የጥቁር ሕዝብ ኩራት ሆኖ ዛሬ ድረስ ዓለም ሲዘክረው የሚኖረው የአድዋ ድል እነሆ 129ኛ ዓመቱን አስቆጥሮ እንኳ ስሜቱ ትኩስ፣ ዘመን አይሽሬ ነው። ትናንት አድዋ ዛሬም አድዋ እንዳለችው ጂጂ ሌሎችም የኪነጥበቡ ዓለም ሰዎች ለአድዋው ድል ወደር የለሽነት፤ ለተዋደቁት ጀግኖች፣ ለፈፀሙት ገድሎች ተዘፍኖላቸዋል፤ ተገጥሞላቸዋል፤ ተበስሮላቸዋል። እንደ ሎሬት ፀጋየ ገብረ መድህን ያሉ ገጣሚያን፣ እንደ እጅግአየሁ ሽባባው ያሉ ሙዚቀኞች፣ እንደ ሓሰን አማኑኤል ያሉ አዝማሪዎች፣ እንደ መክሊታቸው አድዋን አወድሰውታል። ተጠብበውለታል፣ ባለቅኔዎች ተቀኝተውለታል። የኪነጥበቡ ዘርፍ የአድዋን ትውፊት በተለያየ መንገድ ለትውልድ በማሸጋገር ዘመናትን ማሻገር የቻለ ባለውለታ ነው።
የአድዋ ድል ቀደምቶቻችን ውድ መስዋዕትነት ከፍለው ያጎናፀፉን መሆኑን ጂጂ “አድዋ” በሚለው ዜማዋ ውስጥ ገልፃዋለች።
“የተሠጠኝ ህይወት ዛሬ በነፃነት
ሰው ተከፍሎበታል በደምና በአጥንት”
በነፃ እንድንኖረው የተሰጠን የዛሬ ሕይወታችን አስቀድሞ ቀደምቶቻችን እምቢ ለነፃነት ብለው አጥንታቸውን ከስክሰው ነፃነት ነጣቂውን ሰብረው አሸንፈው ወደ መጣበት መመለስ መቻላቸውን የሚያሳይ ጠንካራ ስንኝ ነው።
“ምኒልክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ
ግብሩ እንቁላል ነበር ይህን ጊዜ ሀበሻ”
ዘለሰኛው በመሳጭ ቅላፄ የአድዋን ድል የነፃነት ፋይዳ አሳይቷል። ምኒልክ በመወለዱ ኢትዮጵያን ለመውረር የተነሳውን ሀይል ለመመከት ቆርጠው በመነሳት የአድዋን ጦርነት በመምራት ጠላትን ድል ነስተው ከባርነት ዳንን።
እጅግአየሁ ሽባባው በጥበባዊ ቃላት አድዋን ስታዜም፦
“አድዋ ዛሬ ናት አድዋ ትናንት
መቼ ተነሱና የወዳደቁት”
በማለት አድዋን በዛሬ እና በትናንት ትገልፀዋለች።
የአድዋ ድል ትውልድ አደራውን ሳንረሳ ዛሬም አንዲያስታውሰው አድርጋለች- ጂጂ።
በሀገር ፍቅር ቀስቃሽ ሙዚቃዎቹ የሚታወቀው ቴዲ አፍሮ በአድዋ ታሪክ ላይ የተመሰረተ አስደናቂ ሀይል ያለው ‘ጥቁር ሰው’ እያለ አቀንቅኗል።ኢትዮጵያውያን ሀገር ተወረረች ሲባሉ ቀፎው እንደተነካ ንብ ሆ! ብለው በቁጣ ይነሳሉ። ለዚህም ማሳያ ስለሆነው የንጉሡ ክተት ነጋሪት ያወሳል። ምኒልክ በጥቅምት እኩሌታ ወረኢሉ እንገናኝ ብለው ራሳቸው ንጉሡ በወኔ ዘመቱ፣ ወኔው ተቀጣጥሎ በሕዝቡ ውስጥ ተዛመተ፤ ይህ የተቀጣጠለው ወኔ ለአፍሪካ ድል አስገኘ።
“ኑ አድዋ ላይ እንክተት ያ የጥቁር ንጉሥ አለና
የወኔው እሳት ነደደ ለአፍሪካ ልጆች ድል ቀና”
ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን አድዋን በግጥም ወደር የለሽ ችሎታው ተጠብቦበታል።
“ዋ …አድዋ !…
ያንቺን ጽዋ ያንቺን አይጣል
ማስቻል ያለው አባ መቻል
በዳኘው ልብ በአባ መላው
በገበየሁ በአባ ጎራው
በአባ ነፍሶ በአባ ቃኘው
በለው ብሎ በለው በለው”
ፊታውራሪ ገበየሁ ወይም አባ ጎራው ባልቻ አባ ነፍሶ በአድዋ ጦርነት ግምባር ቀደም ከነበሩት ጀግኖች መካከል ይጠቀሳሉ።
“የአድዋ ሥላሴን ጠላት አረከሰው
ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰው”
“ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ
መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ”
ብሎ ባልቻ ሳፎን በፈረስ ስማቸው ባልቻ አባ ነፍሶን የመድፍ ዘዋሪ አድርጓቸው ዋለ።
“በገበየሁ በአባ ጎራው
በአባ ነፍሶ በአባ ቃኘው
በለው ብሎ በለው በለው”
ብሎ የግጥሙ አውራ ሎሬት ፀጋየ ገብረመድህንን ያስታውሳል።
በአድዋ ጦርነት ወቅት ለድሉ አስተዋጽኦ ካበረከቱት ጀግኖች ውስጥ አዝማሪዎች አይረሱም። በየጦር አውዱ እየተገኙ ትልቅ ስራ መስራታቸው ሁሌም ከጀግኖቹ ጎን ለጎን ይታወሳሉ። ከእነዚህ መካከል ከወሎ የበቀሉት፣ በነገሥታቱ እና በመኳንንቱ ዘንድ የተከበሩ የነበሩ በሐሰን አማኑኤል የተባሉ አዝማሪን ማውሳት ይገባል። ፡፡ በዋናነት የንጉሥ ሚካኤል አዝማሪ ቢሆኑም በዐጼ ዮሐንስም በዐጼ ምኒልክም ዘንድ እንዲሁ ተወዳጅ ነበሩ፡፡ ከዓድዋ ጋር በተያያዘ ስለወሎው ንጉሥ ሚካኤልና ስለታላቁ ጀግና ፊታውራሪ ገበየሁ (አባ ጎራው) ሐሰን አማኑ የሚከተሉትን የሙገሳ ግጥሞች ተቀኝቷል። ስለንጉሥ ሚካኤል እንዲህ አሉ፦
ማን በነገረው ለጣሊያን ደርሶ፤
ሚካኤል መጣ ረመጥ ለብሶ።
ስለፊታውራሪ ገበየሁ የተገጠሙት ሁለት መንቶዎች ግን በስፋት የሚታወቁ ናቸው። የነዚህም ገጣሚ ሐሰን አማኑ ነው።
ታጭዶ ሲወቃ፣ ዐድዋ ላይ ገብስ፤
አናፋው ዘልቆ፣ (ጎራው) በመትረየስ።
ዐድዋ ሥላሴን፣ ጥሊያን አረከሰው፤
ገበየሁ በሞቴ፣ ግባና ቀድሰው።
እያሉ ዘመን ተሻጋሪ በሆኑ ግጥሞቻቸው አወድሰዋል። በጥቂቱ ለማንሳት ሞከርን እንጂ በርካቶች ስለ አድዋ ገጥመዋል፣ ዘፍነዋል፣ ተቀኝተዋል። ብቻ ኪነ ጥበብ አድዋ ትናንት አድዋ ዛሬ እንዳለች ታላቋ ጂጂ የኪነጥበቡ ዘርፍ በአድዋ ድል ዘመናትን ተሻግሮ ስሜቱ እንደጋለ ለትውልድ በማስተላለፍ ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል። እኛም መልካም የአድዋ ድል በዓል እየተመኘን በዚሁ አበቃን።
(መሰረት ቸኮል)
በኲር የካቲት 24 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም