ከአንድ ጀግና ራዕይ ወደ ሕዝባዊ ማዕበል

0
36

በየዓመቱ ህዳር ወር ላይ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ለየት ያለ ትዕይንት ያስተናግዳሉ:: በቀለማት ያሸበረቁ መለያ የለበሱ በሺዎች የሚቆጠሩ የተለያየ ዕድሜ እና ፆታ ያላቸው ሰዎች በአንድ ምት ይሮጣሉ፤ ይተማሉ:: ይህ የደስታ፣ የውድድር እና የአንድነት መንፈስ የሚንጸባረቅበት መድረክ ነው-ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ:: ከስፖርት ውድድር የዘለለ ትርጉም ያለው ይህ ሁነት የኢትዮጵያውያን የሩጫ ፍቅር፣ የማይበገር መንፈስ እና ሀገሪቱ የምትገለጽበት ትልቅ ሕዝባዊ መድረክ ነው::

በዚህ ዓመት ደግሞ ድምቀቱ ይለያል:: ውድድሩ 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓሉን አክብሯል:: “ሶፊ ማልት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ” በሚል ስያሜ  እሁድ ህዳር 14 ቀን 2018 ዓ.ም ተካሂዷል::

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ታሪክ ከኢትዮጵያ የምንጊዜም ጀግና ከሆነው ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ስም ጋር የተቆራኘ ነው:: እ.ኤ.አ በፈረንጆች ሚሊኒየም በሲድኒ ኦሊምፒክ  ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ስላሴ በዐስር ሺህ ሜትር ርቀት ሁለተኛ ደረጃን ይዞ መጨረሱ አይዘነጋም:: ታዲያ ስመ ጥሩ አትሌት ወደ ሀገሩ ሲመለስ የብር ሜዳሊያ ብቻ ሳይሆን በልቡ ውስጥ ሌላ ትልቅ ራዕዩን ይዞ ነበር የተመለሰው:: ከሲድኒ ኦሎምፒክ በኋላ በእንግሊዝ በተካሄደው “የታላቁ የሰሜን ሩጫ” (Great North Run) ላይ እንዲሳተፍ የቀረበለት ግብዣ ራዕዩን ለማሳካት  በር ከፍቶለታል::

እናም የጎዳና ላይ ሩጫ በሀገሩ ኢትዮጵያ የማዘጋጀት ፍላጎት እንዳለው ለታላቁ ሰሜን ሩጫ አዘጋጆች ገለጸ:: በዚህ መንገድ ነው በአፍሪካ ትልቁ  የጎዳና ላይ ሩጫ ሊወለድ የቻለው:: የኃይሌ ዓላማ ሩጫን በኢትዮጵያ ከስታዲየም ውድድርነት አውጥቶ የሕዝብ የዕለት ተዕለት ባህል እና የጤናማ ህይወት ዘይቤ አካል ማድረግ ነበር::

ታዲያ የመጀመሪያው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር ህዳር 16 ቀን 1994 ዓ.ም ነበር የተካሄደው:: ይህም በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የተከፈተበት ክስተት ነበር:: በሀገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ዐስር ሺህ ሰዎች የዋና ከተማዋን ጎዳናዎች አጥለቅልቀው በአንድነት የሮጡበት ዕለት ነበር- ቀኑ:: የመጀመሪያውን ውድድርም የሃሳቡ ጠንሳሽ እና  መስራች አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ አሸናፊ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ::

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ስኬት የሚለካው በተሳታፊዎቹ ቁጥር እድገት እንደሆነ ኢትዮጵያ ራን ዶት ኦርግ መረጃ ያስነብበናል:: በመጀመሪያው ውድድር ዐስር ሺህ የነበረው የተሳታፊ ቁጥር በአምስት ዓመታት ውስጥ ብቻ ከእጥፍ በላይ በማደግ በ1999 ዓ.ም ወደ 25 ሺህ ደርሷል:: በ2011 ዓ.ም ደግሞ 40 ሺህ የሚጠጉ ተሳታፊዎችን አፍርቷል::

25ኛው የብር ኢዮቤልዩ በዓል በተከበረበት  በዚህ ዓመት ደግሞ አዲስ ክብረውሰን ተመዝግቧል:: በዘንድሮው ውድድር 55 ሺህ ተሳታፊዎች በዐስር ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር ተሳትፈዋል:: ይህም ትልቁ የጎዳና ላይ ሩጫ መሆኑን በድጋሚ አረጋግጧል:: እንዲሁም በዓለም ላይ ካሉ ግዙፍ ሕዝባዊ ሩጫዎች ተርታ እንዲሰለፍ አስችሎታል::

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ተልዕኮ የሩጫ ውድድር ማዘጋጀት ብቻ አይደለም:: ውድድሩ ገና በዓለም መድረክ ላይ ያልታዩ ተስፋ ሰጪ ወጣት አትሌቶች ብቃታቸውን እንዲያሳዩ እና በአትሌቲክሱ ዓለም እንዲታወቁ እድል መፍጠር ጭምር እንጂ:: የበጎ አድራጎት እና የማህበረሰብ ንቅናቄ መፍጠርም ሌላኛው የውድድሩ ዓላማ ነው:: ህብረተሰቡን ያስተምራል፤ ገንዘብ በማሰባሰብም ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች ድጋፍም ያደርጋል::

በዚህ ዓመት ብቻ ከአራት ሚሊየን ብር በላይ ለበጎ አድራጎት ሥራዎች ይውላል:: ገንዘቡም ለቼሻየር ኢትዮጵያ፣ ለተስፋ ማህበራዊ እና ልማት ማህበር እንዲሁም ለኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ድጋፍ ይደረጋል:: ውድድሩ ከስፖርታዊ ይዘቱ ባሻገር የቱሪዝም መስህብ እየሆነ መጥቷል:: በዘንድሮው ሩጫ ላይ ብቻ ከ400 በላይ ተሳታፊዎች ከተለያዩ የዓለም ሀገራት መምጣታቸው ተረጋግጧል:: ይህ ታዲያ ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል:: ሀገራችንንም ለዓለም ለማስተዋወቅ ያግዛል::

በዘንድሮው ውድድር ላይ በአካል መገኘት ለማይችሉ ዓለም አቀፍ የሩጫው ወዳጆችም መፍትሄ ተዘጋጅቶ ተመልክተናል:: በ16 የተለያዩ የዓለማችን ከተሞች የሚገኙ ተሳታፊዎች በያሉበት ሆነው በቨርቹዋል ቴክኖሎጂ አማካኝነት የሩጫው አካል ሆነዋል::

የብር ኢዮቤልዩ በዓሉን ለማድመቅ በአትሌቲክሱ ዓለም ስማቸው ገዝፎ የሚነሳው ጀግኖች በአዲስ አበባ በክብር እንግድነት ተገኝተዋል:: ኬኒያዊያኑ የረጅም ርቀት ንጉሡ ፖል ቴርጋት፣ ዳንኤል ኮመን እና ሞሰስ ታኑይ፣ የማራቶን ንግሥቷ ፔሬስ ቺፕቺርቺር እንዲሁም አሜሪካዊው የማራቶን ሯጭ ካሊድ ካኑቺ በውድድሩ ላይ ተገኝተዋል::

ከሕዝባዊ ሩጫው ጎን ለጎን 500 ፕሮፌሽናል አትሌቶች ለዋንጫው እና ለገንዘብ ሽልማት ተፎካክረዋል:: በዚህ ልምድ ባላቸው አትሌቶች የሚደረገው ውድድር በየዓመቱ ከፍተኛ ፉክክር የሚደረግበት ሲሆን አዳዲስ ኮከቦችንም ለዓለም ያስተዋውቃል:: ዘንድሮም ለሽልማት የተዘጋጀው ገንዘብ የውድድሩን ደረጃ እና ጥራት እንደሚያሳይ የዓለም አትሌቲክስ መረጃ ያስነብባል::

ከዋናው ውድድር አንድ ቀን ቀደም ብሎ ቅዳሜ ህዳር 13 ቀን 2018 ዓ.ም ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር የህፃናት ውድድር ተካሂዷል:: ይህም ታላቁ ሩጫ ተተኪዎችን ስለማፍራት ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳያል ተብሏል:: በወጣቶች ስፖርት አካዳሚ በተከናወነው በዚህ ውድድር ላይ አራት ሺህ ህፃናት ተወዳድረዋል::

55 ሺህ ተሳታፊዎች በሁለት ዋና ዋና ምድቦች ተከፍለው ነው ውድድሩን ያከናወኑት:: “ዘና” እና “ፈጣን” ማዕበል በሚል:: “ፈጣን” ማዕበል ምድብ የዐስር ኪሎ ሜትሩን ርቀት ከአንድ ሰዓት በታች ለመጨረስ ዓላማ ያላቸውን ልምድ ያላቸው ሯጮችን ያካተተ ነበር:: “ዘና” ማዕበል ውድድሩን ለመዝናናት፣ ጤናቸውን ለመጠበቅ እና የማህበራዊ ትስስር ለመፍጠር የሚሮጡትን ያጠቃልላል::

በውድድሩ ቀን 50 ዶክተሮችን ጨምሮ በርካታ የህክምና ባለሙያዎች በ22 የህክምና ጣቢያዎች ላይ በመገኘት ፈጣን አገልግሎት ሰጥተዋል:: አንድ ሺህ በጎ ፈቃደኞች ተሳታፊዎችን በማስተባበር፣ ውሃ በማቅረብ እና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ ውድድሩ እንዲደምቅ አስችለዋል:: ውድድሩን ከሁለት ሰዓት ከ30 ደቂቃ በታች ያጠናቀቁ ተሳታፊዎች በሙሉ የሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል::

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በአንድ አትሌት ራዕይ ተጀምሮ ዛሬ የሀገር ኩራት የሆነ ታላቅ የስፖርት ሁነት ለመሆን በቅቷል:: ከስፖርታዊ ውድድርነቱ ባለፈ ኢትዮጵያን ለዓለም በማሳየት፣ ወጣት አትሌቶችን በማፍራት እና የህብረተሰቡን የአንድነት መንፈስ በማጠናከር ረገድ ጉልህ ሚና ተጫውቷል፤ እየተጫወተም ይገኛል:: የዘንድሮው 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓል ያለፉት ስኬቶች የታወሱበት እና ለወደፊቱ ደግሞ የበለጠ ታላቅ የመሆን  ራዕይ የተሰነቀበት ሆኖ ተጠናቋል::

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የህዳር 15 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here