በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከሚመረተው ሰብል ውስጥ በአማካኝ እስከ 30 በመቶ በዋናነት የሚባክነው በድህረ- ምርት ወቅት ሙያዊ ምክረ ሐሳቦችን ባልተከተሉ የአሠራሮች ጉድለት መሆኑን በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት (FAO) እ.አ.አ በ2023 ይፋ ባደረገዉ መረጃ አመላክቷል። ኢትዮጵያ የምርት መጠኗን ለመጨመር የምታደርገውን ጥረት ያህል የድህረ-ምርት ብክነቱን ለመቀነስ መሥራት ካልቻለች የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ አዳጋች እንደሚያደርግባት መረጃው ጠቁሟል። በመሆኑም ድህረ-ምርት ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ መረጃው አፅንኦት ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ግብርና ሚኒሥቴር መረጃ እንደሚያመለክተው ደግሞ በኢትዮጵያ በድህረ-ምርት (Post-harvest) ወቅት የሚባክነው የምርት መጠን እንደ ሰብሉ ዓይነት ቢለያይም በአማካይ ከ20 እስከ 30 በመቶ የሚሆነው ከማሳ እስከ ሸማች ባለው ሂደት ውስጥ ነው። እንደ በቆሎ፣ ስንዴ፣ ጤፍ እና ማሽላ ባሉት ላይ የሚደርሰው ብክነት ከ15 እስከ 25 በመቶ ይገመታል። በተለይም እንደ በቆሎ ያሉ ሰብሎች በአግባቡ ካልተከማቹ ለተባይ ጥቃት ስለሚጋለጡ ብክነቱ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል መረጃው አመላክቷል።
አትክልት እና ፍራፍሬም በቀላሉ የሚበላሹ ምርቶች በመሆናቸው ብክነቱ እጅግ ከፍተኛ ነው። በዚህ ዘርፍ ያለው ብክነት ከ40 እስከ 50 በመቶ ፤ አንዳንዴም ከዚያ በላይ እንደሚደርስ መረጃው ጠቁሟል::
በመሆኑም የ2017/18 የመኸሩ ምርት ብክነት እንዳይደርስበት በአማራ ክልል በተለያዩ ዞኖች የሰብል ስብሰባ ሥራ በጥንቃቄ እየተከናወነ መሆኑ ተጠቁሟል:: በክልሉ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ደጀኔ ሲሳይ እንደገለጹት በ2017/18 የምርት ዘመን በሰብል ከተሸፈነው 552 ሺህ 11 ሄክታር ማሳ ላይ 19 ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ እየተሠራ መሆኑን ለበኵር ጋዜጣ ተናግረዋል።
የዘንድሮው ሰብል ጥሩ ቁመና እንደነበረው የገለፁት ምክትል ኃላፊው፤ ለዚህም ከመኸር እርሻ የሚጠበቀውን ምርት በጥራት እና በመጠን በታቀደው ልክ ለማግኘት ባለፉት ጊዜያት አረምን በወቅቱ ተከታትሎ የማረም፣ ማሳን ከተባይ የማጽዳት፣ ፀረ ተባይ ኬሚካል የመርጨት… ሥራዎች መከናወናቸውን አስታውሰዋል:: በአሁኑ ወቅት ደግሞ ሰብሉ ለአጨዳ በመድረሱ አርሶ አደሩ የቤተሰቡን ጉልበት፣ የቀን ሠራተኛ እንዲሁም ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅሞ በፍጥነት እየሰበሰበ ነው።
በተለይ በቆሎ፣ ማሽላ፣ አኩሪ አተር እና ሌሎችም ሰብሎች ጥራታቸው ተጠብቆ እንዲሰበሰብ ለአርሶ አደሩ በየደረጃው ግንዛቤ እየተፈጠረ መሆኑን ምክትል ኃላፊው ጠቁመዋል። በተለይ ቆላማው አካባቢ ቀድመው የደረሱ እንደ ጤፍ እና ሰሊጥ ተሰብስበዋል። በሰብል አጨዳ፣ በመከመር እና በውቂያ ወቅት ሊደርስ የሚችልን የምርት ብክነት በመቀነስ በዞኑ የታቀደው ምርት እንዲሳካ በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት እና የግብርና ባለሙያዎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም አቶ ደጀኔ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አዲሱ ወልዴ ለበኵር እንደተናገሩት በ2017/18 የምርት ዘመን 120 ሺህ 638 ሄክታር መሬት በተለያዩ የሰብል አይነቶች ተሸፍኗል። ከዚህም ከአምስት ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም (በክላስተር) የተዘራ ነው። በምርት ዘመኑ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱንም ገልጸዋል። የታለመው ዕቅድ እንዲሳካም በሰብል አሰባሰብ ላይ ጥንቃቄ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል:: ምርታማነትን ከማሳደግ አኳያም እየተሠራ ያለው ሥራ የድህረ- ምርት አያያዝ ነው ብለዋል። ከእነዚህ ተግባራት መካከልም ምርቱን ነቀዝ እንዳይበላው ለመከላከል ዘመናዊ የምርት ማከማቻ ጎተራ ማዘጋጀት፣ በዘመናዊ መንገድ ምርትን መሰብሰብ፣ በማጓጓዝ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ እና በወቅቱ መውቃት ተጠቃሾች ናቸው።
ዘገባው እስከተጠናቀረበት ኅዳር 24 ቀን 2018 ዓ.ም በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከ85 በመቶ በላይ ምርት መሰብሰቡንም ተናግረዋል። ስንዴ፣ ማሽላ፣ ጤፍ፣ እንቁ ዳጉሳ፣ ማሾ፣ ባቄላ እና አተር የተሰበሰቡ ሰብሎች ናቸው።
አርሶ አደሮቹ ቀሪ ያልታጨዱ ሰብሎች ለአጨዳ እንደደረሱ በወቅቱ በመሰብሰብ በደረቅ እና በንፁህ ቦታ ማስቀመጥ፣ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እና መሰል ችግሮች ምርቱ እንዳይባክን እንዲሁም እንዳይበላሽ ሙሉ አቅማቸውን በመጠቀም ወቅቶ ወደ ቤት ማስገባት እንዳለባቸው አቶ አዲሱ አሳስበዋል።
በተመሳሳይ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደርም የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ እና በጥንቃቄ በመሰብሰብ የምርት ብክነትን ለመቀነስ እየተሠራ መሆኑን አስታውቋል። በ2017/18 የምርት ዘመን ከ408 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመኸር ሰብል መሸፈኑን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ አዲሱ ስማቸው ለበኵር ተናግረዋል። በዚህ ወቅትም የሰብል አሰባሰብ ሥራ በተቀናጀ መንገድ በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሰፋፊ መሬት ላይ በዘር የተሸፈኑ ማሳዎች በኮምባይነር የታገዘ የሰብል ስብሰባ እየተከናወነ ነው። እስካሁንም በሰብል ከተሸፈነው 408 ሺህ ሄክታር ማሳ ውስጥ 42 በመቶ ሰብል ተሰብስቧል። የምርት ብክነት እንዳይከሰትም ለአርሶ አደሩ በተለያየ መልኩ ግንዛቤ እየተፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል።
የደረሱ ሰብሎችን ለመሰብሰብ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ሥራ መገባቱን የጠቁሙት ምክትል ኃላፊው ኮምባይነሮችን እና የሰብል መፈልፈያ ማሽኖችን የማቅረብ ተግባር እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።
የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ እና በአግባቡ በመሰብሰብ የምርት ብክነትን ለመቀነስ እየተሠራ ስለመሆኑም የተናገሩት አቶ አዲሱ አርሶ አደሩም ሰብሎን በወንፈል (በደቦ) እየሰበሰበ ነው ብለዋል። አርሶ አደሮችም የደረሱ ሰብሎችን የምርት ብክነት እንዳይኖር በፍጥነት እና በጥንቃቄ የመሰብሰቡን ሥራ በትኩረት እንዲያከናውኑ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የግብርና ባለሙያዎችን ሙያዊ ምክር እና የቆየ ልምዳቸውን መሰረት አድርገው የደረሱ ሰብሎችን እየሰበሰቡ መሆኑን የምዕራብ ጎጃም ዞን ጃቢ ጠህናን ወረዳ አርባዕቱ እንስሳ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር መስፍን ተሰማ በስልክ ለበኩር ገልፀዋል። በዚህ ዓመት ሰብሉ በቂ ዝናብ በማግኘቱ የሚጠብቁትን ያህል ምርት ሊያገኙ እንደሚችሉ ተስፋ አድርገዋል። በምርት ዘመኑ ሦስት ሄክታር መሬታቸውን በቆሎ፣ ጤፍ፣ ዳጉሳ፣ በርበሬ እና በሌሎች ሰብሎች ሸፍነዋል።
አርሶ አደሩ እንደተናገሩት “ከአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ” ነውና በግማሽ ሄክታር መሬት የዘሩትን የጤፍ ሰብል በጋራ/በደቦ/ አጭደው በብልሽት የምርት ብክነት እንዳይከሰት ከፍ ባለ ቦታ እና በጥንቃቄ ከምረዋል። በቀጣይ ቀናትም የደረሱ ቀሪ ሰብሎችን ለመሰብሰብ ተዘጋጅተዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በወቅታዊ የግብርና እና ገጠር ልማት ሥራዎች አፈጻጸምን እንዲሁም የቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎች በተመለከተ ኅዳር 21 ቀን 2018 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ ባካሄደው ውይይት ላይ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ደረጀ ማንደፍሮ እንደተናገሩት በ2017/18 የምርት ዘመን በሰብል ከተሸፈነው አምስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ 187 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል። እስከ ህዳር ወር መጨረሻ ሳምንት ሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሄክታር ሰብል ተሰብስቧል። ከዚህ ውስጥ 60 በመቶ የምግብ፣ 35 በመቶ ለኢንዱስትሪ እና አምስት በመቶ ደግሞ ለውጭ ገበያ/ኤክስፖርት/ ይውላል።
ቢሮ ኃላፊው ለበኵር እንደተናገሩት በምርት ዘመኑ ሁለት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም (በክላስተር) ለምቷል። በገበያ ተፈላጊ የሆኑ ዋና ዋና /የኮሞዲቲ/ ሰብሎች እንደ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ማሽላ፣ ጤፍ እና ሩዝ በስፋት በኩታ ገጠም የለሙ ናቸው::
አርሶ አደሩን ከእርሻ ዝግጅት ጀምሮ ያሳየውን ጽናት በምርት አሰባሰቡ ላይ ብክነት እንዳይኖር አጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠይቋል:: አሁን ላይ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ሙያዊ ምክር እና የቴክኖሎጂ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም ኃላፊው ተናግረዋል።
አርሶ አደሮችም በመተባበር ሰብል እንዲሰበስቡ የመቀስቀስ ሥራ እየተሠራ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው፤ ለአብነት ምሥራቅ ጎጃም ዞን ባሶሊበን እና ደብረኤሊያስ ወረዳ በስፋት እየተሰበሰበ ይገኛል። በተመሳሳይ በሰሜን ሸዋ የሲያደብርና ዋዩ ወረዳ በሜካናይዜሽን በስፋት ሰብል የማሰባሰብ ሥራዎች እየሠሩ ነው።
ኮምባይነር፣ ትሬሸር፣ አነስተኛ የማጨጃ እና የበቆሎ መፈልፈያ ማሽኖችንም ጭምር ድህረ – ምርት ላይ የሚደርሰውን ተጽዕኖ ለመከላከል በእጅጉ ወሳኝ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ይህም በሚፈለገው ደረጃ ደርሷል ማለት አይቻልም ያሉት ቢሮ ኃላፊው፤ በቀጣይም ወደ ዘመናዊ ግብርና ትራንስፎርሜሽን /ሽግግር/ ትልቁ አቅም ቴክኖሎጂን መጠቀም በመሆኑ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ አርሶ አደሩ ያልተሰበሰቡ ቀሪ ሰብሎችን በደቦ (በወንፈል) ፈጥኖ የመሰብሰብ ተግባሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል። የግብርና ባለሙያዎችም ለአርሶ አደሩ ሙያዊ ድጋፍ እና ግንዛቤዎችን መፍጠር ይጠበቅባቸዋል። መገናኛ ብዙኃንም አንዱ የልማቱ አጋዥ ስለሆነ የአየር /የሜትሮሎጂ/ ትንብያዎችን እና የጥንቃቄ መልዕክቶችን በየጊዜው እንዲያስተላልፉ ጠቁመዋል። የታቀደው ምርት እንዲገኝ የደረሱ ሰብሎችን በአግባቡ ከብክነት በጸዳ መንገድ እንዲሰበሰብ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ቢሮ ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል።
መረጃ
ለምርት ብክነት ዋና ዋና ምክንያቶች
ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂ አለመኖር፦ ሰብልን ለመሰብሰብ፣ ለማጓጓዝ፣ ለመውቃት እና ለማጽዳት ባህላዊ ዘዴዎችን መጠቀም ለብክነት ይዳርጋል።
የማከማቻ (ጎተራ) ችግር፦ ምርትን ከተባይ፣ ከአይጥ እና ከእርጥበት የሚከላከሉ ዘመናዊ መጋዘኖች (የብረት ጎተራ) እጥረት።
የመሰረተ ልማት ችግር፦ የመንገድ አለመመቸት ምርቱ ቶሎ ወደ ገበያ እንዳይወጣ እና በመንገድ ላይ እንዲበላሽ ያደርጋል።
የአያያዝ እውቀት ማነስ፦ በተለይ እንደ አትክልት እና ፍራፍሬ ያሉ በቀላሉ የሚበላሹ ምርቶችን እንዴት ማቆየት እንደሚቻል ግንዛቤ ማነስ እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ።
ምንጭ፦ ፋኦ (FAO)
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የህዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


