ከግምት ያለፈዉ

0
100

የባሕር ወለል ከፍታ ከሚጠበቀው በላይ በመጨመሩ ዳርቻው በማዕበል እና ሞገድ ከመሸርሸር አልፎ በአቅራቢያው በሚገኝ ስነ ምህዳር እና ኗሪዎች ላይ ውድመት ማስከተሉን ስፔስ ዴይሊ ድገ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል፡፡

በአየር ንብረት ለውጥ መንስኤነት የባህር ወለል ከፍታ ይጨምራል ተብሎ የተገመተው በ2014 እ.አ.አ 0.17 ኢንች ወይም 0.43 ሴንቲ ሜትር ነበር፤ በእውን የተለካው የከፍታ መጠን ግን 0.23 ኢንች ወይም 0.59 ሴንቲሜትር ሆኗል፡፡ ሁነቱም የባህር ወለል ከፍታ ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሻቀቡን አመላክቷል፡፡

በአሜሪካ ደቡብ ካሊፎርኒያ በሚገኘው የናሳ የአሜሪካ የጠፈር መንኩራኩር ማምጠቂያ የሙከራ ጣቢያ ተመራማሪው ጆሽ ዊሊስ በ2024 እ.አ.አ የታየው የውቅያኖስ ወለል ከፍታ ጭማሪ ከተጠበቀው በላይ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ ጭማሪው በተከታታይ መመዝገቡንም ነው እማኝነታቸውን የሰጡት፡፡

ቀደም ባሉት በጣቢያው ከተመዘገበው መረጃ በሙቀት መጨመር በረዶ ቀልጦ ወይም እየሟሟ ወደ ባህር መግባቱ ሁለት ሦስተኛ ለሚሆነው ጭማሪ መንስኤ መሆኑ ነበር የታመነበት፤ ቀሪው አንድ ሦስተኛ ደግሞ በሙቀት መጨመር የባህር ውኃ በመስፋፋቱ ወይም በሙቀት መጠኑ ከፍ ከማለት የመጣ ተደርጎ ታስቦ ነበር- በባለሙያዎች፡፡

አሁን ላይ በመስኩ ባለሙያዎች በተደረገ ክትትል እና ምርምር የባህር ወለል ጭማሪ መንስኤ መገላበጡን እንደደረሱበት ነው ድረ ገፆች ያስነበቡት፡፡ በዚሁ መሰረት በሙቀት መጨመር በባህር ውኃ መስፋፋት (expand) ሲያደርግ የታየው ጭማሪ ሁለት ሦስተኛውን ዕጅ ይዟል፡፡ በባህሩ ዙሪያ የሚገኝ በረዶ ቀልጦ ወደ ባህር በመግባቱ የተስተዋለው ጭማሪ ደግሞ አንድ ሦስተኛውን ጭማሪ መያዙ ነው የተመላከተው፡፡

በአሜሪካ  ዋሽንግተን የሚገኘው የጠፈር ምርምር ተቋም የባህር ጥናት እና ክትትል ኃላፊ ናዲያ ቪኖግራዳቫ ሺፈር በ2024 እ.አ.አ ሙቀቱ ካለፉት 30 ዓመታት ከፍተኛ ጣሪያ ሆኖ መመዝገቡን አስረድተዋል፡፡ አሁን  እየተስተዋለ ያለው ሁነት በዚህ መልኩ የሚቀጥል ከሆነ በመጪዎቹ 30 ዓመታት የባህር ወለል ከፍታው ከ10 እስከ 12 ኢንች ጨምሮ በባህር ዳርቻ በሚገኙ ኗሪዎች እና ስነ ምህዳር ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርስ ነው ያሳሰቡት፡፡

በመጨረሻም የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች፣ ሀገራት ፣ ድርጅቶች ፣የምርምር ተቋማት ወ.ዘ.ተ መፍትሄው ላይ ጠንክረው ሊሠሩ እንደሚገባ ነው በማደማደሚያነት ያሰመሩበት፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የመጋቢት 22  ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here