ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎች

0
9

በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ አንድ ቢሊዮን የሚጠጋ ሰው ለሕመም ሲጋለጥ አንድ ሚሊዮን  ሰዎች ከእንስሳት ወደ ሰው በሚተላለፉ በሽታዎች ሳቢያ እንደሚሞቱ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል።

የእንስሳት፣ የእፅዋት እና የአካባቢ ጤና ካልተጠበቀ ማኅበረሰቡ በበሽታ የመጠቃት ዕድሉ የሰፋ መሆኑም ተጠቁሟል። በመሆኑም የተላላፊ በሽታዎችን ስርጭት ለመቆጣጠር፣ በዘላቂነት ለመቋቋም፣ ለአካባቢ፣ ለእንስሳት፣ ለውኃ እና ለአየር ጤንነት መጠበቅ ተቋማት በትብብር መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ተመላክቷል።

የአማራ ክልል የአንድ ጤና ምልከታ ማስተባበሪያ መማክርት የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም እና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ  በባሕር ዳር ከተማ አካሂዷል።

የአንድ ጤና ምልከታ ማስተባበሪያ መማክርት ውይይቱን ያካሄደው የክልል እና የዞን የሥራ ኃላፊዎች፣ ከፍተኛ ባለሙያዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ጳጉሜን 01 ቀን 2017 ዓ.ም ነው። ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመከላከል የተቋማት ቅንጅታዊ አሠራርን ማጠናከር እንደሚገባም በውይይቱ ተነስቷል።

በውይይቱ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) እንደገለፁት ባለፉት ዓመታት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎች ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ቀውሶችን ሲያስከትሉ ቆይተዋል። የኮሮና ቫይረስ ያስከተለውን ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳትም አብነት አንስተዋል።

ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎች እና በክልሉ የተከሰተው ግጭት በኅብረተሰቡ ላይ እያሳደረ ያለው የጤና፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫና እጅግ አሳሳቢ ነው ያሉት ዶክተር ሙሉነሽ ውስብስብ የስነ – ልቦና ጫናው በኅብረተሰባችን ዘንድ ህይወቱን በተረጋጋ መልኩ እንዳይመራ እያደረገው ይገኛል።

“ትውልድን እና ሀገርን ለመገንባት እና ለነገ መሠረት ጥለን ለማለፍ ከፅንሰት ጀምሮ ሕጻናት ጤናማ ሆነው እንዲያድጉ ክትትል ማድረግ ይገባል” ብለዋል። የአማራ ክልል የበርካታ ፀጋዎች ባለቤት ቢሆንም በርካታ ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ተጋርጠውበታል፤ “ይህን በመገንዘብም የኅብረተሰባችንን ጤና ለመጠበቅ እና አምራች ዜጋ ለመፍጠር የክልሉ መንግሥት ከአጋር አካላት ጋር በመሆን እየሠራ ይገኛል” ብለዋል።

ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎችን፣ የአካባቢ ብክለትን፣  የመድኃኒት መላመድን ለመከላከል መንግሥታዊ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ  ድርጅቶች እና በክልሉ የሚገኙ  ዩኒቨርሲቲዎች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል። በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች እና ባለሙያዎች በክልላችን እያጋጠመ ያለውን የሰው፣ የእንስሳትና የአካባቢ ጤና ችግርን ለመፍታት በክልሉ የሚሠሩ የአንድ ጤና ምልከታ ተግባራትን ቅንጅታዊ አሠራሩን በማጠናከር ሙያዊ እገዛ እንዲያደርጉ ዶክተር ሙሉነሽ ጥሪ አቅርበዋል።

የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ እንዳሉት ከእንስሳት ወደ ሰው በሚተላለፉ በሽታዎች፣ በጸረ ተባይ እና ሌሎች ኬሚካሎች አጠቃቀም ችግር ሰዎች ለሞት እየተዳረጉ ነው። ችግሩን ለመከላከል የአንድ ጤና ምልከታ  ትኩረት ተሠጥቶት እየተሠራ ነው።

ከዚህ በፊት በወረርሽኝ የተከሰቱ እንደ ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19)፣ የመተንፈሻ በሽታዎች፣ ውሻን የሚያሳብድ በሽታ፣ አባ ሰንጋ  የመሳሰሉት በሽታዎች  የበርካታ ሰዎችን ህይወት ከቀጠፉ በሽታዎች ውስጥ ተጠቅሰዋል። ፖለቲካዊ፣  ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ችግር እያስከተሉ ይገኛሉ። ችግሩን ለመከላከል የአንድ ተቋም ኃላፊነት ብቻ ባለመሆኑ ሁሉም ሊረባረብ ይገባል ብለዋል።

እ.አ.አ በ2008 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወኪሎች በተገኙበት በዋናነት የዓለም ጤና ድርጅት (WHO)፣ የምግብና እርሻ ድርጅት (FAO)፣ የእንስሳት ጤና ድርጅት እና የአካባቢ ጤና ድርጅት የአራትዮሽ ስምምነት በማድረግ የአንድ ጤና ማዕከል መሥርተው ወደ ሥራ እንደገቡ አቶ በላይ አስረድተዋል። ይህም ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመከላከል ትልቅ አስተዋፅኦ ነበረው ብለዋል። በኢትዮጵያም ብሎም በአማራ ክልል የአንድ ጤና ምልከታ ማዕከላት እየስፋ መምጣቱን ጠቁመዋል። በመሆኑም የክልሉ ሕብረተሰብ ጤና  ኢንስቲትዩት በክልሉ የአንድ ጤና ምልከታ ማስተባበሪያ መማክርት በተጠናከረ መንገድ ተቋማዊ ሆኖ እንዲቀጥል ከእቅድ ጀምሮ ኢንስቲትዩቱ ከእንሰሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ጽ/ቤት እና ከአካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን ጋር ተግባራትን በተጠናከረ መንገድ እያከናወነ መቆየቱን ገልፀዋል። ይህን አጠናክሮ ለመቀጠል በትኩረት እንደሚሠራም አስረድተዋል።

የአባ ሰንጋ በሽታም በሰሜን ወሎ፣ ዋግኽምራ፣ ሰሜን ጎንደር እና ሌሎች አካባቢዎች  ችግር መሆኑን ገልጸዋል። ውሻን የሚያሳብድ በሽታ እና ሌሎች  በሽታዎችም የኅብረተሰብ ጤና ችግር መሆናቸውን ነው የተናገሩት። በመሆኑም ማኅበረሰቡን የማስተማር፣ የማሳወቅ እና ግንዛቤውን የማሳደግ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል። የክልሉ መንግሥት ካቀደው የ25 ዓመት አሻጋሪ የልማት ዕቅድ ጋር በማቀናጀት ለመሥራት ትኩረት መደረጉን አብራርተዋል።

የአማራ ክልል እንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ቢሮ  የእንስሳት ጤና  ጥበቃ እና ቁጥጥር ተወካይ ዳይሬክተር አሰፋ ረዳኢ  ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመከላከል በአንድ ጤና ምልከታ አማካኝነት እየተሠራ ነው ብለዋል።

ማኅበረሰቡ እንስሳትን ቀድሞ እንዲያስከትብ፣ በአባ ሰንጋ ምክንያት የሞቱ እንስሳትን እንዳይመገብ እና በአግባቡ እንዲያስወግድ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ነው የገለጹት።

የአንድ ጤና ምልከታ ዓለም አቀፍዊ እና ሀገራዊ በመሆኑ አማራ ክልልም ይህንን ጉዳይ ተገንዝቦ በትኩረት እየሠራ ይገኛል። በአንድ ተቋም ብቻ የማይሠሩ ተግባራት በመኖራቸው በጋራ መሥራትን የሚጠይቅ ነው። ኢትዮጵያ በ2030 ውሻን የሚያሳብድ በሽታን እና አባ ሰንጋን ለማጥፋት ዕቅድ ይዛ እየተንቀሳቀሰች እንደምትገኝ ጠቁመዋል። በአማራ ክልል በዚህ ዓመት 100 ሺህ ውሻዎችን ለማስከተብ ዕቅድ ተይዞ ወደ ተግባር መገባቱን ነው ያስረዱት። የውሻ ባለቤቶችም ተከታትለው ማስከተብ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ጤና መምሪያ ኃላፊ አየለ አልማው በበኩላቸው ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመከታተል እና ለመቆጣጠር ካለፉት ዓመታት በተሻለ መንገድ አደረጃጀት ተፈጥሮ እየተሠራ መሆኑን ገልፀዋል። ውሻን የሚያሳብድ በሽታ (Rabies) ለመከላከልም የውሻ ባለቤቶች እንዲያስከትቡ ግንዛቤ በመፈጠሩ ጥሩ ጅምር መኖሩን አስረድተዋል። ለክትባቱ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በማሟላት ከተጠሪ ጽ/ቤቱ ጋር በጋራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። ባለቤት የሌላቸው ውሻዎች ግን ለመከተብ አስቸጋሪ አድርጎታል። ውሻን የሚያሳብድ በሽታ የማኅበረሰቡ የጤና ስጋት በመሆኑ በንቃት መሥራት ይጠበቃል ብለዋል።

የውሻ ባለቤቶች ውሾችን ማሰር፣ በየዓመቱ ማስከተብ፣ ከውሾች ንክሻ ራስን መጠበቅ፣ በበሽታው የሚጠረጠር ውሻ ወይም ሌላም እንስሳ ላይ ከታየ ለአካባቢው የሰው እና እንስሳት ጤና ባለሙያዎች ማሳወቅ፣ የባለሙያን ምክር መተግበር፣ የሞቱ ውሻዎችን ማቃጠል ወይም ከመኖሪያ ስፍራ አርቆ መቅበር ይገባል። የአንድ ጤና ምልከታ ማስተባበሪያ መማክርቱን የአብክመ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሰብሳቢነት፣ የአብክመ እንስሳት እና ዓሳ ሃብት ቢሮ  ምክትል ሰብሳቢነት እና የአብክመ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አባል በመሆን ተቋቁሞ እየሠራ ይገኛል።

 

 

ጤና

ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፍ በሽታ

የእብድ ውሻ በሽታ ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፍ እና ገዳይ በሽታ ነው:: በሽታው እጅግ ጥቃቅን በሆኑ በኤሌክትሮ ማይክሮስኮፕ የሚታዩ ከባክቴሪያዎች ባነሱ (lyssavirus) በሚባሉ ቫይረሶች አማካኝነት ይከሰታል:: በበሽታው ከተጠቁ እንስሳት ወደ ሰው ይተላለፋል:: ቫይረሱ ወደ ሰው ሰውነት በለሃጫቸው እና በምራቃቸው አማካኝነት ከገባ በኋላ የነርቭ ሴሎች በብዛት በሚገኙበት አካባቢ ማለትም በጭንቅላት ሴሎች እና በምራቅ ዕጢዎች ይራባል::

(መልካሙ ከፋል)

በኲር የመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here