በእግር ኳስ አሰልጣኝነት 25 ዓመታትን አሳልፏል። በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ቡድን ብቻ 13 ዓመታትን አሰልጥኗል፤ ይህም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ በአንድ ክለብ ረጅም ጊዜ በማስልጠን ክብረወሰኑን ጨብጧል። ከሰፈር ቡድን እስከ ብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎችን መርቷል። ከመቶ ብር ደሞዝ ተነስቶ ከ120 ሺህ ብር በላይ ተከፋይ ሆኗል። ከጀማሪ የሰፈር ቡድን እስከ ወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ ኃያሉን የሴቶች ከለብ አሰልጥኗል፤ እያሰለጠነም ይገኛል። ከፕሪሚየር ሊግ እስከ ሴካፋ ክለቦች ዋንጫን አንስቷል- በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ስኬታማው አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው።
አሰልጣኝ ብርሃኑ ተወልዶ ያደገው በኦሮሚያ ክልል ከሸኖ ከተማ ውጣ ብላ በምትገኘው “መኑሻ“ በምትባል የገጠር መንደር ነው። ለቤተሰቡ የመጀመሪያ (የበኩር) ልጅ በመሆን በ1973 ዓ.ም ይህቺን ምድር ተቀላቀለ። ከእርሱ በኋላ አምስት እህት እና ወንድሞቹን በሞት በማጣቱ የህይወት ፈተናን ገና በለጋ እድሜው መጋፈጥ ጀመረ።
ገና ሳይጠነክር በስድስት ዓመቱ እናት እና አባቱ በፍቺ በመለያየት ወደ አዲስ አባበ ተሰደዱ። እርሱም የአያቶችን ከብቶች እየጠበቀ ውሎው የእርሻ ማሳ ውስጥ ሆነ። ከአምስት ዓመታት በኋላ ግን ወላጆቹን ፍለጋ ከአያቶቹ ጠፍቶ በብዙ ወደ ሚወራላት እና ወደ ሚጓጓላት አዲስ አበባ ኮብሏል። በመዲናችን እንዳሰበው ተሳክቶለት ወላጆቹን በቀላሉ ማግኝት ባለመቻሉ ትንሹ ብላቴና እንደ ብዙዎቹ የክፍለ ሀገር ታዳጊዎች የጎዳና ህይወት ዕጣ ፈንታው ሆነ።
ከቀናት በኋላ ግን አዲስ አበባ የሚኖረውን አጎቱን በማግኝቱ ከአጎቱ ጋር አብሮ መኖር ጀመረ። በአጎቱ ቤት ሆኖ ትምህርቱን ቀጠለ፤ ጎን ለጎን ደግሞ የቂቤ እና የእንቁላል ነጋዴ የሆነውን አጎቱን በሥራ በማገዝ የአዲስ አበባን ኑሮ ተያያዘው። በአንድ ቀን በተፈጠረ አጋጣሚ ግን ድጋሚ ወደ ጎድና ወጣ፡፡ አሰልጣኝ ብርሃኑ አጋጣሚውን እንዲህ ያስታውሳል።
“እንደተለመደው ከትምህርት ስዓት ውጪ አጎቴን ለማገዝ ቂቤ እና እንቁላል እሸጣለሁ። አንድ ቀን ይህንን የተለመደውን ተግባሬን ለማከናወን ከቤት ወጣሁ፤ ገበያው ደርቶ ነበር እና ቀንቶኝ 140 ብር ሽጬ ወደ ቤቴ እየተመለስኩ ነው። ነገር ግን መንገድ ላይ አንድ ሰው አስቆመኝ። ከመኪናው ሳይወርድ በመስኮቱ “ጋዝ ግዛልኝ” ብሎ 11 ብር እና ሰጠኝ። ለምላክበት ደግሞ አምስት ብር ጉርሻ ሰጠኝ። ብዙም ሳልርቅ ግን ጠርቶ በማስመለስ፤ እንዴት አምንሀለሁ? እንደ ሌሎች ልጆች ብሩን ይዘህ ትጠፋለህ አለኝ። እኔም በተሰጠኝ የአምስት ብር ጉርሻ ቀይ ወጥ ለመብላት በመጓጓቴ እንደ ማስያዣ 140ውን ብር ሰጠሁት። ከነዳጅ ማዲያ ጋዙን ገዝቼ ስመለስ ግን ሰውዬው የለም”። በማለት አሰልጣኝ ብርሃኑ የተፈጠረውን ክስተት ያስረዳል።
በዚህ ጥፋቱም አጎቱን በመፍራት ድጋሚ ውሎ አዳሩ ጎዳና ላይ ሆኗል። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ በልመና እና በምልጃ ድጋሚ ወደ አጎቱ ቤት መመለሱን ያስታውሳል። ህልሙ እግር ኳስ ተጫዋች መሆን ነበር እና ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ ህልሙን ለመኖር በትርፍ ጊዜው ጃንሜዳ መዋል ጀመረ። ይሁን እንጂ እግር ኳስ ለመጫወት ቢሞክርም ብዙ አልገፋበትም።
በወቅቱ ከጓደኞቹም የተሻለ ግብ ጠባቂ መሆኑ ቢታወቅም መልማዮቹ “እጅ ውርወራ” አትችልም ይሉታል። ተስፈኛው ግብ ጠባቂ ብርሃኑም ክህሎቱን ለማሻሻል ጃን ሜዳን ቤቱ ቢያደርገውም መመረጥ አልቻለም። “የእጅ ውርወራ” ማለት ጉቦ መሆኑን ተረዳ፤ እግር ኳስ ለመጫወት የነበረው ምኞት እና ፍላጎት ከብዙ ጥረት እና ድካም ከሰመ።
ከዚያም የተሻለ ህይወት ፍለጋ ተሰደደ። ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር በመሆን አስከፊውን የስደት ህይወት ቀምሷል። ሱዳን ካርቱም ሁለት ወር ከቆዩ በኋላ ግብጽን አስዋን በመዝለቅ የሲናይ በርሃን በማቆራረጥ እስራኤል ሳይገቡ ድንበር ላይ በፖሊስ ተጠርንፈው ከሞት የተረፉት ወደ ማረሚያ ቤት ዘብጥያ ወርደዋል። ከአንድ አመት ተኩል እስር በኋላም ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።
ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰ በኋላ በጃንሜዳ የሰፈር ወጣቶችን ሰብስቦ እግር ኳስ ማሰልጠን ጀመረ። ፍላጎቱን የተመለከትቱ የወረዳው አስተዳዳሪ ቡድናቸውን እንዲያሰለጥን ኃላፊነት ሰጡት። ይህም አሰልጣኝነቱን እንዲወደው አድርጎታል። በ1992 ዓ.ም የሚኒልክ ትምህርት ቤት ሴት ተማሪዎችን በመሰብሰብ ስልጠና ጀምሯል። የቡድኑ ስያሜም “ምስራቅ ሀረር” ይሰኛል። በወቅቱ ሴቶችን ከማድቤት ወደ አደባባይ በማውጣት እግር ኳስ መጫወት እንደሚችሉ አሳይቷል። ለሴቶቹ አዲስ የብርሃን መንገድ በማሳየት ለራሱም ድቅድቁን ጨለማ የገፈፈበት አዲስ ጮራ ፈንጥቋል። ብዙም ሳይቆይ የካ ክፍለ ከተማ ቡድንን የተረከበ ሲሆን ከቡድኑ ጋር የተሳካ አምስት ዓመታትን አሳልፏል።
በኋላም ሴንተራል ዩንቨርሲቲ ኮሌጅ በተሻለ ክፍያ በመቶ ብር ደሞዝ አስፈርሞታል። በዚህ ቡድን ውስጥም ስኬታማ የሆኑ አምስት ዓመታትን ማሳለፉን ተናግሯል። አሁን እያስለጠነ ያለበትን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በ2003 ዓ.ም የተረከበው ሲሆን ባለፉት 13 ዓመታት በክለቡ ስኬታማ ጊዜያትን አሳልፏል። በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 15 ዋንጫዎችን አንስቷል። ሰባት የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ አሳክቷል። በድምሩ እስካሁን ባለው የእግር ኳስ ህይወቱ 25 ዋንጫዎችን መስብሰብ ችሏል። በየካ ክፍለ ከተማ ሁለት ዋንጫ፣ በሴንትራል ዩንቨርሲቲ ኮሌጅ ሁለት በአዲስ አበባ ምርጥ ስድስት ዋንጫ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደግሞ 15 ዋንጫዎችን አስንስቷል፡፡
እርሱ ሴት እግር ኳስ ተጫዋቾችን ማሰልጠን ከጀመረ ከሁለት ዓመትታ በኋላ (በ1994 ዓ.ም) የተቋቋመውን የሴቶች ብሄራዊ ቡድን በተለያየ አራት አጋጣሚዎች አገልግሏል። በ2013 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈበት የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ለፍጻሜ ደርሷል። በዚሁ መድረክ በቀጣዩ ዓመት ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ በ2015 ዓ.ም ድጋሚ ለፍጻሜ ደርሶ እንደነበር አይዘነጋም። ባሳለፍነው ዓመት ኢትዮጵያ ባስተናገደችው የ2016 የካፍ የሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪ ግን ሻምፒዮን ሆኗል።
በሀገራችን ማንም የማይቀበለውን፣ የሚዲያ ሽፍን የማይሰጠውን የሴቶችን እግር ኳስ ለማሻሻል ብዙ ደክሟል። ሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች የተሻለ ክፍያ እንዲከፈላቸው አሁን ድረስ ሽንጡን ገትሮ ይከራከራል። አሁን ላይ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በርካታ ሴት ተጫዋቾች በእርሱ ግፊት ገንዘብ እንዲቆጥቡ በማድረግ ቤት፣ መኪና እና ሀብት ንብረት እንዲያፈሩ አስችሏቸዋል።
ከምንም በላይ ግን የሴቶች እግር ኳስ በሀገራችን ተቀባይነት ማግኘቱ፤ ለሴቶች የተሻለ ክፍያ መጀመሩ እና ሴቶች በስፖርቱ ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸው ያስደስተኛል ብሏል። አሰልጣኝ ብርሀኑ ባለፉት 13 ዓመታት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአሰልጣኝነት አሳልፏል። ከዚህ በኋላም በንግድ ባንክ ቤት ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይበትን ውል መፈራረሙ ይታወሳል። በሀገራችን ብሎም በምስራቅ አፍሪካ እና በአህጉራችን የእግር ኳስ አሰልጣኞች በአንድ ቡድን ቢበዛ ከሁለት ዓመታት በላይ በማይቆዩበት ዘመን አሰልጣኝ ብርሃኑ ግን ይህን ማድረግ ችሏል። ይህ ደግሞ አሰልጣኙ እና ክለቡ ውጤታማ እንዲሆን አስችሏቸዋል።
አሰልጣኞች የክለቡን ባህል፣ ፍልስፍና ተረድተው ተግባራዊ ማድረግ በሚጀምሩበት ወቅት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ለአሰልጣኞችም፣ ለክለቦችም ውድቀት እንደሆነ ይናገራል። አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ከእረኝነት ተነስቶ ጎዳና ህይወትን ቀምሶ፣ የስደትን ህይወት ዐይቶ እና ከመቶ ብር ደሞዝ ጀምሮ አሁን ከ120 ሺ በላይ ወርሃዊ ተከፋይ በመሆን የሀገሪቱ ታላቅ አሰልጣኝ ሆኗል። ይህ ስኬት በአንድ ጀንበር የተገኝ ሳይሆን በ25 ዓመታት ልፋት እና ድካም የተገኝ መሆኑንም ያስረዳል።
ወጣት አሰልጣኞች ከእርሱ ልምድ ይማሩ ዘንድ በአሰልጣኝነት ህይወቱ ዙሪያ በ2007 ዓ.ም መጽሐፍ አሳትሟል። ርጅሙን የአሰልጣኝነት ህይወቱን የሚዳስስ የዶክመንተሪ ፊልም ደግሞ 25 ዓመት የብር እዮቤል በዓሉን በቀጣይ ወር ሲያከብር ይመረቃል። ብርቱው አሰልጣኝ በተወለደበት አካባቢ በሁለቱም ጾታ የእግር ኳስ ፕሮጀክት አቋቁሟል። ስያሜውም “ብርሃኑ ግዛው በሸኖ ፕሮጀክት” ይሰኛል። የአሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የአሰልጣኝነት የብርሃን መንገድ በሀገራችን ብቻ ሳይሆን በአህጉር አቀፍ ደርጃም ማብራት እና ማንጸባረቅ ህልሙ መሆኑን በቆይታችን ነግሮናል።