ከጠብመንጃ ወደ ውይይት!

0
172

አማራ ክልል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ሆኖ፣ በትጥቅ የታገዘ ግጭት  ውስጥ ከገባ ዐሥር ወር ደፈነው። አዋጁ ሰላም እና መረጋጋትን ለማምጣት ታስቦ በመጀመሪያ ለስድስት ወር፣ ከዚያም ለአራት ወር  ዘልቆ ነበር።   ባለፉት  ዐሥር ወራት መንገዶች አስተማማኝ ያልሆኑበት፣ ተማሪዎች ከትምህርት ደጃፍ የራቁበት፣ አርሶ አደሮች ከበሬ ማረሻ ይልቅ የከባድ መሳሪያ ድምፅ የሰሙበት፣ በጥቅሉ ከባድ ሰብዓዊና  ቁሳዊ ውድመትን ያስከተለ  ግጭት ነበር።

በሰሜኑ ጦርነት በርካቶች ሕይዎታቸውን አጥተዋል። ከዚህ ጦርነት በኋላ ደግሞ ሰላም ይሆናል ተብሎ በብዙዎች በተስፋ ተጠብቆ ነበር። ይሁን እንጂ  የሀገሪቱን ከግማሽ በላይ ሕዝብም፣ የቆዳ ስፋትም የያዙት የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች ግጭት ውስጥ ገብተው ከርመዋል።  ሀገራዊ እሴቶች እየላሉ፣ መተማመኑ እየሳሳ፣ ፍረጃ እና ጥላቻው እየወፈ ሂዷል። ይህን ሁሉ ለማከም ብሄራዊ የምክክር ኮሚሽን በአዋጅ የተቋቋመ ቢሆንም ለምክክሩ  እንኳን ግጭቱ፣ ጦርነቱ እና ተኩስ አለመቆሙ ፈተና ሆኗል። በዚያ ላይ ኮሚሽኑ ገለልተኛ እና በነፃ ተቋም ላይ የተመሰረተ ነው ወይ? የሚለው ጥያቄ ጥርጣሬ በማስነሳቱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዳንዶች ራሳቸውን ከምክክሩ አግልለዋል።

በእርግጥ ከሁሉም የሚቀድመው ጉዳይ የመሳሪያን ድምፅ  ከዜጎች ደጅ ማጥፋት ነው። የመሳሪያ ላንቃ እስካልተዘጋ ድረስ ሰክኖ ለመወያየት፣ ለመተማመንም ሆነ በዘላቂ ጉዳዮች ላይ  ውሳኔ ለማሳረፍ ያስቸግራል።

በመሆኑም  ለዚህ ሁሉ ቀውስ ምክንያቱ የፖለቲካ ብልሽት ነውና የፖለቲካ ችግርን በፖለቲካ መፍታት ይገባል። የፖለቲካ ችግር ሲባል ነፃ እና ፍትሐዊ ተቋም አለመኖር፣ የሕግ የበላይነት እና ፍትሕ አለመስፈን፣ አሳታፊ እና ሁሉን ወካይ መንግሥታዊ ሥርዓት አለመፋፋቱ መሆኑ ግልፅ ነው። ስለዚህ መፍትሔውም አካታች ሥርዓትን በውይይት መዘርጋት፣ ፍትሕን ማስፈን፣ የሕግ የበላይነትን በፍትሐዊነት ማረጋገጥ ተገቢነቱ አጠያያቂ አይደለም።

ከሁሉም በላይ ተኩስ ቁሞ ሀቀኛ ውይይት እና ንግግር ማድረግ ተገቢ ነው። በእልህ፣ በማስመሰል፣ በእብሪት፣ በፍረጃ፣ በእኔባይነት ብቻ የሚባባስ እንጂ የሚቃለል ችግር ባለመኖሩ ነገሮችን አለዝቦ ለውይይት መሰናዳት ያስፈልጋል። የሕዝብ ሰላም እንዲመለስ ሀቀኛ ንግግር ወይም ድርድር ግድ ይላል።  ያለበለዚያ በመሳሪያ ብርታት ብቻ መፍትሔ ይመጣል ከተባለ የሰው ደም እየፈሰሰ፣ ሀገር እየፈረሰ፣ ምጣኔ ሐብቱ እየወደመ፣ ታሪካዊዉ ቁርሾ እየሰፋ  ቀውሱ  ከገደብ አልፎ   ሊያስቸግር ይችላል።  ጦርነት ወይም ግጭት ስልጣኔን እና የሰውን ሕይወት የሚበላ፣ ሰውን የሚያሳቅቅ፣ ሐብት የሚያደቅ አደገኛ  ክዋኔ ነው።

ስለዚህ ከግጭት ለመውጣት በግልፀኝነት  የንግግር በር ይከፈት! መፈራረጅ እና መገዳደል   ይብቃ። ሀገራችንም ከራሷ ወደ ራሷ እየተኮሰች ራሷን ማቁሰል የለባትም። አሁንኑ ከጠብመንጃ ወደ ውይይት፣ ከውይይት ወደ ሰላም፣ ከሰላም ወደ ልማት ይገባ!

 

በኲር ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here