ከፔንስዮን ኑሮ ያልታደገ ሙያ

0
253

ኢትዮጵያ በየጊዜው ጠላቶች እየተነሱባት ልጆቿ እንደ ቅጠል ረግፈው እያሻገሯት የቀጠለች ሀገር ናት። ሀገርን የሚያኖረውም በየዘመኑ በሕዝብ የሚከፈል መስዋእትነት ነው። በየጊዜው ወራሪዎች ኢትዮጵያን የቀልባቸው ማረፊያ አድርገው የመውረር ሙከራዎችን አድርገዋል።
በ1969 ዓ.ም የዚያድባሬ መንግሥት የኢትዮጵያን ዳር ድንበር አልፎ ወረራ ፈጽሟል። በወቅቱ የኢትዮጵያ ራድዮው ጋዜጠኛ አበራ ለማ ጦርነቱን ለመዘገብ በግንባር ተገኝቷል። “የብዙኃን እናት ሀገሬን አትንኳት” በሚል ግጥም ጽፎ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዲታተም አደረገ። ግጥሙ ይህችን ውብ እና በየዘመኑ ትውልድ ሊያጸናት የሞተላትን ሀገሬን አትንኳት በሚል በልጅ እና እናት ስሜት የተጻፈ ነበር። በወቅቱ ወጣቱ ድምጻዊ ጌታቸው ካሳ ግጥሙን እንደተመለከተው ደራሲውን አበራ ለማን ማስፈቀድ ነበረበትና ተገናኝተው ተጨዋወቱ። ግጥሙን ለሙዚቃ አስማምቶ ለጌታቸው ሰጠው። አንድም ተጨማሪ “አደሴዋ” የሚል ግጥም ጨመረለት። ይህ የብዙኃን እናት ሙዚቃ ተሰርቶ ለአድማጭ ደረሰ። በወቅቱ ውጊያ ላይ ለነበረው የኢትዮጵያ ሠራዊት እና ሕዝብ ሙዚቃው ትልቅ አቅም እንደነበር አበራ ለማ ያስታውሳል። ይህ ዘፈን እንኳንስ ሀገር በወራሪ ተይዛ ይቅርና በሠላሙም ቀን ብትሆን ሆድ የሚያስብስ ነው።
”በዐድዋ በማይጨው ጀግኖች የሞ ቱላት
ሕ ጻን ሽማ ግሌ የተሰየፉላት
ደመ መ ራራና ቁጡነት ያለባት
ጐጆዬ ናት እና አገሬን አትንኳት”
ጌታቸው ካሳ ይህንን ዘፈን ውብ አድርጎ ተጫውቶታል። ሀገር ውስጧን የከፋው ሲመስለን በዚህ ዘፈን እንቆዝማለን። ሀገሪቱ እንዲሁ ተራራ እና ጋራ አይደለችም። ቁጡ፣ አትንኩኝ የሚል፣ ከሕጻን እስከ ሽማግሌ ሞተው፣ በዐድዋም በማይጨውም ጠላትን ገድለው አፈር ሆነው ያቆዩልኝ የሞቀች ጎጆዬ ናት፤ እባካችሁ አትንኳት ይላል ጌታቸው ካሳ። ኢትዮጵያ ምስጢር፣ ገመና ከታች ቤት ብቻም አይደለችም፤ እናት – እማማም ጭምር ናት። ከጭልፊት ነጣቂ አሞራ በክንፏ እንደምትከልል እናት ዶሮ ብዙኃኑን ያስጠጋች ጥላ ናት፤ ኢትዮጵያ ማለት።
የሀገር ቀጣይነት በትውልዶች መስዋእትነት ይቀጥላል። ጌታቸው ካሳ ዘርዓይ ድረስ በሮም ስለቆመላት፣ ጀግኖች በጦር ሜዳ ወጥተው ስለቀሩላት በቃኝ አላለም። ትናንትን በጀግኖች የቀጠለች አገር ዛሬም የእሱን ተጋድሎ እንደምትፈልግ ያነሳል።
”ዘርዓይ ድረስ ወንዱ በሮም የቆመ ላት
ጀግኖች በጦር ሜ ዳ ወጥተው የቀሩላት
እኔም በተጠ ንቀቅ አለሁሽ የም ላት
ጥቁሯን አፍሪካዊት ኢትዮጵያን አትንኳት”
የጌታቸው ካሳ ሕይወት ከመጀመሪያውም የመነጠልና የመወገዝ አዙሪት ያልተለየው ነው። በዘመኑ ሙዚቃን እንደ ርካሽ ነገር የቆጠሩት አባቱ ሙዚቃ የሚያደምጡ፤ትልቅ ራዲዮ እና ሸክላ ማጫዎቻ የነበራቸው ቢሆኑም በዘፋኝ ልጅ ስማቸው እንዲጠራ አልፈለጉም።
ገና በስድስት ዓመቱ ሙዚቃን ከልቡ ወደዳት፤ አባቱ አይሆንም አሉት። ልጁ ግን ሙዚቃን መርጦ ከቤት ወጣ። ጠፍቶ ወደ ሐረር ፖሊስ ኦርኬስትራ ተጓዘ። “እመኛለሁ” በሚል ሙዚቃ አወጣ። አባቱ ድምጻዊ ጌታቸው ጸጋዬ ተብሎ ሲጠራ ተበሳጩ። በል ጌታቸው ጸጋዬ ስትል እንዳልሰማህ አሉት። በወቅቱ አሰገደች ካሳ (ድምጻዊት) የጌታቸው ፍቅረኛ ነበረች። በቃ በአባትሽ ስም ልጠራ ብሎ ጌታቸው ካሳ ተብሎ ቀጠለ። እመኛለሁ የህይወቱን ጉዞ እና ምኞትን የሚያሳይ ዘፈኑ ነው። ጌታቸው የወደ ኋላውን ህይወቱን ቀደሞ የገለጸ ያህል ዘፈኑ የህይወቱ መጨረሻ ዓመታትን ያልተቃና ኑሮ እና ጥሩ የመኖርን ምኞት ይናገራል።
“እመ ኛለሁ ዘወትር በየዕለቱ
ላሳካው ኑሮን ከብልሃቱ፤
ኑሮና ብልሀት እስኪሳካልኝ
በሐሳብ ግስጋሴ ወደርም የለኝ፤
አልቃና እያለኝ ኑሮና ብልሀቱ
መቼ ው ም አልቀረ ም ኞት መ ዘግየቱ፤
አሻቅቤ ስሮጥ ከበላይ ቋጥኝ
እየተጫነኝ ነው ያልተቃናልኝ”
በዘፈኑ ረገድ ወፍራም እና መልካም ድምጽ አላቸው ከሚባሉ አንጋፋ ድምጻዊያን መካከል ጌታቸው ካሳ አንዱ ነበር። ከፈጣን ባንድ ጀምሮ በቬነስ፣ በሂልተን ፣በዋቢ ሸበሌ፣ ኢትዮ ስታር፣ዋልያስ ባንዶች እና ሆቴሎች በመሥራት ምርጥ ሙዚቃዎችን በሸክላ እንዲሁም በካሴት ሠርቷል። በዘመነ ደርግ ከአምሐ እሸቴ ጋር ወደ አሜሪካ በመጓዝ ሙዚቃዎችን አቅርቧል። ዘፈኖቹ ዛሬም ድረስ የሚደመጡ አዳዲስ ትውልድ ጉሮሮውን የሚያሟሽባቸው፣የዘመን ትዝታዎች የተሳሉባቸው ሆነዋል። እኔስ አልከፋም በሚል ርዕስ ከዋልያስ ባንድ ጋር ምርጥ የትዝታ ዘፈኑን ሠርቷል። ይህ አዘፋፈን ከሌሎች የወቅቱ ዝነኞች የትዝታ ዘፈን በተለየ የሠራሁት የራሴ ስልት ነው ብሏል፤ ጌታቸው። የትዝታን ረቂቅ ስሜት የሚገልጽበት ይህ ዘፈን በ1964 ነበር ለአድማጭ የደረሰው። ትዝታን ጌታቸው ካሳ ይዝፈናት የሚሉ ብዙዎች ናቸው፤ የትዝታው ንጉሥ የሚሉትም አሉ።

”ትዝታሽ ዘወትር ወደ እኔ እየመ ጣ
እፎይ የም ልበት ሕይወቴ ጊዜ አጣ፤
እኔስ አልከፋም ም ንድን ነው ቅሬታ
ስንት እየተሰማ ኝ አለሁ በትዝታ
ርቄ አይሻለሁ በሐሳብ ትዝታ
ተለይቼሽ ስሄድ ቀንም ሆነ ማ ታ”
ሕይወታችን የትናንት ሐሳቦች እና ድርጊቶች የሚርመሰመሱበት የትዝታ ድግግሞሽ ማሳ ነው።ጌታቸው ይኽንን የትናንት ሁነት በመደጋገም ነው የሚያዜመው። ዋ—-ዋዋዋ—–ዋዋዋዋ ሲል አንዳች የሚነዝር ስሜት ይፈጥራል። በዝግታ ይጀምርና መሐል ላይ ደግሞ ፈጣን ያደርገዋል። ስንት እየተሰማኝ አለሁ በትዝታ ይላል፤ ውስጡ ብዙ የሚመላለስ ጉዳይ አለበት።ይኽንን ዘፈን ስንሰማ ሁላችንም ሙዚቃ አፍቃሪያን ወደ ኋላ መጎተታችን አይቀርም። “ፍለጋችን የቆዩ ሙዚቃዎችን አይደለም፤ ትዝታዎቻችንን እንጂ” በሚል አንድ ሰው ከዩቱዩብ ሙዚቃ ስር አስተያየት ጽፎ አንብቤያለሁ። ጌታቸው በርካታ ሙዚቃዎች አሉት። እሸት እሸት፣ቆንጆ ነሽ፣ብቻዬን ተክዤ፣ሳይሽ እሳሳለሁ፣ የከረመ ፍቅር፣ ብርቱካን ነሽ ሎሚ፣ አመሰግናለሁ፣ እወድሻለሁ፣ አዲስ አበባ፣ ልውሰድሽ አንድ ቀን፣ አትጥፊ ከጎኔ፣ ውበትም ይረግፋል፣ ትዝ ባለኝ ጊዜ፣ ትዝታ እና ሌሎችም ተወዳጅ ዘፈኖቹ መታዎሻዎቹ ናቸው። የትዝታ ዘፈኖቹን በተለያዩ ጊዜያት ዘፍኗቸዋል፤ እንደገና ሲዘፈኑ በብዙ መልኩ አዲስ መስለው ተደምጠዋል።
በትዝታ ዘፈኑ (አቀመስሽኝ አሉ)
እንዲህ ብሏል።

“ትናንት ተጨ ንቄ ዛሬም ብሶብኛል
ለማ ዳን ሲቻልሽ ችላ ብለሽኛል
ከከንፈር ከጥርስሽ ዓይንሽ ይሻለኛል
ምንም ሰው ቢበዛ አሻግሮ ያየኛል”
ትናንት የጀመረው የጌታቸው ትዝታ ዛሬም አልተወውም። እመኛለሁ አለ፤ አልተሳካለትም። ያደረ የትዝታው እዳ አገረሸበት። አንቺማ አልጠየቅሽኝም፤ ባይሆን ዓይን ተሻለኝ እንጂ ይላል። ጥርስ እና ከንፈርማ ጭራሽ ሲያዩት ፈገግ ብለው አሽሟጠጡበት። እንዲያውም ድግምት ነው ያበላሽኝ በደህናዬ አይደለም ይላል።

”አቀመሽኝ አሉ መ ድ ኃኒት በጠ ላ
አንቺን አስወድዶ ሌላ የሚ ያስጠ ላ”
ቀደም ብሎ ዋዋዋ —- ያለውን አሁሁሁ- ኡሁሁ ይላል። ገራሚ ሙዚቃ። ጌታቸው ካሳ በአሜሪካን ሀገር ለ28 ዓመታት በተለያዩ ግዛቶች በመዘዋወር ሙዚቃዎችን አቅርቧል። በስደት ሀገር እና በሀገር መካከል ያለውን ልዩነት የሚያሳይ አንድ ግጥም አንጋፋዉን ገጣሚ ጸጋየ ደቦጭን እንዲጽፍለት ይጠይቀዋል። በወቅቱ ጌታቸው ኢትዮጵያም አሜሪካም ይመላለስ ነበር። ግጥሙ ተጻፈ፤ አበበ ብርሀኔ ዜማ ሠራለት፤ ከሀገር የመውጣትን ባይተዋርነት እና ከባድ ፈተና ያሳያል። ሀገሬ ትዝታሽ ተብሎ ዘፈን ወጣ።

“ቀና ብዬ ሳየው ሰማ ይ ደፈረሰ
ልቤም ሳር ቅጠ ሉን ም ድ ሩን
አስታወሰ
ሀገሬ ትዝታሽ ነገሰ፤
ቢስቅ ጠረጠሩት ቢያኮርፍ አደሙ በት
ሰው ያለ ሀገሩ መ ቼም አያም ርበት፤
የባይተዋር እንባ እንዲገደብ ቦዩ
ይመ ለስ ከአገሩ ይታረቅ ከአዋዩ”
ብሎ አዜመ። ይህ ዘፈን እንደ ሀገሬን አትንኳት የሀገር ናፍቆት የሚገለጽበት ነው። በባእድነት የሚኖር ሰው ሳቁም ኩርፊያውም በበጎ አይተረጎምም። ሀያ ስምንት ዓመታትን በባይተዋርነት በስደት ሀገር የቆየው ጌታቸው ካሳ ሲመለስ የቀድሞ የስደት ጓደኞቹን አመሰግናለሁ አለ። የአንዲት ሴት ልጅ አባት ነኝ ይል ነበር ጌታቸው። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር በተደረገ የአስከሬን ሽኝት ላይ ደግሞ ሁለት ልጆች እንዳሉት ተነግሯል። በዚሁ መድረክ ላይ ጥር 3 ቀን 1939 እንደተወለደ ተነግሯል። ትዳር የለውም። በዚሁ መሠረት በ77 ዓመቱ በየካቲት 12 ሆስፒታል፤ የካቲት 12 ቀን 2016 ዓ.ም ከዚህ ዓለም ተለይቷል።
ጌታቸው ካሳ በውጪው ዓለም ጥሩ መኖሩን በተደረጉለት ቃለ መጠይቆች ተናግሯል። ብቸኛ ነበር። ከሙዚቃ በቀር ጓደኛ አልነበረውም። በድህነት ውስጥ አስቸጋሪ ህይወትን ገፍቷል። ከዓምታት በፊት ፔንሲዮን ውስጥ ብቻውን ይኖር ነበር።

“ትዝ ባለኝ ጊዜ ያሳለፍ ነው ፍቅር
ቁጭ ብየ ሳስብ ትጠ ልቃለች
ጀንበር”
ብሎ ከዓመታት በፊት እንዳዜመው የማታው ህይወቱ የመቆዘም እና የችግር ነበር። ሙዚቃ ሲጀምር እመኛለሁ ውስጥ ያስደመጠንን ስንኝ መዝጊያው ላይም ሰምተነዋል፤ አይተነዋል።

“አሻቅቤ ስሮጥ ከበላይ ቋ ጥ ኝ
እየተጫ ነኝ ነው ያልተሳካልኝ”
እንዳለውም በህይወቱ አመሻሽ የኑሮ ቋጥኝ ተጫጭኖት አልፏል። የከፈለው ጥበብ አልከፈለውም። ሙዚቃዎቹ ዛሬም በእጃችን በልባችን፣ በትውስታችን ውስጥ አሉ። ጌታቸው ካሳን ፔንሲዮን ከመኖር አልታደጉትም። በእርጅና ዘመን ማጣት ለዚያውም ዝነኛ እና ተወዳጅ ሰው ሆኖ እንዴት ዓይነት ከባድ ነገር ነው። ከዓመታት በፊት ሰይፉ ፋንታሁን የክብር ዶክትሬት ቢሰጥህ ትፈልጋለህ አለው። “አይ አልፈልግም፤ መቃብሬ ላይ እንዲሠራ የምፈልገው አርቲስት ጌታቸው ካሳ ተብሎ ነው” አለ። ብቸኛ ነኝ የሚለው ጌታቸው ሦስቱም ወንድሞቹ እንደሞቱበት ጠቅሶ ሞት ጥሩ ነው፤ እረፍት ነው ብሏል። ጉዳዩን በውል ከተመለከትው የጌታቸው ከመኖር ሞትን መምረጥ ዝም ብሎ የመጣ አልመሰለኝም። የማምሻን ዘመን በብቸኝነት፣ በችግር እና በህመም ሲሆንበት ሞትን መምረጥ ዕረፍት ሆነለት። የአለም ፀሀይ ወዳጆ ግጥም የጌታቸው ካሳን አኗኗር አስታወሰኝ፤ የማታ እንጀራ ከሚለው መጽሐፍ ውስጥ ራሱ የማታ እንጀራ።

“የማ ታ እንጀራ ስጠ ኝ
የጠ ዋ ት አታስመ ርጠ ኝ
ዘግይተህ በኋላ አስጊጠ ኝ
ማ ታ በክብር ደብ ቀኝ
ከሰው በር አንተው አርቀኝ፤
ጉልበት ጽናቱን ይዞ
አቅሜ ም እንዳቅሙ ተጉዞ
ያልጠ የቀኝን ሳልመ ልስ
መ ንገዴን በወግ ልጨ ርስ—-”
እያለ ይቀጥላል፤ ግጥሙ። የጌታቸው ሕይወት ጠዋት ደስታ ማታ ትካዜ ነበር። በተወለደበት፣ ዝነኛ ሆኖ በሚደነቅበት ከተማ ቤት አልነበረውም። ማምሻው ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለ ሦስት ክፍል መኝታ ክፍል ቤት ሰጠው። በሙዚቃ ክለቦችም መሥራት ጀምሮ ነበር። በተወለደ በ77 ዓመቱ እግሩ አልንቀሳቀስለት ብሎ፣ የልብ ሕመም ተባብሶበት በብቸኝነት ታሞ መሞቱ ተሰማ። ዝነኛው፣ አንጋፋው፣ ሰው አጥቶ፣ በብቸኝነት ኖሮ ማለፍ በቀጣይ በሙዚቃዎቹ ውስጥ የምንሰማው እና የሚከተለን የጥፋተኝነት ስሜት ነው። በሥራዎቹ ሕያው የሆነው ጌታቸው ለቀሪዎቹ ትቶት የሄደው አንዳች የጸጸት እና ከንፈር መምጠጥ ስሜት አይጠፋም።

(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የካቲት 25 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here