“ከእርሻ እስከ ጉርሻ”

0
209

በኢትዮጵያ አጠቃላይ ለእርሻ ከሚውለው መሬት 35 በመቶ የሚሆነውን የአማራ ክልል እንደሚሸፍን የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ያመለክታል። ሆኖም በተደጋጋሚ በሚከሰቱ ግጭቶች በክልሉ የሚገኙትን አርሶ አደሮች ፈትኗቸዋል። ከአንድ ዓመት በላይ የቀጠለው ግጭት ግብርናውን እየፈተነው ይገኛል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አርሶ አደሩ በክልሉ በተፈጠረው የሰላም እጦት እና አለመረጋጋት በስጋት ውስጥ ሆኖም አርሶ፣ አለስልሶ፣ ዘርቶ፣ አርሞ እና ኮትኩቶ … ለፍሬ ያደረሰውን ሰብል መሰብሰብ እንደጀመረ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች መረጃዎችን በስልክ አድርሰውናል። የልፋታቸውን ፍሬ ለመሰብሰብ ሩጫ ላይ ናቸው። ለዚህም በፈጣሪ ዘንድ የዝናቡን መቅለል እና የግጭቶችን መቆም እየተማፀኑ ነው።
በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ባልተሰበሰቡ እና ተሰብስበው ወደ ጎተራ ባልገቡ ሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የጥንቃቄ መልዕክቶች እየተላለፉ ይገኛል። አርሶ አደሩ ለምርጥ ዘር እና ለማዳበሪያ ብዙ ገንዘብ አውጥቶ እንዲሁም ደክሞ እና ለፍቶ ያመረተውን ሰብል ብክነት እንዳይገጥመው በወቅቱ እና በጥንቃቄ መሰብሰብ ያስፈልጋል። አርሶ አደሩ ልፋቱ በከንቱ እንዳይቀርም የደረሱ ሰብሎችን በፍጥነት መሰብሰብ ይጠበቅበታል።
ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ፣ የተባይ ክስተት፣ የግሪሳ ወፍ፣ ግጭቱ … በአጠቃላይ በሰው ሠራሽ እና በተፈጥሯዊ ችግሮች ምክንያት የምርት ብክነትን ከማስከተሉ ባሻገር በጥራት ላይ ጉዳት ያስከትላል። አርሶ አደሩ ይህንን ተገንዝቦ የደረሱ ሰብሎችን የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም እና በተቀናጀ የሰው ኃይል (በደቦ) በፍጥነት መሰብሰብ ይጠበቅበታል። ለዚህም መንግሥት የምርት መሰብሰቢያ ቴክኖሎጂ (ኮምባይነር) በበቂ ቢያቀርብ ሥራውን ያቀላጥፍለታል። ሌላው የደረሱ ሰብሎችን በዘመቻ እና በትኩረት በመሰብሰብ ዝናብ ከማያገኝበት ቦታ ማስቀመጥ፣ መቼ እንደሚታጨዱ እና የመድረቅ መጠናቸውን መለየት፣ ከታጨደ በኋላ በደንብ እንዲደርቁ ማገላበጥ፣ የሚከመርበት ቦታ ደረቅ መሆኑን መለየት፣ በእንጨት ርብራብ ሠርቶ መከመር፣ የአይጥ መንጋ እንዳይበላው ከቁጥቋጦ እና ጫካ አካባቢ ማራቅ ከዚያም ፈጥኖ በደረቁ ወቅቶ ወደ ጎተራ እና ቤት በማስገባት ምርትን ከብክነት መታደግ ይገባል።
የደረሱ ሰብሎችን እየሰበሰቡ እንደሆነ በስልክ ለበኩር አስተያየታቸውን ካደረሱን አርሶ አደሮች መካከል በምሥራቅ ጎጃም ዞን የሁለት እጁ እነሴ ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር የሺዋስ አላምር አንዱ ናቸው። በምርት ዘመኑ የተሻለ ግብዓት አግኝተው ማሳቸውን በተለያዩ ሰብሎች ሸፍነዋል። አርሶ አደሩ ከይዞታ መሬታቸው በተጨማሪ በኪራይ እና በጥማድ ጤፍ፣ በቆሎ፣ ዳጉሳ እና በርበሬ ዘርተዋል። በዚህ ወቅት የደረሱ የጤፍ ሰብላቸውን እንደሰበሰቡ ነው የነገሩን። የሰበሰቡትን የጤፍ ሰብል ዝናብ እንዳያበላሸው መረባርብ በመሥራት በጥንቃቄ መከመራቸውን አክለዋል።
አርሶ አደሩ እንደነገሩን በአንድ ሄክታር ማሳቸው ላይ የነበረውን የጤፍ ሰብል ከሰበሰቡ በኋላ እርጥበትን ተጠቅመው ሽምብራ እና ጓያ ለመዝራት እያረሱ ነው። በቀጣይ ቀናትም የደረሱ የበቆሎ ሰብሎችን እና ሌሎች ሰብሎችን ለመሰብሰብ ተዘጋጅተዋል።
ሌላው የሰሜን ጎጃም ዞን ደቡብ አቸፈር ወረዳ ነዋሪው ሰላምሰው አማረ ናቸው። በሁለት ሄክታር መሬታቸው ላይ ጤፍ፣ በቆሎ፣ ገብስ እና ዳጉሳ ዘርተው ለፍሬ አብቅተዋል። ዓመቱ ጥሩ የሰብል ቁመና የታየበት ነው ብለዋል። የገብስ ሰብላቸውን እንደሰበሰቡ እና አሁን ላይ ደግሞ በሰበሰቡት የጤፍ ማሳው ላይ ጓያ እየዘሩ እንደሆነ ነግረውናል። በቆሎ መድረቁን እና ለመሰብሰብ ዝግጁ መሆኑንም አክለዋል።
አርሶ አደሩ እንደተናገሩት ያጨዱትን የጤፍ ሰብል ከፍ ባለ ቦታ እና በጥንቃቄ ከምረዋል። ይሁን እንጂ ሰሞኑን የዝናቡ ስርጭት በመጨመሩ ስጋት አድሮብኛል ነው ያሉት። ይህ ደግሞ በተለይ በሚዘሩት የጓያ ዘር ላይ ጫና እንደሚያሳድር አስረድተዋል።
አርሶ አደር ሀሰን ይመር በምዕራብ ጎጃም ዞን የጃቢ ጠህናን ወረዳ ነዋሪ ናቸው። የሰላም እጦቱ በዘር ወቅት ጫና አሳድሮ እንደነበር ተናግረዋል። ሆኖም ሦስት ሄክታር በሚጠጋ መሬታቸው የተለያዩ ሰብሎችን ሸፍነዋል። በአካባቢው በቆሎ፣ ጤፍ እና በርበሬ በብዛት እንደሚመረት ተናግረዋል። እንደ በቆሎ ያሉ የደረሱ ሰብሎችን እንደሰበሰቡ አስረድተዋል። የዳግም ሰብል ሽምብራ ዘር ለመዝራት አርሰውም ዝግጁ አድርገዋል።
በሌላ በኩል ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እየዘነበ በመሆኑ በጤፍ ሰብል ላይ ጉዳት ያደርሳል የሚል ስጋት ፈጥሮባቸዋል።
የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ እና በአግባቡ በመሰብሰብ የምርት ብክነትን ለመቀነስ እየተሠራ መሆኑን የምሥራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበበ መኮንን አስታውቀዋል። በዞኑ በ2016/2017 የምርት ዘመን ከ612 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች በዘር እንደተሸፈነ ተናግረዋል።
በዘር ከተሸፈነው ውስጥ ጤፍ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል ያሉት መምሪያ ኃላፊው 190 ሺህ ሄክታር የሚሆነው ማሳ በጤፍ፣ 172 ሺህ ሄክታር መሬት ደግሞ በስንዴ ዘር እና ከ84 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበቆሎ ዘር ተሸፍኗል ብለዋል::
መምሪያ ኃላፊው ለበኩር በስልክ እንዳብራሩት በዞኑ የጤፍ፣ የስንዴ እና የበቆሎ ሰብሎች በስፋት ይመረታሉ። በዓመቱ በቂ ግብዓት አቅርቦት መቅረቡ፣ ተስማሚ የአየር ንብረት መኖሩ እና የበሽታ ክስተቱ ዝቅተኛ መሆኑ የተሻለ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል። ኃላፊው አክለውም ከእርሻ ማሳ ዝግጅት ጀምሮ በግብዓት አቅርቦት እና የተሻሻሉ አሠራሮች ተግባራዊ በመደረጋቸው የተሻለ የሰብል ቁመና ማየት ተችሏል ነው ያሉት።
ከጥቅምት ወር የመጨረሻ ሳምንት ጀምሮ ሰብሎች በስፋት እንደሚሰበሰቡ ተናግረዋል። ሰብሉ በብዛት በሰው ጉልበት እንደሚሰበሰብ የተናገሩት ኃላፊው ከዚህ በተጨማሪም በመሰብሰቢያ ማሽን (በኮምባይነር) እንደሚሰበሰብ ተናግረዋል። በዞኑ የሚገኙ ዘጠኝ ኮምባይነሮችን በሙሉ አቅም ለመጠቀም ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል:: በቀጣይም ከክልል እና ከፊደራል ተጨማሪ ኮምባይነሮች እንደሚገቡ ጠቁመዋል። አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ በመሰብሰብ በደረቅ እና በንፁህ ቦታ ማስቀመጥ ይጠበቅበታል ብለዋል። በወቅቱ ወቅቶ ወደ ቤቱ ማስገባት እንዳለበትም አመላክተዋል።
እንደ ኃላፊው ማብራሪያ በዞኑ ቀድመው የተዘሩ ሰብሎች (ገብስ፣ አተር እና ቦለቄ፣ …) እስካሁን ከ34 ሺህ ሄክታ በላይ የሚሆነውን መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል።
ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እና መሰል ችግሮች ምርት እንዳይባክን እና እንዳይበላሹ አርሶ አደሮች ጉልበታቸውን እና ሙሉ አቅማቸውን በመጠቀም የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ መሰብሰብ እና መውቃት እንደሚገባም መምሪያ ኃላፊው አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት እና ጥበቃ የድህረ ምርት ቴክኖሎጂ ባለሙያው ምትኩ መላኩ እንደገለፁት የምርት ብክነት በጥራት እና በመጠን ይከሰታል። በግብርናው ዘርፍ ልክ እንደ ቅድመ ምርት ዝግጅት ሁሉ ድህረ ምርት ላይ ትኩረት እየተሰጠው እንዳልሆነ ያብራራሉ። የድህረ ምርት አያያዝ ላይ ብዙ እንዳልተሠራም አመላክተዋል። የምርት ብክነት በአያያዝ ጉድለት የሚከሰት እንደሆነም ያስረዳሉ።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በተለያዩ ምክንያቶች 34 በመቶ ያህል የምርት ብክነት ይከሰታል፤ በአግባቡ፣ በወቅቱ እና በጥንቃቄ አለመሰብሰብ እና አለመያዝ፣ የሰብሉን ትክክለኛ የመድረቅ ደረጃ አለመለየት፣ የግንዛቤ ፈጠራ አናሳ መሆን፣ የተሻሻሉ አሠራሮችን አለመከተል፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን አለመጠቀም እና ሌሎች ጉድለቶች ለምርት ብክነት ዋና ዋና ምክንያች እንደሆኑ ባለሙያው አቶ ምትኩ ዘርዝረዋል።
በክልሉ በእርሻ ሥራ ከተሰማራው አርሶ አደር አኳያ ቴክኖሎጂን እየተጠቀመ ያለው አርሶ አደር በጣም ውስን መሆኑን አስረድተዋል። አርሶ አደሩ፣ ባለሀብቱ እና ነጋዴው የተለመደውን አካሔድ በመቀየር ዘመናዊ መንገዶችን መጠቀም ይገባቸዋል ብለዋል።
አርሶ አደሩ ሰብሉን በወቅቱ ማጨድ (መሰብሰብ) ሲከምር በደረቅ ቦታ ማስቀመጥ፣ በአግባቡ ማድረቅ፣ ማገላበጥ፣ በጥንቃቄ ማጓጓዝ፣ መውቃት፣ ማበጠር ይገባል። ከተለመደ አሠራር ወጥቶ ዘመናዊ እና የተሻሻሉ አሠራሮችን መከተል ይገባል። ምርቱ ለገበያ እና ለምግብነት እስኪውል ድረስ በጥንቃቄ መያዝ ተገቢ ነው ብለዋል። አርሶ አደሮች የሰብል መፈልፈያ፣ መውቂያ፣ ማጓጓዣ፣ ማከማቻ፣ መሰብሰቢያ እና ማድረቂያ ቴክኖሎጂ እንዲጠቀሙ ምክረ ሐሳባቸውን አቅርበዋል። ይህ ሲሆን ደግሞ የምርትን ጥራት ከመጨመር ባሻገር የምርት ብክነትን እንደሚያስቀር አብራርተዋል።
በአንዳንድ የምዕራብ አማራ አካባቢዎች ያልተጠበቀ ዝናብ እየተከሰተ ስለመሆኑ የተናገሩት ባለሙያው ዝናቡን ተከትሎ የሚከሰተውን የሰብል ምርት ጉዳት ለመቀነስ አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ መሰብሰብ እንዳለበት ነው ያሳሰቡት። በአጠቃላይ በጥራትም በብዛትም ለማምረት ከእርሻ እስከ ጉርሻ ድረስ የግብርና ተግባራትን በአግባቡ ማከናወን ይገባል ብለዋል።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here