ከፍ ያላሉት የከፍተኛ ሊግ ክለቦች

0
132

የ2017 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር ጥቅምት ዐስር እንደሚጀመር አወዳዳሪው አካል አሳውቋል። ውድድሩ ቀደም ብሎ መስከረም 26 እንደሚጀምር ቀነ ቀጠሮ ቢያዝም ክለቦቹ የበቂ ቅድመ ዝግጅት ጊዜ እንዲያገኙ ታስቦ የቀን ለውጥ ተደርጓል። በሊግ እርከኑ የሚወዳደሩ ክለቦችም ከነሐሴ ዐስር  እስከ 17 ቀን 2017 ዓ.ም የክለብ ፈቃድ (ላይሰንሲንግ) ምዝገባ ማከናወናቸውም ተገልጿል።

ምዝገባ ካከናወኑት  መካከል 20 ክለቦች መስፈርቱን አሟልተዋል። እንዲሁም ምዝገባ ያከናወኑ አራት ተጨማሪ ክለቦች ቢኖሩም መስፈርቱን ግን አላሟሉም ነው የተባለው። ሦስት ክለቦች ደግሞ በተሰጠው የጊዜ ቀነ ገደብ ምዝገባ እንዳላከናወኑ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ መረጃ ያመልክታል። እናም ምዝገባ ያላከናወኑ ክለቦች በዘንድሮው በወንዶች የከፍተኛ ሊግ ውድድር እንደማይሳተፉ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል። ለ2017 የወንዶች ከፍተኛ ሊግ ውድድር ምዝገባ ካላከናወኑ ሦስቱ ክለቦች ውስጥ ሁለቱ የአማራ ክልል ክለቦች ናቸው። ወልዲያ ከነማ እና ሞጣ ከነማ ዘንድሮ በከፍተኛ ሊግ ውድድር የማይሳተፉት ክለቦች ናቸው።

ወልዲያ ከነማ ለረዥም ዓመታት በከፍተኛ ሊግ የቆየ ክለብ ነው። ክለቡ ለመጨረሻ ጊዜ በፕሪሚየር ሊጉ የተሳተፈው ከሰባት ዓመታት በፊት ነበር። ድጋሚ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ለመመለስ ግን ባለፉት ዓመታት ዳገት ሆኖበት ቆይቷል። በ2016 የውድድር ዘመን ደካማ ውጤት ያስመዘገበ ሲሆን ከምድቡ ስምንተኛ ሆኖ ነው ዓመቱን ያጠናቀቀው። ራሱን አጠናክሮ ከአምናው ተሻሽሎ ይመጣል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ወልዲያ ከነማ ዘንድሮ በገንዘብ ችግር ምክንያት እንደማይሳተፍ ተረጋግጧል።

በገንዘብ ችግር ምክንያት ትልቅ ቀውስ ውስጥ የገባው ወልዲያ ከነማ በከፍተኛ ሊግ ለመወዳደር አቅም አንሶታል። ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ሲንከባለል የቆየ ለተጫዋቾች እና ለአሰልጣኞች የቡድን አባላት የደሞዝ እና የፊርማ ያልተከፈለ ክፍያ  ስምንት ሚሊዮን 900 ሺህ  ውዝፍ እዳ እንዳለበትም የክለቡ ሥራ አስኪያጅ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል። ታዲያ ያለበትን ይህን ውዝፍ እዳ መከፈል እስኪችል የአንድ ዓመት የእፎይታ ጊዜ ተሰጥቶ ከውድድር እንዲርቅ አወዳዳሪውን አካል አሳውቆ ተቀባይነት አግኝቷል።

እንደ ክለቡ ሥራ አስኪያጅ ገለጻ ወልዲያ ከነማ በቀጣይ ዓመት ወደ ውድድር ይመለሳል ተብሏል። ከተማ አስተዳደሩ በሚበጅትለት በጀት፣ ከባለሀብቶች እና ደጋፊዎች ገንዘብ በመሰብሰብ ያለባቸውን እዳ በመክፈል እና ራሳቸውን በማጠናከር በ2018 የውድድር ዘመን ለመመለስ ከወዲሁ ሥራዎች እየተሰሩ ነውም ብሏል ሥራ አስኪያጁ።

ሌላኛው ዘንድሮም በከፍተኛ ሊግ የማይሳተፈው ክለብ ሞጣ ከነማ ነው። በ2004 ዓ.ም በአማራ ክልል ዞኖች ውድድር ተሳትፎውን የጀመረው ሞጣ ከነማ ከአንድ ዓመት በኋላ የአማራ ሊግ ውድድርን ተቀላቅሏል። በ2014 ዓ.ም በኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ የተሳተፈው ክለቡ በ2015 ዓ.ም ደግሞ የሀገሪቱ ሁለተኛውን ትልቅ የሊግ እርከን ወደ ሆነው የወንዶች ከፍተኛ ሊግ አድጓል። ይሁን እንጂ በ2016 ዓ.ም በአማራ ክልል በተከሰተው የሰላም ችግር ምክንያት በውድድሩ መሳተፍ አልቻለም።

ዘንድሮም በክልሉ የተፈጠረው የሰላም ችግር እልባት ባለማግኘቱ እንደማይሳተፍ ለእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በደብዳቤ አሳውቋል። ሞጣ ከነማ በቀጣይ በ2018 ዓ.ም ወደ ውድድር እንደሚመለስም ለፌዴሬሽኑ ያስገባው ደብዳቤ ያስነብባል።

ዘንድሮ በወንዶች የከፍተኛ ሊግ ውድድር አማራ ክልልን የሚወክሉ ክለቦች ቁጥርም ሦስት ብቻ ሆኗል። በዚህ መድረክ እንጅባራ ከነማ፣ ደሴ ከተማ እና ደብረ ብርሃን ከተማ የሚሳተፉ ይሆናል። እነዚህ ክለቦች በውድድር ዓመቱ መጨረሻ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እየሰሩ ይገኛል።

እንጅባራ ከነማ በ2004 ዓ.ም ነው የተመሰረተ። በ2013 ዓ.ም ደግሞ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ከፍተኛ ሊግ ተሸጋግሯል። በ2014 ዓ.ም ግን በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት በመድረኩ መቅረብ አልቻለም። ከአንድ ዓመት በኋላ በውድድሩ የተሳተፈ ሲሆን 35 ነጥቦችን በመሰብሰብ ሰባተኛ ደረጃን ይዞ ነበር ያጠናቀቀው።

በመጀመሪያው ዓመት የከፍተኛ ሊግ ተሳትፎው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ያደረጉት የደጋ ፈረሶቹ ባሳለፍነው የ2016 የወንዶች ከፍተኛ ሊግ ውድድር ግን አማራ ክልል በተፈጠረው የሰላም ችግር ምክንያት መሳተፍ አልቻለም። እንጅባራ ከነማ በ2015 ዓ.ም የፊት መስመሩ እና የኋላ ክፍሉ የጎላ ችግር ባይስተዋልበትም በሁሉም የሜዳ ክፍል የነበሩበትን ክፍተቶች ማረም ከቻለ ተፎካካሪ ይሆናል ተብሎ ይገመታል።

ደሴ ከነማ በዚህ ዓመት በወንዶች ከፍተኛ ሊግ ውድድር የሚሳተፍ ሌላኛው የአማራ ክልል ክለብ ነው። ደሴ ከነማ ባሳለፍነው ዓመት በመድረኩ ጠንካራ ተፎካካሪ እንደነበር አይዘነጋም። ቀስ በቀስ ሜዳ ላይ እየተሻሻለ እና ለውጥ እያሳዩ ከመጡ የአማራ ክልል ክለቦች አንደኛው ነው። ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ባጠናቀቀበት የ2016 የውድድር ዓመት፤ ፕሪሚየር ሊጉን ከተቀላቀለው አርባ ምንጭ ከተማ ቀጥሎ ከምድቡ አስፈሪ የፊት መስመር እንደነበረው የሚታወስ ነው።

የኋላ ክፍሉ ግን በቀላሉ የሚረበሽ እና በርካታ ግቦች የተቆጠሩበት እንደነበር ቁጥሮች ይናገራሉ። ክለቡ በአዲሱ የውድድር ዓመት ይህን ክፍተቱን ለመሙላት ከቅድመ ውድድር ዝግጅት ጎን ለጎን የነባር ተጫዋቾችን ውል በማደስ እና  በሁሉም የሜዳ ክፍል አዳዲስ ተጫዋቾችን በማስፈረም ቡድኑን እያጠናከረ ይገኛል። የአሰልጣኙን ውል በማደስ ክለቡን የማጠናከር ስራ የጀመረው ደሴ ከነማ የበርካታ ነባር ተጫዋቾችን ውል አድሷል።

የተከላካይ ሥፍራ ተጫዋች የሆነው ሞገስ ኩምቻ ከጋሞ ጨንቻ እና ባሳለፍነው ዓመት በነቀምቴ ከተማ 11 ግቦችን ያስቆጠረውን ኢብሳ ፈቃዱ ደግሞ ክለቡን ከተቀላቀሉ አዲስ ተጫዋቾች መካከል ይገኝበታል። ደሴ ከነማ በያዝነው የውድድር ዓመት መጨረሻ ፕሪሚየር ሊጉ በመቀላቀል በ1980ዎቹ በወሎ ምድር “የወሎ ምርጥ” የነበረውን ስም እና ዝና እንደሚመልስ ብዙዎች እምነት አሳድረዋል።

ደብረ ብርሃን ከነማ ባለፉት ሁለት የውድድር ጊዜያት በብዙ ቢጠበቅም ደካማ የውድድር ጊዜ ነው ያሳለፈው ማለት ይቻላል። ክለቡ ከተመሰረተ 42 ዓመታትን ቢያስቆጥርም ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ለማደግ ተስኖት ረዥም ዓመታት በታችኛው ሊግ ቆይቷል።  ብርሃኖቹ አምና ከደሴ ከነማ በሰባት ነጥብ አንሰው በ38 ነጥቦች አራተኛ ሆነው ነበር የጨረሱት። የፊት መስመሩ ምንም እንኳ ያን ያህል ደካማ ነው ባይባልም የኋላ ክፍሉ ግን ያልተደራጀ እና በርካታ ግቦች የተቆጠሩበት እንደነበር ይታወሳል።

በመጀመሪያው ዙር ውድድር ይህ ችግሩ ጎልቶ የተስተዋለ ሲሆን ይህም በውጤቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሮበታል። ታዲያ በዚህ ዓመት የአምናውን ችግራቸውን ላለመድገም ከወዲሁ በመሥራት ዓመቱን ከጀመሩ፤ በውድድር ዓመቱ መጨረሻ በውጤት ታጅበው ያጠናቅቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በወንዶች ከፍተኛ ሊግ ውድድር የሚሳተፉ የአማራ ክልል ክለቦች በክልሉ በተፈጠረው የሰላም ችግር ምክንያት፤ በቂ የቅድመ ውድድር ዝግጅት ሳያደርጉ ወደ ውድድር መግባታቸው ይታወሳል። ይህም በውጤታቸው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሮ አልፏል። ይህ እንዳይሆን የሚመለከታቸው አካላት ክለቦችን በመደገፍ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ እገዛ ሊያደርጉላቸው ይገባል። በወንዶች የከፍተኛ ሊግ ውድድር ሁለት ክለቦች ወደ ፕሪሚየር ሊግ የሚያድጉ ሲሆን አምስት ክለቦች ደግሞ ወደ ታችኛው የሊግ እርከን የሚወርዱ ይሆናል። ፕሪሚየር ሊጉን ለመቀላቀል ከሚደረገው ፉክክር ባልተናነሳ  ላለመውረድ የሚደረገው ትንቅንቅም ከወዲሁ የሚጠበቅ ይሆናል።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር ጥቅምት 4  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here