ከዳንኪራዉ መልስ

0
165

ባለፉት 64 ዓመታት በአውሮፓ ዋንጫ ታሪክ በርካታ ያልተጠበቁ ድራማዊ ሁነቶች እና ክስተቶች ተፈጥረው አልፈዋል። ለዋንጫ የተገመቱት ብዙ ርቀት ሳይጓዙ ያልተጠበቁት ቡድኖች በመድረኩ ነግሰው ታይተዋል። ለአብነት የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት እ.አ.አ በ1964፣ ስፔን በ1964፣ ጣሊያን በ1968፣ የቀድሞዋ ምስራቅ ጀርመን በ1972 እና 1980፣ እንዲሁም ኔዘርላንድስ በ1988 ሳይጠበቁ የመድረኩን ዋንጫ ያነሱ ሀገራት ናቸው።

በ1992 እ.አ.አ ዴንማርካውያን የፈፀሙት ገድል ግን በአውሮፓ እግር ኳስ የተለየ መሆኑን ዘአትሌቲክ አስነብቧል። የዴንማርክ ብሄራዊ ቡድን ልክ እንደ ታላላቆቹ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ እና እንግሊዝ በርካታ ዝነኛ እና ስመ ጥር ተጫዋቾች አልነበረውም። ይሁን እንጂ የመድረኩ ምርጥ እንደነበር ታሪክ ያወሳል።

የአውሮፓ ዋንጫ ሲታወስ ሁሌም ተረት የሚመስለው ታሪክ ከዚህ ይጀምራል። እ.አ.አ በ1992 በስዊድን በተደረገው የአውሮፓ ዋንጫ ስምንት ሀገራት ብቻ ነበር የተሳተፉት። አስተናጋጇ ሀገር ስዊድን፣ ዴንማርክ፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ ኔዘርላንድስ፣ ጀርመን፣ ስኮትላንድ እና የኮመን ዌልዝ ነፃ ግዛቶች ናቸው በውድድሩ የተካፈሉት። ቀደም ብሎ 33 ሀገራት በስምንት ምድብ ተከፍለው ማጣሪያቸውን ያከናወኑ ሲሆን የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ፣ ዴንማርክ፣ ሰሜን አየርላንድ፣ ኦስትሪያ እና የፍርኦ ደሴቶች በምድብ አራት  ማጣሪያቸውን ያከናወኑ ሀገራት ናቸው።

ምድቡንም የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ በበላይነት በማጠናቀቅ ወደ ስዊድን የምትበርበትን ትኬት መቁረጥ ችላለች።  ዴንማርክ ሁለተኛ ደረጃ ስትይዝ፣ ሰሜን አየርላንድ፣ ኦስትሪያ እና የፍርኦ ደሴቶች በቅደም ተከተል ተከታዩን ደረጃ ይዝው ምድቡን አጠናቀዋል። ከየምድቡ በበላይነት ያጠናቀቁ ሀገራት ብቻ በአውሮፓ ዋንጫ የሚሳተፉ በመሆኑ ሌሎች ሀገራት ውድድሩን በቴሌቭዥን መስኮት ለመከታተል የውድድሩን መጀመር መጠባበቅ ይዘዋል።

የአውሮፓ ዋንጫው ሊጀመር አስር ቀናት ሲቀሩት ግን የዓለምን ትኩርት የሚስብ ዜና ከወደ ዩጎዝላቪያ ተሰማ። በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ የርስ በርስ ጦርነት መጀመሩን የመገናኛ አውታሮች ይፋ አደረጉ። ይህ ዜና ምድባቸውን በበላይነት ላጠናቀቁት እና የአውሮፓ ዋንጫውን መጀመር በጉጉት ለሚጠባበቁት የዩጎዝላቪያ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች አሳዛኝ ሲሆን ዴንማርካውያንም ቢሆኑ የተደበላለቀ ስሜት ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ የበላይ ጠባቂ ፊፋ አማካኝነት ዩጎዝላቪያ ከአውሮፓ ዋንጫው እንድትታገድ አደረገ። በምትኩም በምድቡ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችው ዴንማርክ ጥሪ ቀረበላት። የተበታተነው የዴንማርክ ብሄራዊ ቡድን በአጭር ጊዜ ውስጥ መሰባሰብ ይችላል ወይ? የሚለው በወቅቱ የብዙዎች የዴንማርካውያን ጥያቄ ነበር።

ምክንያቱ ደግሞ አብዛኞቹ የብሄራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች ከማጣሪያ ጨዋታ በኋላ በተለያዩ የባህር፣ የውቅያኖስ ዳርቻዎች እና ደሴቶች ላይ እየተዝናኑ እና የእረፍት ጊዜያቸውን እያሳለፉ ስለነበር ነው። ዴንማርክ የተበታተነውን የብሄራዊ ቡድን ስብስብ ለማሰባሰብ ጥሪ ስታስተላልፍ በርካቶች የእናት ሀገራቸውን ጥሪ ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው ዳንኪራውን አስበልጠው እንደቀሩ መረጃዎች አመልክተዋል።

የቀድሞው የባርሴሎና እና የሪያል ማድሪዱ ኮከብ ሚካኤል ላውድሮፕ በወቅቱ ከመዝናኛው ቦታ አልወጣም በማለት ወደ ስዊድን አብሮ ካልተጓዙት መካከል ይጠቀሳል። ወንድሙ በሪያን ላውደሮፕ ግን ብሄራዊ ቡድኑን ተቀላቅሏል:: የዴንማርክ ብሄራዊ ቡድን በውድድሩ ለመታየት እና ለመካፈል በቂ ቅድመ ዝግጅት ሳያደርግ ከመዝናኛ ቦታ የተገኙትን ተጫዋቾች ሰብስቦ ወደ ስዊድን ተጉዟል።

ከስብስቡ ውስጥም 20 ተጫዋቾች ከሀገር ውስጥ ሊግ የተመረጡ ነበሩ። የመድረኩ ውድድር ሲጀመር ምድብ አንድ ላይ ከአስተናጋጇ ስዊድን፣ ፈረንሳይ እና እንግሊዝ ጋር የተመደበችው ዴንማርክ ምድቡ የሞት ምድብ በመሆኑ አበቃላት፣ ብዙ ግቦችም ይቆጠሩባታል ተብሎ እንደነበር መረጃው ያወሳል።

የመጀመሪያውን የምድብ ጨዋታም ለዋንጫ ከሚጠበቁት ቀዳሚ ቡድኖች ውስጥ አንዷ ከሆነችው ከእንግሊዝ ጋር ነበር የተጫወተችው። የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን ክሪስ ውድን፣ ማርቲን ኪዊንን፣ ጋሪ ሊንከርን እና አለን ሸረርን የመሳሰሉትን ኮከቦች ይዟል። በእነዚህ ኮከቦች ያለተበገረችው ዴንማርክ ጨዋታውን ያለምንም ግብ በአቻ ውጤት አጠናቃለች:: የዴንማርክ ብሄራዊ ቡድን በ1980ዎች ወርቃማ የሚባለው ትውልድ የነበራቸው ሲሆን በ1984ቱ የአውሮፓ ዋንጫ እንግሊዝን አንድ ለባዶ በማሸነፍ ከውድድሩ ውጪ ማድረጋቸው በታሪክ ማህደራቸው ተቀምጧል።

ፒተር ሽማይክልን፣ ሄነሪክ አንደርሰንን፣ ሄነሪክ ላርሰንን እና ብሪያን ላውድሮፕን የያዘው የዴንማርክ ብሄራዊ ቡድን ሁለተኛውን ጨዋታ ያደረገው ከሌላኛው የመድረኩ ምርጥ ቡድን ጋር ነው። ሎረንት ብላክን እና ኤሪክ ካንቶናን የመሳሰሉትን ተጫዋቾች የያዘው የፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን በወቅቱ አሰልጣኝ ሚሼል ፕላቲኒ እየተመራ ነው ሁለተኛውን የምድብ መርሀግብር ከዴንማርክ ጋር ያደረገው።

በጨዋታውም ዴንማርክ ሁለት ለአንድ ማሸነፍ ችላለች።የዴንማርክ ብሄራዊ ቡድን ተጋድሎ ብዙዎችን አስደንቋል። በመጨረሻው የምድብ ጨዋታ ግን በአስተናጋጇ ሀገር ስዊድን አንድ ለባዶ ተሸንፋለች። ምድቡንም ስዊድን በአምስት ነጥብ በበላይነት በማጠናቀቅ ሩብ ፍጻሜ ስትቀላቀል፣ ዴንማርክ ደግሞ በሦስት ነጥብ ሁለተኛ በመሆን ሳትጠበቅ ወደ ቀጣዩ ዙር ተሸጋግራለች።

በብዙ ለዋንጫ የተገመቱት ፈረንሳይ እና እንግሊዝ ሩቅ ቢጠበቁም ከመንገድ ቀርተዋል። ከሌላኛው ምድብ ደግሞ ኔዘርላንድስ እና ጀርመን ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቅለዋል። ስኮትላንድ እና የኮመን ዌልዝ ነፃ ግዛቶች ከምድቡ የተሰናበቱ ሀገራት ናቸው። የዴንማርክ ብሄራዊ ቡድን በመድረኩ ከወትሮው የተለየ የጨዋታ ታክቲክ፣ እና ፍልስፍና ይዞ አልቀረበም ነበር።

ይልቁንስ ታሪክ የመሥራት ከፍተኛ ጉጉት፣ ተነሳሽነት እና ጠንካራ የአሸናፊነት ስነ ልቦና ብቻ ታጥቆ ነበር ወደ ሜዳ የገባው። በሁሉም ጨዋታዎች 5-3-2 የአሰላለፍ ስልትን ተግባራዊ ማድረጉን መረጃዎች ያሳያሉ። የዴንማርክ ብሄራዊ ቡድን በሩብ ፍጻሜው የወርቃማ ትውልድ ባለቤት ከሆነችው ኔዘርላንድስ ጋር ነበር የተገናኘው።

ይህም ለዴንማርካውያን ሌላኛው ራስ ምታት ነበር። ብርቱካናማዎቹ ሮናልድ ኩማን፣ ፍራንክ ዲቦር፣ ፍራንክ ራይካርድ፣ ዴኒስ ቤርካምፕ፣ ሮድ ጉሌት እና ማርኮ ቫባስተንን በስብስባቸው አካተዋል። መደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜውም በሁለት አቻ ውጤት ተጠናቋል። ወደ መለያ ምት ያመራው ጨዋታም በዴንማርክ አምስት ለአራት አሸናፊነት ተጠናቋል። ይህ ለዴንማርክ ብሄራዊ ቡድን ታምር ሲሆን በሪኒስ ሚሸልስ ለሚመራው የኔዘርላንድስ ብሄራዊ ቡድን ግን ያልተጠበቀ ዱብዳ ነበር።

አሁን የዴንማርክ ብሄራዊ ቡድን የሠርክ ገድሉን በደማቁ ሊጽፍ የ90 ደቂቃ የሜዳ ላይ ፍልሚያ ብቻ ይቀረዋል። በኡሌቭ ጎተንበርግ ስቴዲየም ሰማይ ስር ታምር እንደሚሠራ ደጋፊዎቹም እምነትን አሳድረዋል።

ጀርመንን እና ስዊድንን ያገናኝው ሌላኛወ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ደግሞ በጀርመን ሦስት ለሁለት አሸናፊነት ተጠናቋል። ተጠባቂው የፍፃሜ ጨዋታም በዴንማርክ እና ጀርመን መካከል ሆኗል። ሚሊዮኖች በቀጥታ የቴሌቭዥን መስኮት የተከታተሉት ይህ የፍፃሜ ጨዋታ ውጤቱ ብዙዎች እንደ ገመቱት አልነበረም።

ታላላቅ የእግር ኳስ ኮከቦችን የያዘው የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ሜዳ ላይ እንደ ተርብ ለሚናደፉት የዴንማርክ ተጫዋቾች እጅ ሰጠ። ሁለት ግቦችም ተቆጠሩበት፤ የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች የረባ ኢላማቸውን የጠበቁ የግብ ሙከራዎች እንኳ ሳያደርጉ ከሜዳ ወጡ። ዴንማርካውያን ሁሌም እንደ አዲስ የሚያወሩለት፣ የሚኮሩበት ጀብድም በዚህ መንገድ ተሠራ።

እነዚያ ከየመዝናኛ ቦታው ተለምነው እና ተለቃቅመው የመጡት ተጫዋቾች የእግር ኳስ አባት የሚባሉትን ታላላቅ ሀገሮችን በመጣል የመድረኩን ዋንጫ ማንሳታቸው ዓለምን ጉድ አሰኝቷል። ይህ ታሪክ ዛሬም ድረስ በየአራት ዓመቱ የአውሮፓ ዋንጫ ድግስ ሲዘጋጅ ልክ እንደ ተረት በእግር ኳስ ቤተሰቡ ዘንድ ይወራል። የጋዜጦች እና የመጽሔቶች ወግ ማድመቂያም ይሆናል።

ዴንማርክ በ2024ቱ በጀርመን የአውሮፓ ዋንጫ በምድብ ሦስት ከእንግሊዝ፣ ከስሎቫኒያ እና ከሰርቢያ ጋር የምድብ መርሀ ግብሯን እያከናወነች ነው:: የመጀመሪያውን የምድብ ጨዋታም ከስሎቫኒያ ጋር በማድረግ ነጥብ መጋራቷ የሚታወስ ነው:: ክርስቲያን ኤሪክሰንን፣ አንድሪስ ክሪስቲሰንን፣ ራስመስ ሆይሉንድን፣ ኢምሊ ሆጅበርግን፣ ካስፐር ሽማይክልን እና ዩአኪም አንደርስንን የያዘው ስብስብ የት ድረስ ይጓዛል? የሚለውን አብረን የምናየው የሆናል::

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር ሰኔ 17 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here