በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር በ2017/18 የምርት ዘመን 58 ሺህ 800 ሄክታር መሬት በሰብል ለመሸፈን አቅዶ እየሠራ መሆኑን አስታዉቋል፡፡
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ ሀሰን ሰይድ ለበኵር እንደገለፁት በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የመኸር እርሻን በወቅቱ ለማከናወን የተለያዩ ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ሥራ ተገብቷል። በዞን፣ በወረዳ እና በቀበሌ ለሚገኙ የግብርና ባለሙያዎችም የአቅም ግንባታ ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡
የብሔረሰብ አሥተዳደሩን ምርት እና ምርታማነት ለማሳደግ ሙሉ ፓኬጅን ተጠቅመው አርሶ አደሮች እንዲሠሩ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ኃላፊው ገልፀዋል። ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ነሐሴ 08 ቀን 2017 ዓ.ም 58 ሺህ 839 ሄክታር መሬት መታረሱን ነው የገለፁት። ከታረሰው መሬት ውስጥም 58 ሺህ 750 ሄክታር መሬት በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች ተሸፍኗል። ከዚህ ውስጥ 37 ሺህ ሄክታር መሬት በማሽላ የተሸፈነ መሆኑን ኃላፊው ገልፀዋል። ማሽላን ጨምሮ ጤፍ፣ በቆሎ እና ማሾ አሁን ላይ ተዘርተው እንክብካቤ እየተደረገላቸው የሚገኙ ሰብሎች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
የታለመው ዕቅድ እስከ መጨረሻው እንዲሳካም ለግብዓት አቅርቦት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ኃላፊዉ ተናግረዋል። በምርት ዘመኑ ለብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከሚያስፈልገው 50 ሺህ ኩንታል ሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ 28 ሺህ ኩንታል ደርሷል፡፡ በተመሳሳይ 804 ኩንታል ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቷል።
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በርካታ አካባቢዎች የተፈጥሮ ማዳበሪያ (መደበኛ ኮምፖስት፣ ቨርሚ ኮምፖስት እና ባዮ ሳላሪ ኮምፖስት) የመጠቀም ልምድ እያደገ ነው። የታቀደውን ምርት ለማግኘት አርሶ አደሩ ዘወትር የሰብል ጥበቃ ማድረግ፣ አረምን በወቅቱ ማረም፣ መኮትኮት፣ ሰብልን በተገቢው መንገድ መንከባከብ፣ ዕለታዊ የተባይ እና የበሽታ አሰሳ ማድረግ እና ሌሎች ምርትና ምርታማነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ ተግባራትን ማከናወን እንዳለባቸው አሳስበዋል። የግብርና ባለሙያዎችም ለአርሶ አደሩ ምክረ ሐሳብ ማቅረብ፣ ክትትል እና ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
በምርት ዘመኑ በብሔረሰብ አስተዳደሩ ከአንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎም ይጠበቃል።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የነሐሴ 12 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም