ከከባቢ ዓየር ማዳበሪያ መስሪያ ግብአትን

0
128

ከፍተኛ የኃይል ፍላጐት ወይም በካይትነት ከሚያስከትለው ተለምዷዊ አሰራር በተለየ ከከባቢ ዓየር እና ከውኃ ለአፈር ማዳበሪያ መስሪያ ቁልፍ ግብአት የሆነውን አሞኒያ ማምረት የሚያስችል መሳሪያ መሰራቱን ሳይቴክ ዴይሊ ድረ ገጽ ከሳምንት በፊት ለንባብ አብቅቶታል፡፡

የስታንፎርድ ዩኒቨርስቲ የተመራማሪዎች ቡድን ከፍተኛ ኃይል  ሳይጠይቅ፣ በካይነት ሳይለቅ፣ ግዢ እና ማጓጓዝ ሳይስፈልግ በአርሶ አደሮች ጀርባ የሚታዘል በእርሻው ውስጥ አሞኒያን ማምረት የሚያስችል መሳሪያ ነው የሰሩት፡፡

የስታንፎርድ ዩኒቨርስቲ እና በሳኡድ አረቢያ የንጉስ ፉአድ የነዳጅ እና ማእድን ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ናቸው በጥምረት ከብክለት የፀዳ አዲስ ኃይል ቆጣቢ አማራጭን ያስተዋወቁት፡፡

የተሰራው አዲስ መሳሪያም ባለፈው የታህሳስ ወር መግቢያ ከቤተሙከራ ወጥቶ በመስክ አገልግሎት ላይ ውሏል፡፡ በዚሁ ወቅት መሳሪያውን ለውጤት ካበቁት ከፍተኛ ተመራማሪዎች ኘሮፌሰር ሪቻርድ ዛሪ ግኝቱ በአየር ውስጥ የሚገኘውን ናይትሮጂን በመጠቀም አሞኒያን በዘላቂነት ማምረት ያስችላል ነው ያሉት፡፡ በተጨማሪም ለስነ ምህዳር ተስማሚ፣ ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ተመራጭ ርምጃ መሆኑንም ነው አፅንኦት ሰጥተው ያሰመሩበት፡፡

ተመራማሪዎቹ አዲሱን ወጪ ቆጣቢ ከብክለት የፀዳ መሳሪያ ለመንደፍ ሲያጠኑ የተለያዩ አካባቢያዊ ሁኔታዎችን ማለትም ርጥበትን፣ የነፋስ ፍጥነት፣ አሲዳማነት በአሞኒያ ምርት ላይ ተፅእኖ እንዳያሳድር ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረጋቸው ተብራርቷል፡፡

የስታንፎርድ የኬሚስትሪ ምርምር ሳይንቲስት ታያዎ ሶንግ አዲሱ መሳሪያ እና የማዳበሪያ ግብዓት የአመራረት ስልቱ ከበካይትነት “ካርቦን” ነፃ መሆኑን ነው ያረጋገጡት፡፡

አዲሱን መሳሪያ ለገበያ ዝግጁ እና ተደራሽ ለማድረግም ከሁለት እስከ ሦስት ዓመታት እንደሚጠይቅ ነው የንጉስ ፉአድ ፔትሮሊዬም እና ማእድን ዩኒቨርስቲ ተባባሪ ተመራማሪ ቻን ባሻ ባሺር  ያመላከቱት፡፡::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here