ካሽሚር

0
96

ከታሪክ አኳያ ካሽሚር የሚለው ቃል በምእራባዊው የሂማሊያ ተራሮች ያለውን የካሽሚር ሸለቆ ብቻ የሚወክል ነበር። አሁን ላይ ደግሞ ሰፊ ግዛትን የሚወክል ከአፍጋኒስታን፣ ከቻይና፣ ፓኪስታን እና ሕንድ ጋር ድንበር የሚጋራ ሰፊ ነገር ግን አጨቃጫቂ  መሬት ነው። ይህኛውን ካሽሚር ስናነሳ ሶስት ወሳኝ ስፍራዎችን ማመላከት ተገቢ ነው።

 

አንደኛው የሕንድ ጃሙ እና ካሽሚር ግዛት ነው፤  ሰሜናዊ የሕንድ ግዛት ሲሆን ወደ 10 ነጥብ 1 ሚሊዮን ያህል ሕዝብ የያዘ እና 56,665 ስኩዌር ማይል ስፋት ያለው መሬት ነው።  የጃሙ እና ካሽሚር ግዛት አንዱ ነው። በሁለተኛነት ሰሜናዊ ፓኪስታን ውስጥ የሚጠቃለለው አዛድ ካሽሚር ሲሆን ሶስተኛው ክፍል አክሳይ ቺን የተባለው በቻይና ቁጥጥር ስር የሆነው በጣም ተራራማ የሆነው የሂማሊያ ክፍል ነው።

 

ጀማሙ እና ካሽሚር የሚባለው ይህ የህንድ ግዛት በሦሥት አውራጃዎች የተከፈለ ሲሆን የካሽሚር ሸለቆ፣ ጃሙ፣ እና ላዳክህ ይባላሉ። የሦሥቱ አውራጃ ኖኗሪዎች የተለያዩ እምነት ተከታዮች እና የተለያዪ ቋንቋችን ተናጋሪ ናቸው። የካሽሚር ሸለቆ ዘጠና በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ሙስሊም እና የካሸሚርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ናቸው። የጃሙ ሕዝብ ደግሞ 56 በመቶ ሒንዱ 44 በመቶው ደግሞ የሙስሊም ተከታይ ሲሆኑ አብላጫው ሕዝብ የዶግሪ ቋንቋ ተናጋሪ ናቸው። የላዴክህ አውራጃ ደግሞ 59 በመቶ የቡድሂዝም እና 49 በመቶው የእስልምና ተከታይ የሆኑ በአብዛኛው የቲቤትኛ ቋንቋ ተናጋሪ ናቸው።

 

ሁለተኛው አዛድ ወይም ነፃዋ ካሽሚር (ወይም በፓኪስታን የተያዘ ብላ ሕንድ የምታውቀው ክፍል) ከፓኪስታን ሰሜንምስራቅ የሚገኝ 5ሺ 134 ስኩዌር ማይል የሚሸፍን ክፍል ነው። አብላጫው ሙስሊም የሆነ በብዛት  የፓሃሪ እና የፑንጃብ ተናጋሪ ሕዝብ የሆኑ ወደ 3.2 ሚሊዮን ሰዎች የሚኖርበት የካሽሚር አካል ሲሆን ዋና ከተማዋ ሙዛራፋባድ ይባላል።

ሦስተኛው ሰሜናዊው የፓኪስታን አካባቢዎች ነው፤ ከ27ሺ 990 ስኩዌር ማይል ስፋት ያለው 1.8 ሚሊዬን ሕዝብ የሚኖርበት አብዛኛዎቹ ሙስሊሞች ሲሆኑ የፓሽቶ እና ኡርዱ ተናጋሪዎች የሚኖሩበት ሌላው የካሽሚር ክፍል ነው።

እነዚህ ሶስት ንኡስ ክፍሎች የሚያካትተው አጠቃላዩ ክልል እንግዲህ እስከ አሁን ህንድ እና ፓኪስታን ጠቅልለን ሙሉውን ክፍል መግዛት ይገባኛል እያሉ የሚወዛገቡበት ክልል ነው። ከእነዚህ ከሶስቱ ክልሎች በተጨማሪ ደግሞ በቻይና የተያዘው አክሳይ ቺን የተባለው እና ሕንድ እና ቻይና በይገባኛል የሚወዛገቡበት ሰው የማይኖርበት በተራራሮች የተሞላው ክልል መካከል ይገባል።

 

እስከ 1938 ዓ.ም ያለው ታሪክ

የካሽሚር ሸለቆ የጥንታዊው እና የመካከለኛው ዘመናት  የሳንስክሪት እና የቡድሂስት አስተምህሮ እና የስነ ፅሁፍ መፍለቂያ ማእከል  ነበር። በአስራ ሶስተኛው ክፍለ ዘመን ሙስሊሞች ከማካከለኛው እስያ ወደ ካሽሚር መሰደድ የጀመሩበት ጊዜ ነበር። እናም አካባቢው በሙስሊም ስርወ መንግሥት አስተዳደር ስር ገባ። አብዛኛው የካሽሚር ሕዝብም በ14ኛው ክፍለ ዘመን ላይ በሰላማዊ መንገድ ወደ እስልምና እምነት ተቀይረዋል። ካሽሚር ሰፊ እስላማዊ አካባቢ ሆነ። በ1578 ዓ.ም በሕንዱ የሙግሃል ስርወ መንግስት ቁጥጥር ስር በገባችበት ወቅት ራሱ አብዛኛው ክፍሏ ሙስሊም ነበር። መዲናውን ደልሂ እና አግራ ላይ ያደረገው የሙግሃል ስርወ መንግሥት እስከተዳከመበት 1750 ዓ.ም ድረስ ካሽሚርን የግዛቱ አካል አድርጓት ቆይቷል። በዚህ የሙግሃል አስተዳደር በተዳከመበት ወቅት አካባቢውን አህመድ ሻህ አብዳሊ የተባለ ገዢ ተቆጣጥሮ ያዛት እና የአፍጋኒስታን ግዛት አካል አደረጋት። በ1811 ዓ.ም በህንድ የሚገኘው የእንግሊዞች ኢስት ኢንዲያ ካምፓኒ ተቀናቃኝ የሆነው የሲክህ ስርወ መንግሥትአካባቢውን ከአፍጋኖች እጅ ወስዶ እስከ 1838 ዓ.ም  ድረስ የካሽሚር ሸለቆን በስሩ አስተዳድሮታል።

 

ካሽሚር የምድረ ላይ ገነት እስከመባል የደረሰች እጅግ ውብ፣ ተስማሚ የአየር ንብረት እና ከማንም ጋር አብሮ መኖር የሚችል መስተጋብር የተላበሰ ማህበረሰብ የሚኖርባት ተወዳጅ ስፍራ እንደሆነች ብዙዎች ይመሰክሩላታል። ስለሆነም ካሽሚር እነዚህ የተለያዩ ማንነቷ ሌሎች እንዲማልሉባት ካደደረጉ ምክንያቶች መካከል የጠቀሳሉ። የካሽሚር ተፈጥሯዊ አቀማመጥ እጅግ ተፈላጊ አድረጓታል። ለአብነት በሕንድ እና በመካከለኛው እስያ መካከል ይደረግ ለነበረው የንግድ ልውውጥ ዋና መተላለፊያ ስፍራ ነበረች። በዚህ ላይ በዓለማቀፍ ደረጃ ተወዳጅ የሆነውን፣ ከ16ኛው ክፍለዘመን ጀምሮ እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የዓለም ገበያ አስፈላጊ ሸቀጥ ሆኖ የዘለቀውን ፣ የካሽሚር  መከናነቢያ ልብስ አምራች በመሆኗም የማይመኛት የለም ይባላል። ዛሬም ድረስ በእኛም ሀገር ካሽሚር የሚባል የጣቃ ልብስ እንደፋሽን ሆኖ የነበረውም ከካሽሚር ጋር የሚገናኝ ይመስላል።

የካሽሚር አካባቢ ሌላው አማላይ ነገር ተፈጥሯዊው ውበቷ እና ከሰሜናዊው የሕንድ አምባዎች እጅግ የተለየው ደጋማ የአየር ንብረት ስለነበራት ነው። እንደውም ብዙ ጊዜ በሂማሊያ ተራሮች ተከቦ የሚገኝ ሸለቆዋ እና በሀይቆች እና በወንዞች የተሞላ መሬት በመሆኗ በተደጋገሚ ጊዜ ነዋሪዎቿ እና ገዢዎቿ እንደ ምድር ገነት እድርገው ይቆጥሯት ነበር።

 

የብሪታኒያ እጅ በካሽሚር

አካባቢውን በኢስት ኢንዲያ ካምፓኒዋ በኩል አስሳ በእጇ ለማስገባት የቋመጠችው ሌላኛዋ ሀገር ታላቋ ብሪታኒያ በካሽሚር ክልል ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ፣ በምርቶቿ፣ በአየር ንብረቷ፣ እንዲሁም በተፈጥሮ ውበቷ ከበፊቶቹ ገዥዎቿ በበለጠ ሁኔታ ተመኝታት ነበር። መማለል ብቻ ሳይሆን በ1830ዎቹ የሲክህን ስርወ መንግሥት በማሸነፍ በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ገዥዎች የተያዙ የነበሩ ክፍሎችን ወደ አንድ በማጋመድ የጃሙ እና ካሽሚር ክልላዊ መንግሥት ፈጠረች። ኢስት ኢንዲያ ካምፓኒም  በመቀጠል የካሽሚር ሸለቆ፣ ጃሙ፣ ላዳክህ፣ ጊልጊት የተባሉትን ሰሜናዊ ክልሎችን ወደ አንድ አመጣቸው። እነዚህን ሁሉንም አሁን የሚያነታርኩትን ስፍራዎች ነበር በ1838 ዓ.ም ወደ አንድ አካል በማዋሀድ የጃሙ እና ካሽሚር ግዛት እንዲባል ያደረገው።

 

ካምፓኒው ከአፍጋኒስታን ጋር በነበረው ጦርነት ያገዛቸውን ከጃሙ የአካባቢ የጎሳ አለቃ ውስጥ ታማኙን መሪ በአዲሱ ግዛት ላይ የአካባቢው ገዥ አድርጎ ሾመው። ስለሆነም ክልሉ በቀጥታ በቅኝ ገዥው መንግሥት የሚመራ ሳይሆን፣ በተዘዋዋሪ በካምፓኒው እና በብሪታኒያው ንጉሥ ይታዘዝ ነበር።  በዚህ መካከል ተከታታይ የሆኑ መሪዎች በመንግሥቱ ውስጥ ያልተገደበ ስልጣን ይጠቀሙ ነበር።  እነዚህ ገዚዎች ዶግራ፣ ሂንዱ እና ከካሽሚር ያልሆኑ መሪዎች ሲሆኑ፣ በካሽሚር ሸለቆ ወይም በላዳክህ ክልል ላይ ለማስተዳደር ያላቸው ተቀባይነት ያነሰ ነበር፤  ይህም በካሽሚሮች እና በሙስሊሞች ላይ ካሽሚር ያልሆኑት እና ሂንዱዎች እንዲሾሙ በሚያበረታታው ፖሊሲ አማካኝነት ነገሩን የከፋ አደረገው። ይህ በካሽሚር ሸለቆ ውስጥ ያለውን አመራሩን በመቃወም በ1910ሮቹ እና 20ዎቹ ሀላፊነት የሚሰማው መንግሥት እንዲኖር እና በ1930ዎቹም አካታች መንግሥት እንዲመሰረት የሚጠይቅ ሰፊ ንቅናቄን ፈጠረ። እነዚህን መብቶች የሚጠይቀው በካሽሚር ያለው ዋናው የፖለቲካ ድርጅት በ1920ቹ ስሙን የመላው የጃሙ እና ካሽሚር ብሄራዊ ኮንፈረንስ በሚል ተሰየመ። በ19030ዎቹ የነበረው የድረጅቱ መሪ ሸክ አብዱላህ በብሪቲሽ ህንድ ውስጥ ከሚታገለው የህንድ ብሄራዊ ኮንግረስ ጋር ጥብቅ ትስስር ፈጥሮ ነበር።

 

የሕንድ ነፃነት እውንነት አይቀሬ መምሰሉ በጨመረበት ሁኔታ እና የብሪቲሿ ሕንድ ልትከፋፈል መሆኑ ግልፅ ሲሆን፣ ለብሪቲሽ ዘውዳዊ አስተዳደር ተጠሪነት ኖሯቸው የተመሰረቱት ራስገዝ የብሪቲሽ ባለሟሎች የሆኑት 500 የሚሆኑ የክልል አስተዳደሮች እጣ ፋንታ ምን ሊሆን ነው የሚል ጥያቄ መጫሩ አልቀረም።በአጭሩ የቅኝ ገዥው አስተደዳደር እነዚህን ልዑላዊ አስተዳዳሪዎች አንዴ የሕንድ ግዛቱን ለቆ ከወጣ በኋላ ከብሪታኒያ ምንም አይነት ጥበቃ እንደማይደረግላቸው እና  ከሕንድ ወይ ከፓኪስታን ጋር የመቀላቀል ምርጫ እንዲያደርጉ አስታውቋቸው ነበር።

ለአብዛኞቹ ግዛቶች ይህ  ያን ያህል ከባድ አልነበረም፣ ምክያቱም እንደየ መልካምድራዊ አቀማመጣቸው ሕንድን ወይም ፓኪስታንን በቀላሉ መርጠዋል። ነገር ግን ለጥቂት ግዛቶች ግን በርካታ ችግሮችን አስነስቷል።

 

ከእነዚህ ግዛቶች አንዱ የጃሙ እና ካሽሚር ነበር። በአቀማመጡ ምክያት ከሕንድ ወይም ከፓኪስታን መላምታዊ ምርጫ ማድረግ ነበር የሚችሉት። በዚህ ላይ ደግሞ አብላጫው ሕዝብ ሙስሊም ነበር። የካሽሚርን ምርጫ ካወሳሰቡ ሌሎች በርካታ ምክንያቶች ውስጥ መሪው ሂንዱ ነበር  እና የመቀላቀል ውሳኔ የማሳለፍ ሕጋዊ ስልጣን ነበረው፤ ይሁን እንጂ ነፃ ሀገር የመሆን ህልምም ነበረው። ብሄራዊ ኮንፈረንስ የተባለው ዋነኛው የፖለቲካ ድርጅት ከሕንድ ብሄራዊ ኮንግረስ ጋር ጥብቅ ትስስር የነበረው በመሆኑ ከሕንድ ጋር ወደመቀላቀል አዝማሚያ ያዘነብል ነበር፤ ነገር ግን የገዛ መሪው በተለያዩ ጊዜያት የራስ ገዝነት እድል መኖሩን ወይም ከሕንድ እና ከፓኪስታን ጋር በስምምነት የጋራ አስተዳደር እንዲኖር አስተያየት ያቀርብ ነበር። በካሽሚር ሸለቆ ውስጥ የሚኖሩ አብዛኛው ሕዝብ ድርጅቱን ሲከተል፣ የጃሙ ሙስሊሞች ደግሞ ይበልጥ ወደ ፓኪስታን አዘነበሉ። በአንፃሩም የላክህ ሕዝብ እና የጃሙ ሒንዱዎች ፍላጎት ከሕንድ ጋር መሆን ነበር።

 

የካሽሚር ግጭት መወለድ

እ.አ.አ በነሀሴ 14 እና 15 1947 ዓ.ም ፓኪስታን እና ሕንድ በቅደም ተከተል ረብሻ፣ ግራ መጋባት፣ እና ሁከት በታጀበ ሁኔታ ነፃነታቸውን ከእንግሊዝ አግኝተው ነበር። የካሽሚሩ የአካባቢ  መሪ ሀሪ ሲንግህ በቅልቅሉ ዙሪያ ሳይወስን ቀጠለ። ነፃ ሀገር የመሆን ሃሳብ አስተናገደ፣ እንዲሁም ፓኪስታንን ሕንድንም እያማተረ ሲያወላውል ባለበት ከአንዳንድ የጎሳ ታጣቂዎች አመፅ ተቀሰቀሰበት። በዚህ ወቅት ፓኪስታን አማፂያኑን በወታደራዊ ድጋፍ እያገዘች መሆኑን ሲያውቅ የካሽሚሩ ገዢ ወደ ሕንድ ድጋፍ ይጠይቃል ነገር ግን የሕንድ ወታደር ወደ ስፍራው ከመሰማራቱ ፊት ካሽሚርን ከሕንድ ጋር የማቀላቀል ስምምነት በ1938 ዓ.ም በጥቅምት ወር ላይ ተፈራረሙ።

እናም የሕንድ ጦር የካሽሚሩን ገዢ ለመታደግ ሲዘምት ከፓኪስታን ጦር ጋር ተላተመ። በሁለቱ ሰራዊቶች መካከል ጦርነት እንዳገረሸ ሕንድ ለተባበሩት መንግሥት ድርጅት ጽሕፈት ቤት ጣልቃ እንዲገባ ጠየቀች።

 

የመንግሥቱ ድርጅት ጥያቄውን ለመመለስ ክልሉ ወደ ሕንድ ወይም ወደ  ፓኪስታን እንዲቀላቀል የሪፈረንደም ምርጫ ለማድረግ ተወያየ። ይሁን እንጂ ሁለቱም ሀገራት ሪፍረንደም ከመካሄዱ በፊት ክልሉ ከወታደራዊ ቀጠናነት እንዲፀዳ በቀረበው የስምምነት ሀሳብ ላይ አልተስማሙም። ሐምሌ 1941 ዓ.ም  ላይ ፓኪስታንና ሕንድ የተኩስ አቁም ቀጠና እንዲኖር በመንግሥታቱ ድርጅት በቀረበው መሰረት ስምምነት ፈረሙ እና ክልሉ ተከለ።

ሁለተኛው ጦርነት የተከሰተው በ1957 ዓ.ም  ነበር። በመቀጠልም በ1991 ዓ.ም  ላይ ሕንድ በፓኪስታን ከሚደገፉ ኃይሎች ጋር አጭር የሚባል  ግጭት አድርጋ እንደነበር የቢቢሲ ዘገባ ያሳያል። በዚያ ወቅት ሁለቱም ሀገራት ኒኩሌር የታጠቁ ሀገራት ዝርዘር ውስጥ ገብተው ነበር። አሁንም ውጥረቱ እንደቀጠለ ሲሆን እያንዳንዳቸው ክልሉን የመጠቅለል የቆየ ፍላጎታቸውን ማሳካት ይፈልጋሉ። የካሽሚር ግጭት ወደፊት ምን እጣ ፋንታ ይኖረው እንደሆነ ባይታወቅም የሁለቱ የንትርክ ምንጭ እንደሆነ ግን ቀጥሏል።

(መሠረት ቸኮል)

በኲር የሰኔ 2 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here