ከዋክብት የሚፈለፈሉበት  ፋብሪካ

0
13

የእግር ኳስ አካዳሚዎች ክለቦችን ወደ ግዙፍ ተቋማት የሚቀይሩ የለውጥ ማዕከላት ናቸው። የገቢ ምንጭ ከመሆናቸው ባሻገር የክለቡን ደም እና ስጋ የሆነውን ፍልስፍና በመጠበቅ የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ዘ አትሌቲክ ያስነብባል።

በዓለም ላይ ጥቂት አካዳሚዎች ባለተሰጥኦ ኮከቦችን በማፍራት እና ልዩ ፍልስፍናን በመከተል ይታወቃሉ። የባርሴሎናው ላ ማሲያ (La Masia) የኳስ ቁጥጥር (Tiki-Taka) ፍልስፍናን በማስርጽ ሊዮኔል ሜሲ፣ ዣቪ እና ኢኒዬስታን የመሳሰሉ  የእግር ኳስ ሊቆችን  አፍርቷል። የአያክስ አምስተርዳሙ ዲ ቱኮምስት ቶታል ፉትቦልን እያቀነቀነ እንደ ዮሃን ክራይፍ እና ዴኒስ ቤርካምፕ ያሉ በቴክኒክ የበለጸጉ ተጫዋቾችን ለዓለም አበርክቷል።

የስፖርቲንግ ሊዝበኑ አካዳሚ እንደ ክርስቲያኖ ሮናልዶ እና ሉዊስ ፊጎ ያሉ የባሎንዶር አሸናፊዎችን ሲያፈራ፣ የቤንፊካው ካምፐስ ደግሞ አካዳሚውን ወደ ትርፋማ የንግድ ድርጅት በመቀየር ባለፉት ዐስር ዓመታት ብቻ ከተጫዋች ሽያጭ ከአንድ ቢሊዮን ዩሮ በላይ ገቢ በማግኘት ከዘመናዊ እና ስኬታማ አካዳሚዎች ተርታ ተሰልፏል።

የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናልም የእነዚህን ውጤታማ አካዳሚዎች መንገድ እየተከተለ ይገኛል፡፡ በሰሜን ለንደን  የሚገኘው የሄል ኤንድ አካዳሚ የወደፊት ኮኮቦችን እየፈለፈለ ይገኛል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብቻ ቡካዮ ሳካን፣ ኤሚል ስሚዝ ሮውን እና ኤዲ ንኬቲያን ለዓለም እግር ኳስ አበረክቷል፡፡

በቅርብ ዓመታት ደግሞ ኤታን ንዋኔሪን፣ ማይልስ ሌዊስ-ስኬሊን፣ ማክስ ዳውማንን እና የመሳሰሉትን የመጪውን ዘመን ኮከቦች  ያበረከተው አካዳሚው አሁን ላይ በእግርኳሱ ዓለም እየተወደሰ ይገኛል፡፡ ሄል ኤንድ አካዳሚ በጥንቃቄ የተነደፈ፣ በላቀ ፍልስፍና የሚመራ እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ አንድ ግዙፍ የእግር ኳስ ፋብሪካ ነው።

የሄል ኤንድ አካዳሚ ስኬት በአንድ ጀምበር የተገነባ  አይደለም ይልቁንም፣ በጠራ ፍልስፍና እና ከዋናው ቡድን ጋር በተፈጠረ ጠንካራ ድልድይ የተገነባ የአንድ ታላቅ ሥርዓት ውጤት ነው ይለናል- ዘ አትሌቲክ። አካዳሚው የአርሰናልን ማንነት በደማቸው ያሰረጹ፣ በቴክኒክ የላቁ እና የአሸናፊነት ሰነ ልቦናን የተላበሱ ተጫዋቾችን ለመቅረጽ የተነደፈ ነው።

አካዳሚው ጥልቅ መሰረት ያለው እና  የማይናወጥ ፍልስፍናን የያዘ ጭምር ነው።  ታዳጊዎች የሄል ኤንድን  ደጃፍ ከረገጡበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ኤምሬትስ ስታዲየም  ድረስ የአርሰናልን ባህል እና ማንነት ከደማቸው ጋር እንዲዋሀድ  ይደረጋል። ከእግር ኳስ ስልጠናው ጎን ለጎን በትምህርታቸውም የላቁ እንዲሆኑ አካዳሚው ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣል።

ይህም ምናልባት በእግር ኳስ ካልተሳካላቸው ለቀጣይ ህይወታቸው እንዲዘጋጁ እና በሜዳ ላይ የሚያጋጥሙ ውስብስብ የታክቲክ ፈተናዎችን በቀላሉ እንዲረዱ ያግዛቸዋል፡፡ በተጨማሪም ተጫዋቾች የሚያጋጥማቸውን  ችግሮች በብቃት እንዲወጡ እና ከሽንፈት በኋላም በፍጥነት እንዲያገግሙ የሚያስችል የአዕምሮ ጥንካሬን ያላብሳቸዋል።

ሄል ኤንድ አካዳሚ ከግለሰብ ይልቅ የቡድን ስኬትን ቅድሚያ ያበረታታል። አካዳሚው አንድን ታዳጊ በስድስት ዓመቱ ተቀብሎ እስከ ዋናው ቡድን ድረስ የሚያደርስበት መንገድ ልክ እንደ አንድ  ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የተደራጀ ነው።

ገና በዘጠኝ ዓመት እድሜ ላይ ያሉ ታዳጊዎች የልምምድ ክፍለ ጊዜያቸው በቪዲዮ ይቀረጻል። ከዚያም አሰልጣኞቻቸው የተቀረጸውን ምስል በመተንተን ጠንካራ እና ደካማ ጎናቸውን ያሳዩዋቸዋል። በተጨማሪም በየስፍራቸው የሚጫወት የዋናው ቡድን ተጫዋችም አማካሪ ሆነው ይመደቡላቸዋል፡፡ ይህም ስህተታቸውን በፍጥነት እንዲያርሙ እና የጨዋታ ግንዛቤያቸውን እንዲያሳድጉ ትልቅ ሚና ይጫወታል።

ሥራ አስኪያጁ ፐር ሜርተሳከር እንደተናገረው የሄል ኤንድ አካዳሚ ግብ  ለሚኬል አርቴታ የሚሆኑ እና ከክለቡ የጨዋታ ዘይቤ ጋር የሚስማሙ አሸናፊዎችን መፍጠር ነው። ይህ ሁሉ ፍሬ የሚያፈራው ግን  የዋናው ቡድን አሰልጣኝ በታዳጊዎቹ ላይ እምነት ሲኖረው ብቻ ነው።

በአሁኑ ወቅት በአካዳሚው ውስጥ የሚገኙ እና ወደፊት የአርሰናልን እና የእንግሊዝን እግር ኳስ ይቆጣጠራሉ ተብለው የሚጠበቁ በርካታ ታዳጊዎች አሉ። ገና በ15 ዓመቱ “ቀጣዩ ካካ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ማክስ ዳውማን  አሁን ላይ የፕሪሚየር ሊጉ መነጋገሪያ የሆነ ባለተሰጥኦ ነው።

ታዳጊው በአውሮፓ የወጣቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ታሪክ በእድሜ ትንሹ ግብ አስቆጣሪ በመሆን አዲስ ክብረወሰን ሰብሯል። በቅርቡ  በኤምሬትስ አርሰናል ኒውካስትል ዩናይትድን ባሸነፈበት ጨዋታም በፕሪሚየር ሊጉ መሰለፉ አይዘነጋም፤ ለአርሰናልም የፍጽም ቅጣት ምት ማስገኘቱ የሚታወስ ነው።

ሌላው “የሳሊባ አልጋ ወራሽ” ተብሎ እየተወደሰ ያለው የ15 ዓመቱ የመሃል ተከላካይ ማርሊ ሳልሞን ነው፡፡ በእድሜው ከሚጠበቀው በላይ የአካል ብቃት እና የመከላከል ብስለት አለው ሲሉም ብዙዎች  ያሞካሹታል። ሳልሞን ከእድሜው በሁለት ዓመት ከፍ ብሎ ከ18 ዓመት በታች ቡድን ጋር በቋሚነት መጫወቱ ልዩ ተሰጥኦ እንዳለው ያረጋግጣል። በ2024/25 የውድድር ዘመን ብቻ ለ18 ዓመት በታች ቡድን 17 ግቦችን ያስቆጠረው የ17 ዓመቱ ዳን ኬሲም ሌላኛው በመጪው ዘመን ተስፋ የተጣለበት የሄል ኤንደ አካዳሚ ፍሬ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት 40 በመቶ የሚሆነው የአርሰናል ዋና ቡድን ስብስብ ከአካዳሚው የተገኙ መሆናቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ ይህም ክለቡን ከከፍተኛ ወጪ አድኖታል። የሄል ኤንድ አካዳሚ ለአርሰናል የሚያበረክተው አስተዋጽኦ በሜዳ ብቻ የተወሰነ አይደለም። አካዳሚው ለክለቡ ከፍተኛ የገቢ ምንጭም ሆኗል። አካዳሚው ፍሬዎቹን በመሸጥ ረብጣ ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝቷል፡፡ ከአሌክስ ኢዎቢ 35 ሚሊዮን ፓውንድ፣ ከጆ ዊሎክ 20 ሚሊዮን ፓውንድ እና ከፎላሪን ባሎጉን 40 ሚሊዮን ፓውንድ  ገንዘብ ወደ ካዝናው አስገብቷል፡፡

ይሁን እንጂ ክለቡ የአካዳሚ ፍሬዎቹን በቤቱ ለማቆየት የመሰለፍ ዕድል እና ተስፋ መስጠት ይኖርበታል። እንደ ቺየዶ ኦቢ-ማርቲን ያሉ ድንቅ ታዳጊዎችን ከጉሮሮው እንዳይነጠቅ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅበታል፤ ተጫዋቾች በአካል እና በአዕምሮ እንዳይጎዱም ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላበት አያያዝ ያስፈልጋቸዋል በማለት ዘ አትሌቲክ  ትንታኔውን ይቋጫል።

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የጳጉሜ 3 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here