውስጥ እንዳለ እና የእሱ መቸገር ለጠቅላላው ሕዝብ የሚያመጣውን ዳፋ በማሰብ የግለሰቦች፣ የመንግሥት እና የሁሉም የቤት ሥራ እና ግዴታ መሆን አለበት፡፡
(ስንቅነሽ አያሌው)
በኲር መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም