ከአቧራማዉ ኮረብታ እስከ ሳንቲያጎ በርናቤዉ

0
8

የእግር ኳስ ውበቱ በዘጠና ደቂቃ የሜዳ ላይ ፉክክር ብቻ  አይደለም። የእግር ኳስ እውነተኛ ጣዕም እና ምስጢር የሚወጣው ከሜዳ ውጪ በሚፈጠሩ የሰዎችን ልብ በሚነኩ አስገራሚ ታሪኮች ጭምር ነው። እግር ኳስ ከጨዋታነት አልፎ የህይወት ትምህርት ቤት፣ የተስፋ ቋት እና የህልም መፍቻ ቁልፍ መሆኑን የሚያረጋግጡ ክስተቶች አልፎ አልፎም ቢሆን ሲከሰቱ እንመለከታለን። ከሰሞኑ የዓለማችን ታላላቅ የስፖርት የመገናኛ አውታሮችን እና የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችን ትኩረት የሳበው እንደተለመደው የክርስቲያኖ ሮናልዶ ወይም የሊዮኔል ሜሲ ጉዳይ አይደለም።

የዓለም ዐይኖች ሁሉ ያረፉት በአንድ የ15 ዓመት ፔሩዋዊ ታዳጊ ላይ ነው። ስሙ ክሊቨር ሁዋማን ሳንቼዝ ይባላል። ከሳምንታት በፊት በደቡብ አሜሪካዊቷ ፔሩ ሊማ ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ አንድ አቧራማ ኮረብታ ላይ ሆኖ በሞባይል ስልኩ ጨዋታ ሲያስተላልፍ የነበረው ክሊቨር በዓለም ትልቁ የክለቦች መድረክ ላይ እንዲገኝ ተጋብዞ ታላቁን ጨዋታ በቀጥታ ጨዋታ አስተላላፊነት (በኮሜንታተርነት) ተሳትፏል።

ክሊቨር በጉጉት የሚጠበቀውን የሪያል ማድሪድ እና የማንችስተር ሲቲን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ በታሪካዊው ሳንቲያጎ በርናቤው ስታዲየም በአካል ዘግቦታል። የእግር ኳስ ጋዜጠኛ የመሆን የልጅነት ህልሙን ለማሳካት የከፈለው መስዋዕትነት ዛሬ የዓለምን ትኩረት ስቧል። “ይህ ድል ለእኔ ብቻ ሳይሆን እንደ እኔ ህልም ላላቸው ነገር ግን አቅም ላጠራቸው ልጆች ሁሉ ታላቅ ተስፋ ነው” ሲል ታዳጊው በደስታ እንባ ታጅቦ ስሜቱን ገልጿል።

ታዳጊው የሚኖረው ከፔሩ ዋና ከተማ ሊማ በጣም ርቃ በምትገኝ ገጠራማ ከተማ ውስጥ ነው። በውስጡ የሚብላላውን የእግር ኳስ ጋዜጠኛ የመሆን ጠንካራ ህልም ሰንቆ በፔሩ የተካሄደውን የኮፓ ሊበርታዶሬስ (የደቡብ አሜሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ) የፍጻሜ ጨዋታ የዘገበበት ክስተት የታዳጊውን ህይወት እስከወዲያኛው የቀየረበት አጋጣሚ ሆኖ አልፏል። ታሪኩ ከዚህ ይጀምራል፤ ከቤተሰቦቹ ጋር ሆኖ ጨዋታውን በቲቪ ከማየት ይልቅ በቦታው ተገኝቶ ድባቡን በማህበራዊ የትስስር ገጽ ለመተንፈስ ወሰነ። ለዚህም የ18 ሰዓታት አድካሚ እና አስልቺ ጉዞን በአውቶቡስ አደረገ።

እንዲህ ዓይነት ረጅም ጉዞ እንኳን ለ15 ዓመት ታዳጊ ለአዋቂም የሚከብድ መሆኑን ይህን ጽሁፍ የሚያነብ ሁሉ ያውቀዋል። ነገር ግን ዋና ከተማዋ ሊማ ሲደርስ የገጠመው እውነታ ከህልሙ ጋር የተራራቀ እና ልብን የሚሰብር ነበር። ከሰዓታት ጉዞ በኋላ ስታዲየሙ በር ላይ ሲደርስ ወደ ስታዲየም የሚያስገባ ትኬት አልነበረውም፤ የመግቢያ ዋጋውም ከአቅሙ በላይ ሆነበት። በዙሪያው ያሉ ሰዎች ደስ ብሏቸው ትኬታቸውን እያሳዩ ሲገቡ እሱ ግን ባዶ እጁን ቀረ።

ይሁን እንጂ “ተስፋ መቁረጥ” በክሊቨር መዝገበ ቃላት ውስጥ ቦታ አልነበረውም። ወደ ስታዲየሙ መግባት ባለመቻሉ ስታዲየሙን ከላይ ቁልቁል ማየት ወደሚቻልበት አንድ ኮረብታ ወጣ። አካባቢው የሚመች አይደለም፤ አቧራማ፣ ንፋስ የሚበዛበት እና ለመቀመጥ እንኳን አስቸጋሪ የሆነ የድንጋይ ስፍራ ነበር። በዚያ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ክሊቨር የራሱን “ስቱዲዮ” ፈጠረ። ስልኩን እንደ ዘመናዊ የቴሌቪዥን ካሜራ፣ ኮረብታውን እንደ ዘመናዊ ስቱዲዮ ተጠቅሞ ጨዋታውን ለቲክቶክ ተከታዮቹ በቀጥታ ማስተላለፍ ጀመረ።

በስልኩ ስክሪን ላይ የሚታየው ምስል የስታዲየሙን ርቀት የሚያሳይ ቢሆንም የድምፁ ጥራት እና የቃላት አወራወሩ ግን ልክ በስታዲየሙ ውስጥ ባለው የቪአይፒ ክፍል ተቀምጦ እንደሚያስተላልፍ ባለሙያ ነበር። እያንዳንዱን የተጫዋች እንቅስቃሴ የኳስ ቅብብል እና የደጋፊዎች ጩኸት በስሜት ይገልጽ ነበር። የቃላት አጠቃቀሙ፣ ስሜቱ እና ለሙያው ያለው ፍቅር በቪዲዮው ላይ በግልጽ ይታይ እንደነበር የያሆ ስፖርት መረጃ ያመለክታል። ይህ በኮረብታ ላይ በችግር እና በድህነት ውስጥ ሆኖ የተቀረጸ ቪዲዮ በሰዓታት ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ቀልብ ሳበ። የቲኪቶክ አልጎሪዝም ይህንን ቅንነት የተሞላበት ቪዲዮ ለዓለም አዳረሰው። ዓለምም በአድናቆት “በኮረብታ ላይ ሆኖ እንደ ባለሙያ በታላቅ በራስ መተማመን የሚዘግበው ይህ ድንቅ ልጅ ማነው?” በማለት መጠየቅ ጀመረች።

የቲክቶክ ቪዲዮው በአስደናቂ ፍጥነት ከተሰራጨ እና በሚሊዮኖች ከታየ በኋላ ነገሮች በብርሃን ፍጥነት ተቀያየሩ። የፔሩ እግር ኳስ ማህበረሰብ ለዚህ ታዳጊ ክብር ለመስጠት እና እውቅና ለመስጠት አልዘገየም። አንድ የሀገሪቱ የሊግ ክለብ እና የስፖርት ሚዲያ አካላት ክሊቨርን ፈልገው በማግኘት ታሪኩን ለመቀየር ወሰኑ። በኮረብታ ላይ በአቧራ ተሸፍኖ በስልክ ካሜራ ብቻ ሆኖ ሳይሆን በስታዲየም ውስጥ በክብር ተቀምጦ፣ ዘመናዊ የጆሮ ማዳመጫ አድርጎ እና ከፊት ለፊቱ ማይክሮፎን ተደቅኖለት አንድ የሊግ ጨዋታን በኮሜንታተርነት እንዲመራ ጋበዙት። ይህ ለክሊቨር የመጀመሪያው ፕሮፌሽናል የሆነ የስራ ልምድ ነበር።

ማይክሮፎኑን ሲይዝ በታዳጊነቱ እና በልምድ ማነስ ምክንያት እጁ ይንቀጠቀጥ ይሆናል፣ ድምፁ ይርገበገብ ይሆናል ተብሎ ተገምቶ ነበር። ነገር ግን የሆነው ተቃራኒው ነው። ክሊቨር ልክ ለዓመታት ልምድ እንዳለው አንጋፋ ጋዜጠኛ ወንበሩ ላይ ተመቻችቶ ተቀመጠ። ጨዋታው ሲጀመር ያሳየው መረጋጋት አስደናቂ ነበር። የጨዋታ ንባቡ (Game reading)፣ የታክቲክ ትንታኔው እና በተለይም ያ አስደናቂ ጉሮሮን የሚያንቀጠቅጥ የደቡብ አሜሪካውያን “ጎልልልል” የሚል ድምፁ የፔሩን ሕዝብ አስደመመ። በስርጭቱ ወቅት አብረውት የነበሩት አንጋፋ ጋዜጠኞች ሳይቀሩ በአድናቆት ሲመለከቱት ነበር። “ይህ ልጅ የተወለደው ለዚህ ሙያ ነው፤ ድህነት እና የቦታ ርቀት እንጂ ተሰጥኦ አላነሰውም” የሚለው አስተያየትም ከየአቅጣጫው እንደ ጎርፍ ይፈስ ጀመር።

የክሊቨር ዝና እና ታሪክ ውቅያኖስ ተሻግሮ አውሮፓ በተለይም የስፔኑ ማድሪድ ከተማ ደረሰ። የዓለም የክለቦች ንጉሥ የሆነው ሪያል ማድሪድ እና የእንግሊዙ ኃያል ማንችስተር ሲቲ በሚያደርጉት የሞት ሽረት የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ላይ ክሊቨር በልዩ ሁኔታ እንደ ክቡር እንግዳ ተጋብዞ እንዲገኝ ተወሰነ። ይህ ግብዣ ተራ ግብዣ አልነበረም፤ በዓለም ላይ ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የእግር ኳስ አፍቃሪያን ለማግኘት የሚመኙት ነገር ግን ጥቂቶች ብቻ ያሳኩት እድል ነው። ጨዋታው የዘመናችን ትልቁ የእግር ኳስ ጦርነት ተደርጎ የሚወሰድ ሲሆን ቪኒሺየስ ጁኒየር፣ ጁድ ቤሊንጋም እና ኤርሊንግ ሃላንድ የመሳሰሉ የዓለም ኮከቦች እርስ በርስ የሚፋለሙበት መድረክ ነው።

ክሊቨር ከሳምንታት በፊት በቲቪ ወይም በስልኩ ስክሪን ብቻ ይመለከታቸው የነበሩትን እነዚህን ኮከቦች አሁን በቅርበት ተመለከታቸው፤ በተዘጋጀለት ምቹ ቦታም ሆኖ ታዘባቸው፤ በእጁም ጨበጣቸው። የሳንቲያጎ በርናቤው አለቃ ፍሎረንቲኖ ፔሬዝም ለዚህ ታዳጊ ጋዜጠኛ የተመቻቸ ቦታ እና አስፈላጊውን የሙያ ፈቃድ (Accreditation) መስጠታቸው ታዳጊው በነፃነት እንዲንቀሳቀስ አስችሎታል።

ይህ የክሊቨር ታሪክ ስለ አንድ ግለሰብ ብቻ የሚወራ ጉዳይ ብቻ አይደለም። ይልቁንም ስለ እግር ኳስ መንፈስ (Spirit of Football) እና ስለ ሰው ልጅ የላቀ ተስፋ የሚናገር ትልቅ የህይወት ፍልስፍና ጭምር እንጂ። ብዙ ጊዜ በዓለማችን “ገንዘብ ከሌለህ ህልምህን ማሳካት አትችልም” “ያለ ትምህርት እና ያለ ድጋፍ የትም መድረስ አይቻልም” የሚሉ ተስፋ አስቆራጭ አስተሳሰቦች ይንፀባረቃሉ። ክሊቨር ግን ይህንን የተሳሳተ አስተሳሰብ በ18 ሰዓት ጉዞ እና በአንድ አቧራማ  ኮረብታ ላይ በመቆም ሰብሮታል። እግር ኳስ የሀብታሞች መጫወቻ ወይም የባለፀጎች መዝናኛ ብቻ ሳይሆን ህልም ፣ ተስፋ ለሰነቁ እና ጥልቅ ፍላጎት ላላቸው ሁሉ ክፍት የሆነ መድረክ መሆኑን በተግባር አረጋግጧል ሲል የሪል ቶታል ኒውስ መረጃ አመልክቷል።

ጥልቅ ስሜት (Passion) ከዘመናዊ ካሜራ፣ ከውድ ስቱዲዮ እና ከትልቅ የቴሌቪዥን ጣቢያ በላይ ኃይል እንዳለው የክሊቨር ድምፅ ሕያው ምስክር ነው። እውነተኛ ተሰጥኦ ቦታ፣ ጊዜ እና ሁኔታ እንደማይገድበው እንደ ወርቅ በአቧራ ውስጥም ቢሆን እንደሚያበራ አሳይቷል።  የክሊቨር ስኬት የቴክኖሎጂ እና የማህበራዊ ሚዲያ በጎ ጎን ማሳያም ተደርጎ ተወስዷል። አንድ ታዳጊ ከፔሩ ኮረብታ ላይ  በርቀት የሠራው ሥራ በቅጽበት ዓለምን አዳርሶ፣ ድንበር እና አህጉር አቋርጦ ህይወቱን መቀየር ችሏል።

ይህ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ሆነው ህልማቸውን ለሚከተሉ ታዳጊዎች “ተሰጥኦ ካለህ እና ያለማቋረጥ ጥረት ካደረክ ዓለም በሆነ መንገድ ታገኝሃለች” የሚል ታላቅ ተስፋን የሚሰጥ መልእክት ያስተላልፋል። ታዳጊው በቅርቡ በሰጠው ቃለ መጠይቅ ላይ “ትናንት በኮረብታ ላይ ነበርኩ፤ ዛሬ በበርናቤው አለሁ ነገን ደግሞ አብረን እናያለን። እግር ኳስ ህይወቴ ነው! ህልማችሁን አትተው! በሩ ሲዘጋባችሁ መስኮቱን ስበሩ” ሲል ረዥሙን ጉዞ ገና መጀመሩን ተናግሯል።

በሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ላይ ክሊቨር ሁዋማን ሳንቼዝ በበርናቤው ስታዲየም ሲገኝ ከእሱ ጋር አብሮ የተገኘው የፔሩ ሕዝብ መንፈስ ብቻ አይደለም። በዓለም ዙሪያ ያሉ በድህነት ውስጥ ሆነው ትልቅ ህልም የሚያልሙ በገጠራማ ስፍራዎች ሆነው ኳስ የሚጫወቱ እና እድል የሚጠብቁ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህልመኛ ታዳጊዎች መንፈስም ከእሱ ጋር አብሮ በሳንቲያጎ በርናቤው ይገኛል። ጨዋታው በማንችስተር ሲቲ አሸናፊነት ተጠናቋል። ነገር ግን የዚህ ታሪክ ትክክለኛው አሸናፊ ገና ጨዋታው ሳይጀመር ነበር የታወቀው። እሱም ተስፋ ያልቆረጠው በአቧራማ ኮረብታ ላይ ሆኖ ህልሙን የጠራው የ15 ዓመቱ ክሊቨር ነው። ማድሪድ ለዚህ ወጣት እጆቿን ዘርግታ ስትቀበል የተቀበለቸው አንድን ድንቅ ታዳጊ ብቻ ሳይሆን የማይበገረውን የሰው ልጅ የጥረት ውጤትን ጭምር መሆኑን ያሆ ሰፖርት አስነብቧል።

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የታህሣስ  6  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here