ከገቢም በላይ…

0
82

አረንጓዴ ልማት ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚሠራው ኤደን ግሪን (www.edengreen.com) የተሰኘ ድረ ገጽ እንዳስነበበው የከተማ ግብርና በውስን መሬት ከፍተኛ ተጠቃሚነትን በማስገኘት ፈጣን ለውጥ እያስመዘገበ ያለ ዘርፍ ነው። ለዜጎች ገቢ ከማስገኘቱም በላይ የአየር ንብረት መዛባትን ለማስተካከል ፍቱን መድኃኒት መሆኑን ነው።

ድረ ገጹ እንዳስነበበው አርጀንቲና፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳ፣ ቻይና፣ ኮሎምቢያ እና ጋና በከተማ ግብርና በዓለም አቀፍ ደረጃ በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ሀገራት ናቸው።

ከዚህ ጋር በተያያዘ በቅርብ ጊዜ እምርታ እያሳዩ ከሚገኙ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያን ጠቅሷታል። ሀገራችን ሁሉንም አይነት የአየር ንብረት ባለ ጸጋ እና የውኃ ማማ መሆኗ ዘርፉን ለማሳደግ መልካም አጋጣሚዎች ናቸው።

በኢትዮጵያ የከተማ ግብርና እየተስፋፋባቸው ከሚገኙ ከተሞች መካከል ባሕር ዳር ተጠቃሽ ናት። በባሕር ዳር ከተማ አስዳደር ግብርና መምሪያ የአትክልት እና ፍራፍሬ ባለሙያ ሞላልኝ መንግሥቱ ያረጋገጡልንም ይህን እውነታ ነው። ባለሙያው እንደነገሩን ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ አካባቢዎች በዘርፉ አገልግለዋል። “በሥራ ዓለም ካየኋቸው ሁሉ ለከተማ ግብርና እንደ ባሕር ዳር ከተማ እጅግ የተመቼ የለም” ይላሉ። ለዚህ ደግሞ ከምቹ የአየር ንብረት በተጨማሪ የተትረፈረፈ የውኃ ሀብት መኖሩን ነው ያነሱት።

አቶ ሞላልኝ እንዳሉት የከተማ ግብርና ለበርካታ ዜጎችም የሥራ ዕድልን የፈጠረ ነው። ከእነዚህ መካከል ደግሞ አቶ በሪሁን ማሩ አንዱ ናቸው። ነዋሪው እንዳሉት በሦስት ሄክታር መሬት ቅመማ ቅመምን ጨምሮ የሀበሻ ጎመን፣ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ጥቅል ጎመን እና በቆሎን በማምረት ኑሯቸውም በተሻለ መንገድ መምራት ችለዋል፡፡

የአትክልት እና ፍራፍሬ ባለሙያው አቶ ሞላልኝ እንዳብራሩት በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ብቻ በበጀት ዓመቱ 635 ሄክታር መሬት በአትክልት እና ፍራፍሬ ለምቷል። ፓፓያ፣ አቮካዶ፣ ቀይ ሥር፣ ቆስጣ፣ ጥቅል ጎመን፣ ቲማቲም፣ የሀበሻ ጎመን፣  ዘይቱኒ፣ ማንጎ እና ሀባብ ዋናዎቹ በመልማት ላይ የሚገኙ አትክልት እና ፍራፍሬ ናቸው፡፡ የአናናስ ምርት ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተለመደ እና እየተስፋፋ የሚገኝ መሆኑን ባለሙያው ተናግረዋል። ዘርፉ ከአምስት ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡

ኅብረተሰቡ ዘመናዊ ቴክኖሎጅን በመጠቀም የከተማ ግብርናን ልምድ አድርጎ እንዲሠራ ባለሙያዎች ተመድበው ግንዛቤ ፈጠራ እና ድጋፍ መደረጉን አቶ ሞላልኝ አክለዋል። ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

በባሕር ዳር ከተማ በከተማ ግብርና የተሻለ ውጤት የተመዘገበው በተለይ በአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ነው። በዚህ ተጠቃሽ ከሆኑት ተቋማት መካከል አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) አንዱ ነው። በኮርፖሬሽኑ የስምሪት እና ጠቅላላ አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ውብሸት ኃይሌ አሚኮ ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን የሚለውን መሪ ሐሳቡን (ሞቶውን) ከዘገባ በተጨማሪ በከተማ ግብርናም በተግባር ያረጋገጠ ነው ብለዋል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ግቢ በአትክልት እና ፍራፍሬ (ማንጎ፣ ፓፓያ፣ ዘይቱን፣ ሃብ ሃብ፣ ጎመን፣ ካሮት፣ ቲማቲም፣ ቆስጣ፣ …) ዛፎች የተከበበ እና አረንጓዴ ፀዳል የተላበሰ ነው፤ ይህ መሆኑ ታዲያ ምቹ የሥራ አካባቢ እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ አቶ ውብሸት ደግሞ በግቢው ውስጥ ያለው የከተማ ግብርና “ከግቢው አልፎ ለማኅበረሰቡ አርዓያ ሆኗል” ነው ያሉት፡፡ ለዚህ ማሳያ ያነሱት ደግሞ በርካታ ኮርፖሬሽኑ ሠራተኞች የከተማ ግብርናን በመኖሪያ አካባቢያቸው እያስፋፉ መሆናቸውን ነው፡፡

የግቢው አትክልትና ፍራፍሬዎች በቶሎ የሚደርሱ መሆናቸውም ለየት እንደሚያደርገው አቶ ውብሸት ተናግረዋል፤ በነሐሴ ወር 2016 ዓ.ም የተተከለ ፓፓያ በአምስት ወር ጊዜ ውስጥ ፍሬ ማፍራቱን ልብ ይሏል፡፡ ይህ መሆኑ ታዲያ ሌላውን በማነሳሳት ዘርፉ እንዲሰፋ እያደረገ ነው፡፡ “ለኅብረተሰብ ለውጥ መትጋት ማለትም ይህ ነው” ብለዋል አቶ ውብሸት፡፡

እንደ አቶ ውብሸት ማብራሪያ የአሚኮ ግቢ የከተማ ግብርና ውጤታማ እንዲሆን በቂ ውኃ መኖር እና ኃላፊዎችም አስፈላጊ ግብዓቶችን ለማሟላት ቀና መሆን መልካም አጋጣሚዎች ናቸው፤ ከዚህ በተጨማሪም ተገቢ ክትትል እና እንክብካቤ ይደረጋል፡፡

በባሕር ዳር ከተማ የሚገኙ መሥሪያ ቤቶች ሰፊ ቦታን ያካለሉ ናቸው፤ ይሁን እንጂ ብዙዎቹ ከቢሮነት እና አጥሮ ከመቀመጥ በዘለለ ሌላ ተግባር ሲከውኑበት አይስተዋልም፡፡ በመሆኑም የአሚኮን ተሞክሮ በመውሰድ ለከተማ ግብርና ትኩረት ሰጥተው ቢሠሩ ሲሉ ነው አቶ ውብሸት መልዕክት ያስተላለፉት፡፡ የክልል ምክር ቤት አባላትን ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና ሌሎችም የአሚኮን የከተማ ግብርና እንቅስቃሴ በመጎብኘት ለኮርፖሬሽኑ አድናቆት መቸራቸውን አስታውሰዋል፡፡

ሌላው የከተማ ግብርና እንዲስፋፋ በአርዓያነት ከሚጠቀሱት ድርጅቶች መካከል አመልድ ኢትዮጵያ አንዱ  ነው፤ አቶ ዋቢ ተስፋዬ ደግሞ በድርጅቱ የአትክልት እና ፍራፍሬ ባለሙያ ናቸው። ድርጅቱ ከከተማ ውጪ ትኩረቱን አድርጎ ቢሠራም የከተማ ግብርናን ለማስፋፋትም አስተዋጽኦ እያደረገ ነው። ለአብነትም በባሕር ዳር እና አካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎች የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞችን በተመጣጣኝ ዋጋ ገዝተው ተጠቃሚ መሆናቸውን አንስተዋል።

የከተማ ግብርና መስፋፋት ዘርፈ ብዙ ጥቅም አለው የሚሉት አቶ ዋቢ “አረንጓዴነት በራሱ ውበት ነው፤ ከዚያ አለፍ ሲልም ጤናማ የአየር ንብረት እንዲኖር በማድረግ ለጤናማ ሕይወት መሠረት ነው” ብለዋል። እንደሚታወቀው አረንጓዴ ዕፅዋት ምግባቸውን ለማዘጋጀት የሚጠቀሙት (ወደ ውስጥ የሚያስገቡት) የሰው ልጅ በትንፈሳ የሚያስወጣውን አየር (CO2) ነው። እነዚህ ዕፅዋት ከሌሉ ታዲያ የዚህ አየር ክምችት የአየር ንብረት እንዲዛባ ያደርጋል።

በተቃራኒው አረንጓዴ ዕፅዋት ምግባቸውን ሲያዘጋጁ ወደ ውስጥ የምናስገባውን አየር (ኦክስጂን) ይለቃሉ። ይህ ደግሞ ጤናማ የአየር ንብረት እንዲኖር ያደርጋል። የሁለቱ ምጥጥን (የሰው እና ዕፅዋት ቁጥር) ታዲያ የከባቢ አየርን ጤናማነት ይጠብቃል፤ በአጠቃላይ የከተማ ግብርና መስፋፋት ከገቢ በተጨማሪ ጤናማ የአየር ንብረት እንዲኖር ያደርጋሉ።

ከባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው በበጀት ዓመቱ 635 ሄክታር መሬት በአትክልት እና ፍራፍሬ ለምቷል፡፡

 (ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር የካቲት 1724 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here