ከአውደ ባሕል እስከ ባሕል እና ኪን

0
140

በኲር ጋዜጣ ታህሣሥ 7/1987  ዓ.ም የክልል ቀዳሚዋ ጋዜጣ ወይም የሕትመት ውጤት ሆና መውጣት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ከነበሯት የተለያዩ አምዶች ውስጥ በወቅቱ አውደ ባሕል ይባል የነበረው ከቀዳሚዎቹ ውስጥ አንዱ ነው::

በኲር የካቲት 3/1987  ዓ.ም ለንባብ ካበቃችው የአውደ ባሕል አምዷ ጀምሮ እስከ 1989 ዓ.ም ድረስ ከክልሉ ቱባ ባሕሎች ውስጥ የተወሰኑትን ለአንባቢዎች አድርሳለች::

በኲር ጋዜጣ በወቅቱ የክልሉ ብቸኛ ልሳን ከመሆኗ ጋር ተያይዞ በርካታ ግብረ መልሶች የሚደርሷት እና በርካታ ጸሐፍትም የሚሳተፉባት የመገናኛ አውታር ነበረች::

ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ ወደ አንባቢዎች ይደርሱ ከነበሩትና ሳይቋረጡ አሁን እስካለንበት 2017 ዓ.ም ድረስ ከዘለቁት አምዶች ውስጥ  በሂደት የተለያዩ ስያሜዎች እየተሰጡት የዘለቀው የባሕል አምድ ተጠቃሽ ነው::

ከ1987 እስከ 1989 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ በአውደ ባሕል አምዶች ሱስኒዮስ እና ደብረ መዊዕ፣ ዞዝ አምባ ጊዮርጊስ፣ አጼ ፋሲል እና የጎጃሙ ቤተ መንግሥታቸው፣ ዙር አምባ፣ አባ ጥላዬ እና ብሂሎቻቸው፣ ዳባት እና አያሌው ብሩ፣ የጎጃሙ ሶደሬ (የአቮላ ተራራ)፣ የደሴዎቹ የፈውስ ብልሃተኞች፣ ብሶትን በሙሾ፣ ቁስቋም እና እቴጌ ምንትዋብ፣ ዝናብ የማያስገባው የጣራ መስኮት (ስቁረት)፣ አባይ ያልተፈታው እንቆቅልሽ፣ የዘመን መቁጠሪያችን እና አዲስ ዓመት፣ ነብይ በሀገሩ እና በዘመኑ፣ ሮሃ ላሊበላ፣ ላኮመልዛ የሀገር ቤዛ፣ በዓለ ጥምቀት በዓለ መጸለት፣ ሥነ ቃል በውበት ገላጭነት የሚሉ እና ሌሎችም ከክልሉ ባሕል ጋር ተወራራሽ የሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች ተከትበዋል::

ጌታቸው ፈንቴ፣ ታቦር ገብረ መድኅን፣ ሆሳዕና ተስፋሁን (ከሰሜን ጎንደር ባሕል እና ስፖርት መምሪያ)፣ ማሩ ደስታ፣ ዣክ ሲራክ፣ጀማል መሐመድ፣ መምህር ትዕዛዙ እንግዳ (ከደሴ)፣ ዕልልታ አሜን፣ ዘውዱ ሞኝነቴ፣ አበረ አዳሙ፣ አባትሁን ዘገየ፣ ተስፋዬ ደምሴ እና ሌሎች ደግሞ በአውደ ባሕል አምድ ላይ ጽሑፋቸውን ያሰፈሩ ጋዜጠኞች እና ተሳታፊዎች ናቸው::

ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት የበኲር አውደ ባሕል እትሞች ላይ ደግሞ የአምዱ አዘጋጅ አበረ አዳሙ ነበር:: በዚሁ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ በአውደ ባሕል አምድ አወይቱ ፍል ውኃ ለመንፈስ ፍስሃ፣ የረመዳን ወር እና ትሩፋቱ፣ የክርስቶስ ሰምራ ገዳም ጥያቄ ምላሽ ያገኝ ይሆን? የሚሉና ሌሎች በርካታ ባሕል ነክ ጉዳዮች በጋዜጣዋና በአምዱ ቦታ አግኝተዋል::

መልኬ ከበደ፣ አንዳርጋቸው ታምር፣ አንዱዓለም አባተ፣ ሰኢድ አሊ (ከመንጎል ሥነ ጽሑፍ ክበብ-ደሴ)፣ ጌታቸው ተስፋ፣ ጎራው ሳልለው፣ ወንድሜነህ ደሳለኝ፣ ተዋነይ ዘጎንጅ፣ ፀሐዬ መሰለ፣ ጥላሁን ወንዴ፣ ካሣ ርጥብነህ፣ ወርቁ ዓለሙ፣ ምንይችል እንግዳ እና ሌሎችም በአምዱ ላይ የተሳተፉ ባለውለታዎች ናቸው::

በበኲር ጋዜጣ ላይ የሚስተናገደውን አውደ ባሕል አምድ በ1993 መነጽር ስናየው ደግሞ በአምዱ አናት ላይ “አምዱ የክልሉ ሕዝብ ባሕል ወግ እና ልምድ የሚጠበቅበትን፣ የሚስፋፋበትንና የሚዳብርበትን፣ ጎጂ ልምዶች የሚወገዱበትን፣ ቅርሶች ተጠብቀው ለኢኮኖሚ አጋዥ ኃይል የሚሆኑበትንና የፈጠራ ባሕል የሚዳብርበትን መንገድ ይጠቁማል” ተብሎ ተጽፎለታል::

በዚህ ወቅት የአምዱ አዘጋጅ ታምራት ሲሳይ ነበር:: በአምዱ ላይ ሴዲት ኤልሻዳይ፣ ዘውዱ ሞኝነቴ፣ ይገርማል አማረ፣ መልኬ ከበደ፣ ጌታቸው ፈንቴ፣ ከደብረ ብርሃን ጸዳል አማተር የጋዜጠኞች ክበብ እና ሌሎችም ተሳታፊዎች የብዕር ትሩፋታቸውን አሳርፈዋል::

በኲር ጋዜጣን እና የባሕል አምዷን እየቃኘን ያለነው በወፍ በረር መሆኑን የትዝታችን አንባቢዎች እንድትገነዘቡልን አደራ እንላለን:: በዚሁ ወደ 1997 ዓ.ም ስንሻገር ደግሞ አቆልቋይ፣ ዋንዛዬ፣ የምንጃር ጨዋታ፣ የአርሶ አደሩ ቃሎች፣ ትስኪ ፏፏቴ፣ መግደርደር በጎንደር፣ ቅጥ ያጣ ፍርሃት፣  በየዳ የጥንቱ ባሕል አምባ እና ሌሎችም አምዱን የሚመጥኑ ባሕላዊ ጽሑፎች ለንባብ በቅተዋል::

ፋንታዬ ዘገዬ፣ መኩሪያው ዳኘው፣ አብዮት ኩምሳ፣ መዝሙር ሃዋዝ፣ ሕይወት ጥበቡ፣ ነጋ ገላዬ፣ ጌታቸው ፈንቴ፣ ስለሺ አምባው፣ ዳሪክ መልካየሁ፣ ቲቲ፣  ወለጋ ተስፋዬ፣ ዕዝራ ዘወርቅ አብዶ እና ፀሐዬ መሰለ በአምዱ ላይ ከተሳተፉት ውስጥ ጥቂቶቹ  ናቸው::

አሁንም በወፍ በረር የምናስቃኛችሁን የበኲር 30ኛ ዓመት የባሕል አምድ በትዝታ ለማስቃኘት 2001 ዓ.ም ላይ ደርሰናል:: በ2001 የበኲር ጋዜጣ አውደ ባሕል አምድ ላይ የሻደይ ባሕላዊ ጨዋታ (ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ) በተሳታፊ የተከተበ፣ ዘወልድ የወንዝ አባት፣ አስተርዮ፣ “ሸህ ለጋ” ውጤታማው ሽምግልና፣ መላ የሚያሻቸው ሕገ ወጥ አስጎብኚዎች፣ ጓሳ ልብስም ጉርስም፣ ትኩረት የሚሹ የመስህብ ቦታዎች፣ አንኮበር እና ሌሎችም የክልሉ ባሕላዊ ትውፊቶች በጋዜጣዋ ቦታ ተሰጥቷቸዋል::

አዱኛሽ አክሊሉ፣ ተሾመ ሽፈራው፣ ሙሉጌታ ባዬ፣ ዑመር መሐመድ፣ ኬስ ሴራ ሴራ፣ ፋንታዬ ዘገየ፣ ሰላም ይሁን ዓለም፣ አሻግሬ ቱፋ፣ እሱባለው ካሣ፣ ታምሩ ታደሰ፣ ሸጋው ሙሉማር፣ ጥላሁን ወንዴ፣ ሰለሞን አጉኔ፣ ሞገስ አመራ፣ ዘማቹ አዳሙ፣ ኤሊያስ ሙላት፣ ቢኒያም ተዘራ፣ አለሚቱ የኔት፣ ሃይማኖት ተስፋዬ እና ሌሎችም የተቋሙ ጋዜጠኞች እንዲሁም ተሳታፊዎች በጋዜጣዋ ሁለንተናዊ እድገት ላይ የራሳቸውን ሚና ተወጥተዋል::

ወደ 2007 ዓ.ም ስንሻገር ደግሞ አምዱ ኪን በሚል ስያሜ ተቀይሯል:: በዚሁ ዓመት ከየካቲት ወር ጀምሮ ደግሞ አምዱ ጥበብ በሚል እና ኪን/ባሕል ተብሎ የክልሉን ባሕላዊ ጉዳዮች ሲያስተናግድ ቆይቷል:: ሰው ፍለጋ፣ የመንገድ ላይ ወሬ፣ የቅኝት ጨዋታ፣ ከባሕር ዳር እስከ ገዳሪፍ፣ ተዓምረኛው ሐይቅ፣ የትንሳኤ በዓል እና ዓለም አቀፋዊ ገጽታው፣ የጥበብ ምሽት እና ሌሎችም የብዕር አሻራዎች ትላንትን ከዛሬ በሚያቀራርቡ እንዲሁም የክልሉን ባሕል በጉልህ በማስተዋወቅ አዎንታዊ ሚናቸው ተንጸባርቋል::

አባትሁን ዘገየ፣ ስንቅነሽ አያሌው፣ ጸጋዬ የሺዋስ፣ ደምሳቸው ፈንታ፣ ኦዝያን፣ አብርሃም ገብሬ፣ ምትኬ ቶሌራ፣ አስማማው በቀለ፣ ደረጀ አምባው፣ ሱራፌል ስንታየሁ፣ ዋለልኝ አየለ፣ አብዮት ዓለም፣ የሺሃሳብ አበራ እና ሌሎችም የአምዱ ድምቀት ሆነው ዘልቀዋል::

በ2011 ዓ.ም አምዱ ልቦለድ/ወግ የሚል ስያሜ ተሰጥቶት የሚጻፉበትም አጫጭር ልቦለዶች እና ወጎች ሆነዋል:: በዚህ ወቅት የአምዱ ጽሑፎች በካርቱኒስት ሰርጸ ድንግል የካርቱን ሥዕሎች የተደገፉ ናቸው::  ፋሲካን በጥይት፣ የጡረታ ደሞዝ፣ የቀብሬ ማስታወሻ፣ የተቃርኖ ዓለም፣ የተራበው ሚዛን፣ እብድ እሁድ፣ መልስ አልባው፣ የተራበው መብራት፣ ያልተማረው፣ ሁሉ አማረሽ፣ እምባ ጓል አስመረዊቲ፣ የምጽዓት ቀን ዘጋቢው፣ መርዝ የተቀባው ሰይፍ፣ ወፍራም ደም እና መሰል ጽሑፎች በተቡ ብዕሮች ተከትበዋል::

አብዮት ዓለም፣ እርሳሱ በላይ፣ የኔሰው ማሩ፣ እመቤት አህመድ፣ ሀብታሙ አዱኛ፣ አባትሁን ዘገየ፣ ሱራፌል ስንታየሁ፣ ታደሰ ጸጋ፣ ጌታቸው ፈንቴ፣ እሱባለው ይርጋ፣ እያዩ መለሰ እና ሌሎችም ተሳትፎ አድርገዋል::

በ2015 ዓ.ም አምዱ በድጋሚ ባሕል እና ኪን ወደሚለው ስያሜው ተመልሷል:: አበጋር፣ ባቲ ገበያ፣ ጮቄ የአፍሪካ የውኃ ማማ፣ ኸረ ባቲ ባቲ፣ የዑራ ጥሪ፣ አራት ዓይና ጎሹ፣ የዕንቁላል ድልድይ፣ አምራች ዘማች፣ የአፋር መልኮች፣ ወረ ኢሉ፣ የጎንደር እስክስታ፣ እሹውዬ፣ እናትዋ ጎንደር፣ ካሲናው ጎጃም፣ ጎደቤ ብሔራዊ ፓርክ፣ የተደበቀችው ገዳም፣ ቀን ሲከፋ እና መሰል በሆኑ ርዕሶች እንደተለመደው ከክልሉ መልከ ብዙ ባሕሎች እየተቆነጠረ ቀርቧል::

አሁን ያለንበት 2017 ዓ.ም ላይ ስንደርስ በክልሉ ባለው የሰላም መደፍረስ ምክንያት ጋዜጠኞች ከተለያዩ የክልሉ አከባቢዎች የሚያስቃኙት ባሕላዊ ጉዳዮች ተገድበዋል:: በዚሁ የፀጥታ መደፍረስ ምክንያትም ጋዜጣዋ ታትማ ለስርጭት መብቃት አልቻለችም፤ ያም ሆኖ ግን ጋዜጣዋም ሆነች የባሕል እና ኪን አምዷ በዲጂታል ሚዲያ ለአንባቢዎች መድረሳቸውን ቀጥለዋል::

ከችግሩ ጋር በተያያዘም በባሕል እና ኪን አምድ የተለያዩ ሙዚቀኞች ሥራዎች፣ ኪናዊ ክዋኔዎች እና ሌሎችም እየተተነተኑ አምዱ የነገን ሰላም በጉጉት በመጠበቅ ላይ ይገኛል:: በአምዱ ላይ እንደወትሮው ብዙ ጋዜጠኞች መሳተፍ ስላልቻሉም አምደኛው አቢብ ዓለሜ ጠንካራ ብዕሩን እንካችሁ እያለን ይገኛል::

የ30 ዓመት ዕድሜ ባስቆጠረችው የበኲር ጋዜጣ ላይ የባሕል አምዷ ምን ዓይነት ጽሑፎችን ይዞ እንደሚወጣና ተሳታፊዎቹ እነማን እንደነበሩ ለማስታወስ ሞክረናል:: ጌታቸው ፈንቴ፣ አባትሁን ዘገየ፣ ሸጋው ሙሉማር፣ አብዮት ዓለም፣ ሱራፌል ስንታየሁ፣ እሱባለው ይርጋ እና አቢብ ዓለሜ ተሳትፏቸው የላቀ የአምዱ ዘጋቢዎች ናቸው:: አምዱን በማስተዳደር እና በመምራት አሻራቸው የተቀመጠ የአሚኮ ጋዜጠኞችም የምስጋናው ተቋዳሽ ይሆናሉ::

አብዛኞቹ በበኲር ጋዜጣ ባሕል እና ኪን አምድ ላይ የተሳተፉ ጋዜጠኞች አሁንም ከበኲር ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል የተዛወሩ ቢሆኑም እንኳን በአሚኮ ውስጥ ጋዜጠኛ ሆነው የቀጠሉ በመሆናቸው የደስታቸውን ወሰን መገመት ይቸግራል:: በተለይ ጌታቸው ፈንቴ፣ ጥላሁን ወንዴ፣ አባትሁን ዘገየ፣ ሙሉ አብይ እና ታምራት ሲሳይ ከበኲር ጋዜጣ ሁሉም አምዶች ጋር ቆይታቸው ረዘም ያለ በመሆኑ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ሁሉንም እንኳን አደረሳችሁ ማለት ይወዳል::

በዚህ የትውስታ ዳሰሳ ውስጥ ለበኲር የባሕል አምድ አስተዋጽኦ አበርክታችሁ ስማችሁ ያልተጠቀሰ ዘጋቢዎች ወይም ተሳታፊዎች ብትኖሩ ዳሰሳው በወፍ በረር እንደሆነ እንድትገነዘቡ አደራ እላለሁ:: ያም ሆኖ ግን በ30 ዓመቱ የበኲር ጋዜጣና የአሚኮ ጉዞ ውስጥ ለነበራችሁ አስተዋጽኦ ምስጋናችን ይድረሳችሁ::

(እሱባለው ይርጋ)

በኲር የታኅሳስ 7  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here