ከወሰንን ሁላችንም እንችላለን

0
123

በግሪክ አቴንስ ከተማ በተካሄዱ 42 ኪሎ ሜትር በሸፈኑት የማራቶን ውድድሮች ለ12ኛ ጊዜ ተሣትፈው ያጠናቀቁት የ88 ዓመቱ አዛውንት እድሜ ቁጥር ብቻ እንጂ ከምንም እንደማይገድብ አብነት መሆናቸውን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል፡፡

ግሪካዊው የ88 ዓመቱ ኘሉታርቾስ ፑርሊያካስ በያዝነው ዓመት ህዳር ወር መግቢያ በተካሄደው 41ኛው የማራቶን ውድድር ለ12ኛ ጊዜ ተሣትፎው ስድስት ሰዓት ከ31 ደቂቃ በሆነ ሰዓት ማጠናቀቅ ችለዋል፡፡ ባለፈው ዓመት የተካሄደውን ውድድር በስድስት ሰዓት ከ49 ደቂቃ ማጠናቀቃቸውን ያስታወሱት አዛውንቱ በዘንድሮው 18 ደቂቃ ማሻሻላቸው ከደስታ በላይ መሆኑን ነው ያበሰሩት፡፡

የማራቶን  ውድድሩ   ከ2500 ዓመታት በፊት ማራቶን በተሰኘው የጦርሜዳ የተገኘውን የድል ዜና የአቴናው መልእክተኛ ፊዲፒደስ ለህዝቡ ለማብሰር የሮጠበትን ርቀት እና አቅጣጫ  ተከትሎ በየዓመቱ የሚካሄድ መሆኑ ነው የተብራራው፡፡

የ88 ዓመቱ አዛውንት በየእለቱ ከሰኞ እስከ አርብ ከአራት እስከ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት እንዲሁም ቅዳሜ እና እሁድ  የመለማመጃ ርቀቱን በመጨመር እስከ 20 ኪሎ ሜትር በመሮጥ ልምምድ ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡

ልምምዳቸውን እንደማያቆራርጡ የተናገሩት አዛውንቱ እንደሚችሉ፣ ያሹትን ከመፈፀም ምንም እንደማይገድባቸው በውስጣቸው ካሰረፁት ስሜት ጋር ተዳምሮ ጠንካራነትን ብርታትን አጐናጽፏቸዋል፡፡

አዛውንቱ በየእለቱ ልምምድ ሲያደርጉ የሚመለከቷቸው  ሁሉ እድሜያቸውን ጠይቀዋቸው ሲነግሯቸው ለማመን እንደሚቸገሩ አስተውለዋል፡፡ መልሳቸውን በምንቸገረኝ በዝምታ አለማለፋቸውንም “ለምንድን ነው የማታምኑት? ሁላችንም እንችላለን! እስከፈለግን ድረስ” ሲሉ ፊት ለፊት እንደሚጋፈጧቸውም ነው ያሰመሩበት፡፡

በአኗኗር ዘይቤያቸው ወይም ልምዳቸው ሲጋራ እንደማያጨሱ፣ ከመጠን በላይ እንደማይጠጡ እና የተመጣጠነ ምግብ እንደሚያዘወትሩ አልሸሸጉም፤ ይህም ባሉበት የእድሜ ደረጃ የወሰኑትን፣ ያመኑበትን ለመፈፀም እንዳስቻላቸው ነው ያደማደሙት፡፡::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የታኅሳስ 21 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here