ካንሰር እና መከላከያዎቹ

0
134

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን የካንሰር ታማሚዎችን ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ በርካታ ሰዎችም በዚህ በሽታ ከአጠገባችን በሞት ሲለዩ እየተመለከትን ነው፡፡ ታዲያ ከዕለት ተለት ሥር እየሰደደ ብዙዎችን እያሰቃየ ለሞት የሚዳርገው ካንሰር ምንድን ነው? የሚለውን ለማወቅ በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ በኪዳነ-ምሕረት የሕክምና ማዕከል እና በአፊላስ ሆስፒታል የካንሰር ምርመራ ወይም ፓቶሎጂ ስፔሻሊስት ሐኪም ዶ/ር በረከት አማረ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡

ዶ/ር በረከት እንዳስረዱት ካንሰር ማለት በሰውነት ውስጥ ያሉ ሕዋሶች ባልተለመደ መንግድ ወይም ከቁጥጥር ውጪ የሚራቡበት ሁኔታ ነው፡፡ እነዚህ ሕዋሳት በመራባት እና አንድ ላይ በመሆን እብጠት በመፍጠር እንዲሁም ከተፈጠሩበት ወይም ከተነሱበት አካባቢ ያሉ የሰውነት አካሎቻችንን በመውረር አለፍ ሲልም የደም ሥሮችን በመቦርቦር እና በመበጣጠስ በሰውነታችን በሚገኙ በማንኛውም የሰውነት ቀዳዳ በማለፍ ወደተለያዩ አስፈላጊ ወደሆኑ የሰውነት አካሎቻችን በመሄድ ጉዳት  ያደርሳሉ፡፡

ማንኛውም ያበጠ ነገር ሁሉ ካንሠር ማለት አይደለም የሚሉት ዶ/ር በረከት  የሰውነት የሕዋሳት መራባት ሁለት አይነት ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ አንደኛው ከፍተኛ የሆነ ጉዳት የማያደርስ ሞኝ እጢ ሲሆን ሁለተኛው ጉዳት የሚያስከትል (ለሕልፈት ሕይዎት) የሚዳርግ አደገኛ ዕጢ (ካንሰር) ነው፡፡ ሞኝ ዕጢ ያልተፈለገ የሕዋሳት መራባት ሆኖ ሳለ እዛው ከተነሳበት ከጀመረበት ቦታ ላይ ብቻ የሚገኝ ነው፡፡ በቀላሉም በቀዶ ጥገና ማስወገድ ይቻላል፡፡

አደገኛ ዕጢ (ካንሰር) የሚባለው ግን ከቁጥጥር ውጪ የሚራባ ሕዋሳት ሆኖ ሳለ ከተነሳበት አካባቢ እና በዙሪያው ያሉ ጤነኛ ሕዋሳትን የሚወር፣ ሥራቸውን የሚያጠፋ እና ጉዳት የሚያደርስ ሊሆን ይችላል፡፡ ለሕይወት አስፈላጊ ወደ ሆኑ (ቫይታል ኦርጋን) የውስጥ የሰውነት ክፍሎች በመሄድ ለሞት የሚያደርስ በሽታ ነው፡፡

በዓለም እና በኢትዮጵያ ያለው የካንሠር ሁኔታ ምን ይመስላል?

የካንሰር ስርጭት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ሁኔታ ባለሙያው ሲያብራሩ እ.አ.አ በ2022 የዓለም ጤና ድርጅት ባደረገው ጥናት መሠረት  ወደ 20 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በዓለምአቀፍ ደረጃ ካንሠር ተገኝቶባቸዋል፡፡ ከነዚህ ሰዎች ግማሽ ያህሉ ወይም 9 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በዛው ዓመት በሕመሙ ምክንያት ሞተዋል፡፡

ካንሰር በጾታ ያለበት ሁኔታ ተለይቶ ሲታይም በዓለማችን በሴቶች ላይ ከሚከሰቱ የካንሠር ሕመሞች መካከል የመጀመሪያው የጡት ካንሠር ነው፡፡ ሁለተኛው ከሳንባ ወይም ከመተንፈሻ አካላት ጋር የተገናኙ የካንሰር አይነቶች ሲሆኑ በሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ደግሞ የትልቁ አንጀት ካንሰር ነው፡፡ በወንዶች ላይ በአንደኛ ደረጃ የሚከሰተው የፕሮስቴት (በወንድ የመራቢያ አካላት ላይ የሚነሳ) ካንሰር ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ከሳንባ እና ከመተንፈሻ አካላት የሚነሳ ካንሠር ነው፡፡ ከትልቁ አንጀት የሚነሳ ካንሰር ደግሞ በሦስተኛ ደረጃ ያጠቃቸዋል፡፡ ባለሙያው ሌሎች የሰውነት አካሎችም ላይ የሚነሱ ካንሰሮች እንዳሉ ነው  ያብራሩት፡፡

በኢትዮጵያ ካንሰር ያለበትን ሁኔታ ሲያስረዱም በሀገሪቱ በደንብ የተጠና ጥናት የለም፡፡ ይሁንና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጥቁር አንበሳ  ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አጋዥነት በአዲስ አበባ ከተማ በተቋቋመ ካንሰር ሪጀስትሬሽን በሚባል ተቋም በ2015 ዓ.ም በተደረገ ጥናት ወደ 62 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች  ካንሰር ተገኝቶባቸዋል፡፡ ሁለት ሦስተኛው የሚሆነውም  ካንሰር በሴቶች ላይ  ሪፖርት የተደረገው ሲሆን ከዚህ ውስጥ አንድ ሶሰተኛ የሚሆነውን የጡት ካንሰር በመውሰድ በአንደኘነት ይጠቀሳል፡፡

በሁለተኛነት የማሕጸን ጫፍ ካንሰር ነው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ሪፖርት የተደረገው የትልቁ አንጀት ካንሰር ነው፡፡ ከዓለም አቀፍ የካንሰር ሁኔታ ጋር ሲነጻጸር በሁለተኛ ደረጃ የሚገኘው የሳንባ ካንሰር ነበር፤ በኢትዮጵያ ግን የማሕጸን ጫፍ ካንሰር መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ባደጉት ሀገራት የማሕጸን  ጫፍ ካንስር ከአንድ እስከ አስር ካሉት ዝርዝሮች ወጥቷል፡፡ ይህ የሆነበት የማሕጸን በር ጫፍ ካንሰርን  መከላከል ስለሚቻል ያደጉት ሀገራት ከፍተኛ የመከላከል ሥራን በመሥራታቸው ነው፡፡ በኢትዮጵያ በወንዶች ላይ ከሚከሰቱ የካንሰር አይነቶች ቅደም ተከተሉ ይለያይ እንጂ  በዓለም ላይ ካለው የወንዶች የካንሰር ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡

ለካንሰር በሽታ አጋላጭ ምክንያቶች

ባለሙያው የካንስር ሕመም መነሻው ይህ ነው ተብሎ ለመናገር እንደሚያዳግት ነው የተናገሩት፡፡ ሆኖም አጋላጭ ምክንያቶች የሚባሉትን የዘረዘሩ ሲሆን እነሱም አኗኗር፣ በዘር (የቅርብ የቤተሰብ አባላት ይዟቸው ከነበረ) አንደኛው አጋላጭ ነው፡፡

ከአኗኗር ጋር ያሉትን ስናይ ቀይ ወይም ከፍተኛ ጮማ ስጋን አብዝቶ መመገብ፣ በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦች፣ ዝቅተኛ የፋይበር ያላቸው መግቦችን ተመጋቢ መሆን፣ አትክልት እና ፍራፍሬዎችን አዘውትሮ አለመመገብ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ ከፍተኛ የሆነ የአልኮል መጠጥ፣ ሲጋራ ማጨስ፣ የፋብሪካ ብናኞች እና ኬሚካሎች፣ የጸረ ተባይ እና አረም ኬሚካሎች፣ ለከፍተኛ የፀሐይ ጨረር መጋለጥ፣ ሄድ መጣ የሚል ቁስል፣  ኢንፌክሽኖች ወይም ተሕዋሲያን እንደ ሂዩማን ፓፒሎማ ያሉ ቫይረሶች፣  የጉበት ቫይረሶች እና የጨጓራ ባክቴሪያዎች እንዲሁም እድሜው ከ45 በላይ የሆነ ሰውም በካንሰር የመያዝ አጋጣሚው ከፍ ያለ ነው፡፡  ይህ ሲባል ግን በሕጻናት ላይም ካንሠር አይከሰትም ማለት እንዳልሆነና የደም ካንሰር እና የጭንቅላት ካንሰር የመሳሰሉ ካንሰሮች በሕጸናት ላይ ከሚከሰቱ ካንሰሮች መካከል መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

የካንሰር ምልክቶች

ባለሙያው እንዳስረዱት የካንሰር ምልክቶች ካንሰሩ እንደተነሳበት ሁኔታ ይለያያል፡፡ የየራሱ ካንሰር የራሱ የሕመም ምልክት እንዳለው የገለጹ ሲሆን በጥቅሉ ግን ካንሰር ያለበት ሰው ቀስ እያለ የሚታይ የሰውነት የክብደት መቀነስ፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ ከፍተኛ ድካም፣ ካንሰሩ በተነሳበት አካባቢ ሄድ መጣ የሚል የሕመም ስሜት ይኖረዋል፡፡

ካንሰር እንዳለብን በምን ልናውቅ እንችላለን

አንድ ሰው ካንሰር በሰውነቱ ውስጥ መኖሩን ለማወቅ የካንሰሩ አይነት በምርመራ መረጋገጥ አለበት፡፡ በርካታ ምርመራዎች እንዳሉ ያብራሩት ባለሙያው እንደማንኛውም በሽታዎች የሚወሰዱ የደም ምርመራዎች፣ አልትራሳውንድ፣ ራጅ፣ ሲቲስካን እና ኤም አር አይ፣ ኮሎኖስኮፒ፣ የፓቶሎጂ ምርመራዎች በዋነኝነት እንደሚደረጉ ነው ያስረዱት፡፡

ሕክምናዎቹ

ዶ/ር በረከት እንደገለጹት ካንሰርን ለማከም በመጀመሪያ የሕመሙ ደረጃ ምን ላይ ይገኛል? የሚለው መታወቅ አለበት፡፡ ካንሰር ደረጃ  አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት እና አራት ተብሎ ይከፈላል፡፡

ደረጃ አንድ የሚባለው ካንሰሩ ከተነሳበት አካባቢ ብቻ ተወስኖ ሲገኝ ነው፡፡ በደረጃ አንድ ላይ የሚገኝ ካንሰር ያለባቸው ታካሚዎች ሕክምናቸው ቀላል ይሆናል፤ የመዳን እድላቸውም ከፍተኛ ነው፡፡   ካንሰሩ ከተነሳበት አካባቢ ሆኖ ከአጠገቡ ያሉ ሊምፍኖዶችን  ሲይዝ ደረጃ ሁለት ካንሰር ይባላል፡፡ በዚህ ደረጃም ከንሰሩ ሊታከም ይችላል፡፡

ደረጃ ሦስት የሚባለው ደግሞ አጠገቡ ያሉ ደም ስሮችን ይወራል፤ በርቀት ያሉ ፍርንትቶችን የሚያጠቃ ነው፡፡ ደረጃ አራት የሚባለው ደግሞ ካንሰሩ የተለያዩ የሰውነት አካሎችን እና ክፍሎችን ሲያዳርስ ነው፤ ወደ ሳንባ፣ አዕምሮ… ሲሄድ ነው፡፡ ካንሰሩ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደረሰ የሚባለውም ደረጃ ሦስት እና አራት ላይ ሲደርስ ሲሆን የሚደረገው ሕክምናም ውስብስብ እና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ነው፡፡ የሕሙማን የመዳን እድላቸውም ጠባብ ሊሆን ይችላል፡፡

መከላከያዎቹ

ባለሙያው እንደሚሉት የመጀመሪያው የመከላከያ መንገድ ለሕብረተሰቡ ስለካንሰር በሽታ በቂ የሆነ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ በሰፊው መሥራት ነው፡፡ ሌላው ካንሰርን ልንከላከለው የምንችለው የቅድመ ካንሰር ምርመራዎችን በማድረግ ነው፡፡ የትልቁ አንጀት ካንሰርን ከ50 እና 60 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች በአምስት ዓመት አንድ ጊዜ የኮሎኖስኮፒ ምርመራ በማድረግ የቅድመ ካንሰር ምርመራ በማድረግ መከላከል ይቻላል፡፡ ለጡት ካንሰር አንድ እድሜዋ ከ20 ዓመት በላይ የሆናት ሴት የወር አበባ ባየች ከሰባት እስከ 10 ባሉት ቀናት  ቤቷ ሆና ሻወር ስትወስድ ጡቶቿን በእጆቿ በመዳበስ መመርመር ትችላለች፡፡ በዚህም ጠጠር ያሉ ነገሮች በጡቶቿ አሉ ወይ፣ በጡቷ ጫፍ ላይ የሚወጣ ፈሳሽስ አለ ወይ ሚለውን መለየት ያስችላታል፡፡  እነዚህ ነገሮች ከተከሰቱ ደግሞ ወደ ሕክምና ተቋም በመሄድ መመርመር አለባት፡፡ እድሜዋ 40 ዓመት በላይ የሆናት ሴት ደግሞ የማሞግራፊ ምርመራ ከሦስት እስከ አምስት ዓመት አንዴ እየደጋገመች ማሰራት የጡት ካንሰር ለመከላከል እና ቀድሞ ህመሙ ሳይንሰራፋ ለማወቅ ይመከራል፡፡ ሌላው ለማሕጸን በር ጫፍ ካንሰርም መንስኤ የሆነውን ሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስን መከላከል የሚያስችል ክትባትን የግብረ ስጋ ግንኙነት ያልጀመሩ ሴቶችን (እድሜያቸው እስከ 14 የሚገኙትን) ማስከተብ በሽታውን ይከላከላል፡፡  በመጨረሻም የካንሰር ሕክምና የሚሰጡ ተቋማትን ተደራሽነትን በማስፋት፣ በበቂ ሁኔታ የካንሰር ሕክምና የሚሰጡ ባለሙያዎችን በማፍራት፣ የኬሚካል ርጭት ሲደረግ ተገቢውን የኬሚካል ርጭት አለባበስን በመተግበርም ካንሰርን መከላከል እንደሚቻል መክረዋል፡፡

ጤና አዳም

የካንሰር ሕክምናዎች

ቀዶ ሕክምና:- ዕጢውን እና በዙሪያው ያሉትን ሕብረ ሕዋሳት ማስወገድን ያካትታል፡፡

ኪሞቴራፒ፡- የካንሰር ሕዋሳትን ለመግደል ወይም ለማዘግየት መድሃኒቶችን ይጠቀማል፡፡

የጨረር ሕክምና፡- የካንሰር ሕዋሳትን ለማጥቃት እና ለማጥፋት ከፍተኛ መጠን ያለው የጨረር መጠን ይጠቀማል፡፡

ኢምዮኖቴራፒ(Immunotherapy)፡-  የካንሰር ሕዋሳትን ለመለየት እና ለማጥቃት የሰውነትን በሽታ የመከላከል ስርዓት ያጠናክራል፡፡.

የታለመ ሕክምና፡- ብዙውን ጊዜ የተወሰኑ የጄኔቲክ ሚውቴሽን ባላቸው ካንሰሮች ውስጥ ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡

የሆርሞን ሕክምና፡- የካንሰርን እድገት የሚያበረታቱ ሆርሞኖችን ተፅእኖ ለመግታት ወይም ለመግታት ያለመ ነው፡፡

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የጥር 25 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here