“ገበሬው መጣ ሳስሎ ማጭድ
ስንዴ እና ጤፉን በወቅቱ ሊያጭድ!” የሚለው የኢትዮጵያዊያን ብሂል በተግባር የሚታይበት ወቅት ነው። አርሶ አደሩ ፈጣሪውን አምኖ፣ ሰማዩ የሚለግሰውን ዝናብ ጠብቆ አርሶ፣ አለስልሶ፣ ዘርቶ፣ ኮትኩቶ፣ አርሞ፣ ከወፍ እና ከተባይ ጠብቆ ለፍሬ ያደረሰውን ሰብል መሰብሰብ ጀምሯል።
ከዚህ ባለፈም ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚሻ ወቅት ነው፤ ካልሆነ ደግሞ አርሶ አደሩ ከግንቦት ጀምሮ የለፋበት መና ሊቀር ይችላልና ነው:: በመጠንም በጥራትም የምርት ብክነት እንዳይከሰት ታዲያ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል።
ለሰብል ስብሰባው በቂ የሰው ጉልበት እና ዘመናዊ የምርት መሰብሰቢያ ቴክኖሎጂ እጅግ አስፈላጊ ናቸው። ለሰብል ስብሰባው በርካታ የሰው ኃይል ከሚፈለግባቸው አካባቢዎች መካከል ደግሞ የምዕራብ ጎንደር ዞን አንዱ ነው። በዞኑ የሰሊጥ ሰብል ስብሰባም ተጀምሯል::
የደረሱ ሰብሎችን እየሰበሰቡ እንደሆነ በስልክ ለበኩር አስተያየታቸውን ካጋሩን አርሶ አደሮች መካከል የምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ ደለሎ አካባቢ ነዋሪው አርሶ አደር ሀብቱ ፅዱ አንዱ ናቸው፤ አርሶ አደሩ እንደነገሩን በ343 ሄክታር መሬት ላይ ሰሊጥ፣ ጥጥ፣ ማሽላ፣ አኩሪ አተር እና ማሾ እያመረቱ ይገኛሉ:: ከዚህ ውስጥ 20 ሄክታር መሬት በሰሊጥ ሰብል የተሸፈነ ነው።
የሰብሉ ቁመና ሲታይ የሚጠብቁትን ያህል ምርት ሊያገኙ እንደሚችሉ የተናገሩት አርሶ አደር ሀብቱ ምርቱ አሁን የመሰብሰቢያው ወቅት ነው ብለዋል፤ ምርቱን ወቅቱን ጠብቆ ለመሰብሰብ ታዲያ በአካባቢው በርካታ የጉልበት ሠራተኞች እንደሚያስፈልጋቸው ነው የገለፁት:: እርሳቸውም የሰሊጥ ሰብላቸውን ለመሰብሰብ ከ200 በላይ የጉልበት ሠራተኞች እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል::
ይሁን እንጂ የጉልበት ሠራተኛ እጥረት እንዳጋጠማቸው ነው በስልክ የነገሩን። እንደ አርሶ አደሩ ማብራሪያ ሰሊጥ ጊዜ የማይሰጥ ሰብል ነው፤ በትክክለኛው ጊዜ መሰብሰብ ካልተቻለ ደግሞ ምርቱ በቀላሉ በመፍሰስ ለብክነት ይጋለጣል::
በተመሳሳይ የአኩሪ አተር የመሰብሰቢያ ጊዜም እየደረሰ በመሆኑ በቂ የሰው ኃይል ያስፈልጋቸዋል:: ሠራተኞችን ለመቀበልም የተሟላ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸው ሠራተኞች እንዲመጡላቸው ጥሪ አቅርበዋል::
የምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ባለሙያ ቻላቸው አቸነፍ ለበኩር በስልክ እንደተናገሩት ከመኸር እርሻ የሚጠበቀውን ምርት ለማግኘት ባለፉት ጊዜያት ሰብልን የማረም፣ የመጠበቅ እና የመንከባከብ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።
ወቅቱ ደግሞ የሰሊጥ ምርት የሚሰበሰብበት ነው፤ በመሆኑም የምርት ብክነት እንዳይከሰት የዞኑ ግብርና መምሪያ ከሚመለከታቸው ጋር በመሆን የምርት ብክነትን ለመቀነስ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
ዞኑ ለውጪ ገበያ የሚቀርቡ (የኤክስፖርት) እና የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን ጨምሮ ለምግብ የሚሆኑ ሰብሎችን በስፋት ያመርታል። ሰሊጥ፣ ጥጥ፣ አኩሪ አተር እና ማሽላ ደግሞ በስፋት ከሚመረቱ መካከል ናቸው።
ባለሙያው እንዳሉት ምዕራብ ጎንደር ዞን በቅባት ሰብሎች ከአማራ ክልል አልፎ እንደ ሀገር ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው አካባቢ ነው፤ በመሆኑም የደረሱ ሰብሎችን ርብርብ በማድረግ በወቅቱ መሰበሰብ ይገባል::
በ2017/18 የምርት ዘመን 529 ሺህ 649 ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ 525 ሺህ 26 ሄክታሩ በተለያዩ የሰብል አይነቶች ተሸፍኗል። በዘር ከተሸፈነው ውስጥ ሰሊጥ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል፤ ባለሙያው እንዳስታወቁት 181 ሺህ 929 ሄክታር መሬት በሰሊጥ የተሸፈነ ነው። ከዚህም አንድ ሚሊዮን 311 ሺህ 952 ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል። እስካሁንም ከ38 ሺህ ሄክታር በላይ የሰሊጥ ሰብል ተሰብስቧል።
የዞኑ ግብርና መምሪያ እንዳስታወቀው በዞኑ የለማውን የሰሊጥ ሰብል በወቅቱ ለመሰብሰብ ከ900 ሺህ በላይ የጉልበት ሠራተኞች ያስፈልጋሉ። የምግብ፣ የመጠለያ፣ የውኃ፣ የመድኃኒት እና ሌሎች አቅርቦቶችም ዝግጁ ተደርገዋል::
ይህን ታሳቢ በማድረግ የጉልበት ሠራተኞች በቶሎ ወደ ዞኑ እንዲመጡ ባለሙያው አቶ ቻላቸው አቸነፍ ጥሪ አቅርበዋል:: የታጨደው ሰብል በዝናብ እንዳይበላሽም በአግባቡ አናፍሶ እና አድርቆ በመከመር ምርቱን ከብልሽት መታደግ እንደሚገባ አስረድተዋል።
ምርቱ ጊዜው ሳያልፍ እንዲሰበሰብ እና ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ በየአካባቢው ያሉ የግብርና ባለሙያዎች አስፈላጊውን ሙያዊ ድጋፍ እንዲያደርጉም አሳስበዋል።
በዞኑ በዘር ከተሸፈነው ጠቅላላ መሬት (525 ሺህ 26 ሄክታር መሬት) ከ12 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት የድህረ ምርት አያያዝ ባለሙያው ምትኩ መላኩ ለበኩር ጋዜጣ እንደተናገሩት የድህረ ምርት አያያዝን በተመለከተ ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ ሰፊ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እየተሠራ ነው። አርሶ አደሩ ቀድሞ ለሰብል ስብሰባው የሚያስፈልገውን ቁሳቁስ እንዲያሟላ እና አስፈላጊውን የሰው ኃይል እንዲዘጋጅ ምክረ ሐሳቦች እየተሰጡ ነው።
ክልሉ ያቀደውን የምርት መጠን ለማሳካት ቅድመ ምርት ላይ ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጠው ሁሉ ድህረ ምርት ላይም ሁሉም መረባረብ አለበት። በሀገራችን ብሎም በክልላችን ሰብል ወቅቱን ጠብቆ ከማሳ ስለማይሰበሰብ ሰብሎች በድርቀት ብዛት ተሰባብረው ይወድቃሉ፤ ይረግፋሉም።
በማሳ ውስጥ ወይም በቤት አካባቢ በመከመር እንዲቆዩ ስለሚደረግም በዝናብ፣ በፀሐይ፣ በቤት እና ዱር እንስሳት እንዲሁም በአዕዋፍ ይጠቃሉ፤ ለተባይም ይጋለጣሉ:: ከዚህም ሌላ ገበሬው እህሉን የሚወቃው ጥራቱን ባልጠበቀ አውድማ ላይ በከብቶች በማበራየት ወይም በዱላ በመደብደብ ስለሚሆን ፍሬዎች በመፈናጠር፣ በመሰባበር እና በከብቶች ሽንት፣ እበት እና በሌሎች ባዕድ ነገሮች ይበከላሉ::
ይህ ሁሉ ተደማምሮ ታዲያ ከፍተኛ የምርት ብክነትን እንደሚያስከትል ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት፤ ጥራቱንም ዝቅ ያደርገዋል፡፡ዳይሬክተሩ እንዳስገነዘቡት የደረሱ ሰብሎችን ለመሰብሰብ የሚያስፈልጉ ማጭዶች ወይም ሌሎች መሣሪያዎች ለሰብል ስብሰባው የሚመቹ መሆናቸውን ማረጋገጥ፣ የተበላሹ ምርቶችን ካልተበላሹት መለየት ያስፈልጋል። እያንዳንዱ ሰብል ሲደርስ የሚያሳየውን የድርቀት መጠን በመከታተል ፈጥኖ ማጨድ እና መውቃትም ይገባል።
በተመሳሳይ ከዓመት ዓመት አርሶ አደሩ ቴክኖሎጂን የመጠቀም ፍላጎቱ እየጨመረ ነው፤ የምርት ብክነትን ለመከላከል የምርት መሰብሰቢያ፣ ማድረቂያ፣ ማጓጓዣ፣ መውቂያ እና ማከማቻ ቴክኖሎጂዎች ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው። ይህም የምርት ብክነትን በከፍተኛ መጠን እንደሚቀንስ ነው የተናገሩት።
ይሁን እንጂ በክልሉ በእርሻ ሥራ ከተሰማራው ከፍተኛ የአርሶ አደር ቁጥር አኳያ ቴክኖሎጂን እየተጠቀመ ያለው ውስን መሆኑን አስረድተዋል። ይህም የሆነው ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቅ መሆኑን ደግሞ በምክንያትነት አንስተዋል።
በአብዛኛው የምርት ብክነት ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እና የተባይ መከሰትን ጨምሮ በአያያዝ ጉድለት የሚከሰት ነው። በወቅቱ፣ በአግባቡ እና በጥንቃቄ አለመሰብሰብ እና አለመያዝ፣ የተሻሻሉ አሠራሮችን አለመከተል፣ የሰብሉን ትክክለኛ የመድረቅ ደረጃ አለመለየት፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን አለመጠቀም፣ የከረመው እህል በተባይ የመያዝ ዕድሉ ሰፊ በመሆኑ የከረመን እና አዲሱን እህልን ቀላቅሎ ማስቀመጥ፣ የእህል ማስቀመጫ ጎተራዎችን አለማፅዳት፣ በተገቢው መንገድ አለማበጠር፣ የግንዛቤ ማነስ እና ሌሎች ጉድለቶች ለምርት ብክነት ምክንያች ስለመሆናቸውም አንስተዋል።
በመሆኑም አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን የሚቀርቡ ውስን የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም እና በተቀናጀ የሰው ኃይል (በደቦ) በፍጥነት መሰብሰብ ይጠበቅበታል ብለዋል። አርሶ አደሩ ሰብሉን በወቅቱ መሰብሰብ፣ ሲከምር ደረቅ ቦታ መምረጥ፣ በአግባቡ አገላብጦ ማድረቅ፣ በጥንቃቄ ማጓጓዝ፣ ደረጃውን በጠበቀ አውድማ መውቃት እና ምርቱን ከገለባው (ከባዕድ ነገሮች) መለየት፣ ነጋዴውም ሆነ የእርሻ ባለሀብቱ ደረጃውን የጠበቀ የእህል ማከማቻ መጋዝን መጠቀም ይጠበቅበታል።
ከዚህ በተጨማሪም ከፕላስቲክ የተሠሩ የእህል ማከማቻ ከረጢቶችን (ዘመናዊ ጆንያዎች) እና ከተባይ የሚከላከሉ ከብረት የተሠሩ የእህል ማከማቻ ጎተራን መጠቀም ይገባል። ይህ ሲሆን ደግሞ የምርትን ጥራት ከመጨመር ባሻገር የምርት ብክነትን ያስቀራል።
ምርቱ ለገበያ እና ለምግብነት እስኪውል ድረስ በጥንቃቄ መያዝ ተገቢ መሆኑን የጠቆሙት ባለሙያው ከእርሻ እስከ ጉርሻ ድረስ ጥንቃቄ በተሞላበት ሥራን ማከናወን ይገባል ብለዋል።
በሰሊጥ ምርት የክልሉን አቅም ከማጎልበት አንፃር በትኩረት እየተሰራ ሲሆን የግብርና ባለሙያዎች ለአርሶ አደሮች እና ባለሀብቶች ተገቢውን ክትትል እና ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ከክልሉ ግብርና ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። የቢሮው የሰብል ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ አስላከ ለበኩር እንደገለጹት፤ በክልሉ በመኸር 550 ሺህ 465 ሄክታር መሬት በሰሊጥ ዘር ተሸፍኗል። ከዚህም አራት ሚሊዮን 404 ሺህ ኩንታል የሰሊጥ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
መረጃ
የምርት ብክነት ለመቀነስ ሊደረጉ የሚገቡ ጥንቃቄዎች
ከመጠን በላይ ሳይደርቅ በወቅቱ መሰብሰብ።
ምርትን የመሰብሰብ ተግባር መከናወን ያለበት ፀሀያማ እና ደረቅ አየር ባላቸው ቀናት መሆን አለበት፡፡
የታጨደው ሰብል በዝናብ እንዳይበላሽም በአግባቡ አናፍሶ እና አድርቆ መከመር አለበት።
የሚሰበሰበው ምርት ከአፈር ጋር እንዳይነካካ በዝርግ ሸራ ላይ ወይም በጆንያ ውስጥ መግባት ይኖርበታል።
ለጥራጥሬዎች እና ለእህሎች እንደ ኮምባይነር ያሉ ዘመናዊ ማሽነሪዎችን መጠቀም ያስፈልጋል።
ምርቱን ለማጓጓዝ ተገቢውን ማሸጊያ (ለምሳሌ ጠንካራ ሳጥን፣ የተሻሻለ ጆንያ) መጠቀም እና ሌሎች ጥንቃቄዎችን ማድረግ ይገባል።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም