“ክለቦች የማኅበረሰቡን ክፍተቶች የመሙላት ኃላፊነት አለባቸው”

0
108

በኢትዮጵያ ብሔራዊ፣ ከፍተኛ እና ፕሪሚየር ሊጎች በተጫዋችነት እና በአሠልጣኝነት ለረጅም ዓመታት ካስቆጠረው አሠልጣኝ አረጋይ ወንድሙ ጋር በክፍል አንድ ቆይታ አድርገናል፡፡ በዋናነት ወደ እግር ኳሱ እንዴት እንደገባ፣ በኋላም ወደ ውትድርናው እንደተቀላቀለ አንስተናል፡፡ በውትድርናው ቤትም መልሶ ወደ እግር ኳስ እንደመጣ አንስተናል፡፡ በዚህ የመጨረሻ ክፍል ደግሞ በተለያዩ ክለቦች የነበረውን ቆይታ እና ስለ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ያጫውተናል፤ ምልከታውን ያጋራናል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

የጥቁር አባይ ክለብን ለከፍተኛ ሊግ አብቅተኸዋል፡፡ በቤቱ ብዙ ትዝታም አለህ፡፡ ዛሬ ላይ ግን ጥቁር አባይ የእግር ኳስ ክለብ ፈርሷል፡፡  ምን ይሰማሀል?

እንደ ጥቁር አባይ ያሉ ክለቦች ሕዝባዊ ተቋማት ነበሩ፡፡ ትርፋማ የሚሆኑትም በሕዝቡ ውስጥ ነው፡፡ ማኅበራዊ ኃላፊነት ሊኖራቸው ይገባ ነበር ብየ ነው የምለው፡፡ ጥቁር አባይ የእግር ኳስ ክለብ መፍረስ አልነበረበትም፡፡ መሰል ተቋማት ለትርፍ የተቋቋሙ አይደሉም፤ ይልቁንም ማኅበራዊ ኃላፊነት ለመወጣት የተቋቋሙ ናቸው፡፡ በተለይ በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚኖሩ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ስነ ልቦናዊ እና ሌሎች ክፍተቶችን የመሙላት ኃላፊነት በተቋማቱ ላይ ተጥሏል፡፡ ስለዚህ የሚመለከታቸው አካላት ጥቁር አባይን እና ሌሎች ክለቦችን መመለስ አለባቸው ብየ አስባለሁ፡፡

በደርግ ጊዜ የነበረው የስፖርት ፖሊሲ እያንዳንዱ ተቋም በስሙ የእግር ኳስ እና የሌሎች ስፖርቶች ክለብ እንዲኖራቸው ያደርግ ነበር፡፡ ይህም ግዴታ ነበር፡፡ ከተቋማት ባሻገር ቀበሌዎች እና ወታደራዊ ክፍሎች ሳይቀር የስፖርት ቡድን መመስረት ግዴታቸው ነበር፡፡ በስፖርታዊ ክንዋኔዎችም ማኅበረሰቡ በተለያዩ ዘርፎች ተጠቃሚ ነበር፤ በመሆኑም የፈረሱ ክለቦች ዳግም ተመሥርተው ወደ እንቅስቃሴ መግባት አለባቸው ነው የምለው፡፡

ወልድያ ከነማ የእግር ኳስ ክለብን ወደ ፕሪሚየር ሊግ ማስገባት ችለህ ነበር፡፡ በወልድያ ከነማ የነበረህ ቆይታ ምን ይመስላል?

ለወልድያ ከነማ ክለብ ልዩ ፍቅር አለኝ፡፡  ስልክ ተደውሎልኝ የወልድያ ከነማን እንዳሰለጥን መታሰቤ ሲነገረኝ እጅግ ታላቅ ደስታ ነበር የተሰማኝ፡፡

አሰልጣኝ ሆኜ ከተመረጥኩም በኋላ ቡድኑን በጥሩ ሁኔታ ለማዋቀር ቀደም ሲል ከነበሩ ልጆች ጋር እና አዳዲስ ልጆችን መልምለን ጠንካራ ዝግጅት ማድረግ ነው የጀመርነው፡፡ በመጀመሪያዎቹ አካባቢ በፕሪሚየር ሊጉ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ ነበር የቆየው፡፡  ጥሩ ቡድን ተሠርቶ ከምጠብቀው ደረጃ ባለመድረሱ አበሳጭቶኛል፡፡ በወቅቱ ቡድኑን ትልቅ ደረጃ ለማድረስ ውስጤ ከተነሳበት መንፈሳዊ ቅናት እና ፍላጎት አንጻር በጣም ጎድቶኛል፡፡

በወቅቱ በፕሪሚየር ሊጉ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ እንኳ ለምን አንደኛ ደረጃን አልያዘም የሚል ጫና ነበር፡፡ በማንኛውም ቦታ ሁለተኛ ደረጃን ይዘህ ለምን አንደኛ ደረጃ አልሆነም የሚል ተቃውሞ አያስፈልግም፡፡ በእግር ኳስ ውስጥ አብዛኞቹ ስኬቶች በሂደት የሚመጡ ናቸው፡፡ የእኛ አጠቃላይ ማኅበረሰባዊ አስተሳሰባችን  አንደኛን እንጂ ሁለተኛ፣ ሦስተኛ፣ አራተኛ እና ሌሎች ከኋላ ያሉ ደረጃዎችን የሚቀበል አይደለም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ይህ አስተሳሰብ አደገኛ ሊሆን ይችላል፡፡

 

ብዙውን ጊዜህን ብሔራዊ ሊግ እና ከፍተኛ ሊግ ላይ አሳልፈሃል፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት በሲዳማ ከነማ ምክትል አሰልጣኝ  ሆነህ ነበር፤ በፕሪሚየር ሊግ የነበረህ ቆይታ ምን ይመስላል?

ወደ ፕሪሚየር ሊግ ለመምጣት ብዙ ዓመት ደክሜያለሁ፡፡ በሙያዊ እውቀት ለመዘጋጀት እና ስልጠናዎችን ለመውሰድ ከፍተኛ ጥረት አድርጌያለሁ፤ ብዙ ዋጋም ከፍያለሁ፡፡ ነገር ግን ለረጅም ጊዜ መንገዱ አልገባኝም ነበር፡፡ አሁን ሦስት መንገዶች እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ አንደኛው ቡድን ይዘህ ማስተዋወቅ ነው፡፡ ነገር ግን እድለኛ ካልሆንህ “ዞርበል” ልትባል ትችላለህ፡፡ ለአብነት ውብሸት መድንን ፕሪሚየር ሊግ አስገብቶ ወርዷል፡፡ እንደገና ነው ባንክን ይዞ መጥቶ ጥሩ አቋም ያሳየው፡፡ ምከንያቱም “የፕሪሚየር ሊግ አሰልጣኝ አይደለም የእንትን አሰልጣኝ ነው” ብለው ይመድቡሃል፡፡

አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ከፋሲል ከነማ ወጥቶ ሲዳማ ቡናን ከያዘ በኋላ አንድ ቀን ተገናኝተን አወራን፡፡ ስለምደባውም በደንብ ነገርኩት፡፡ እሱም አብረን መሥራት እንደምንችል ቃል ገባልኝ፡፡ ወደ ሲዳማ ቡናም ወሰደኝ፡፡ በስልጠናው ከፍ እያልክ በሄድክ ቁጥር ወደ ጨዋታ እና ተጫዋች ማስተዳደር (ማኔጅመንት) ነው የምታተኩረው፡፡ በከፍተኛ እና በብሔራዊ ሊጉ መመሳሰል ቢኖርም የበለጠ የምታተኩረው በሥልጠና ላይ ነው፡፡

ከፍተኛ ሊግ ላይ አሠልጣኙ የበለጠ ስልጣን አለው፡፡ ወደ ላይ ስትወጣ ግን ሥልጣኑ የተጫዋቹም ጭምር ነው፤ ስለዚህ የጋራ ነው ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ተጫዋቹ የእሱ ብስለት እና ዕድሜ ከሚያስተዳድረው በላይ ገንዘብ አለው፡፡ የአሰልጣኙ ታች ነው፡፡ ይሄን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ በውጪ ሀገር በቢሊየን እየተከፈላቸው ከጨዋታ በኋላ ከአሰልጣኙ ስር ነው የሚገቡት፤ በእኛ ሀገር እንደዚያ አይነት ብስለት የለም፡፡ ይህ ደግሞ ስፖርቱን ልጁንም የሚጎዳበት ሁኔታ ከፍተኛ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የተዘጋጄ ጠቅላላ ሁኔታ የለም፡፡ ይህ ማለት የሚያማክር ሰው፣ ገንዘቡን እና ንግዱን እንቅስቃሴውን የሚያስተዳድርለት ሰው እና ሌሎች እንቅስቃሴውን የሚያግዘው ሰው የለም፡፡ ስለዚህ ይሄን ለማጣጣም ከአሰልጣኙ እኩል አስተዳደሩ ሥልጣን አለው፤ ኃይለኛ ነው፡፡ ስለዚህ እነኝህን ነገሮች ስዩም ከበደ ስር ሆኜ መማር ስለነበረብኝ ነው ወደ ሲዳማ ከነማ የሄድኩት፡፡

በከፍተኛ፣ በብሔራዊ እና በፕሪሚየር ሊጎች ሠርተሃል፤ በዚህም ከፍተኛ ልምድ አለህ፤ ከዚህ በመነሳት የሀገራችንን እግር ኳስ ደረጃ እንዴት ታየዋለህ?

በአሜሪካ እና እንግሊዝ ሀገር ከወሰድኳቸው ሥልጠናዎች መካከል አንዱ ተጫዋች እና ጨዋታ ትንታኔ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታዎችን በብስራት ቴሌቪዢን ትንታኔ እሰጣለሁ፡፡ ትንተናውን ስታየው ደስ የሚሉ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ዓለም አቀፍ ሥልጠናዎችን ከወሰድክ በኋላ እና እንደ ሙያተኛ ስትመለከተው  ግን የሀገራችን እግር ኳስ ወዴት እየሄደ ነው ብለህ የምትደነግጥባቸው ነገሮች አሉ፡፡

ወደ ሦስተኛ ሜዳ የምንሸጋገርባቸው ሥርዓቶች፣ በደመ ነፍስ የምትሠራቸውን ነገሮች የምታስተካክልባቸው ነገሮች፣ በሜዳ ውስጥ የሚገጥሙ ችግሮችን መፍትሔ የምታበጅባቸው ስልቶች፣ ይሄን ለማድረግ ደግሞ በአጭር ጊዜ ውሳኔ የመስጠት ጥበብ፣ የጨዋታን ፍጥነት ለመጨመር የሚጠቀሙባቸውን መንገዶች እና እኛ ጋር ያለውን ስታስተውል ትደነግጣለህ፡፡ ስለዚህ እጅግ ብዙ ሥራዎች ይጠብቁናል፡፡

አሠልጣኝ አረጋይ ወንድሙ ወደፊት ምን አቅዷል?

እንደማንኛውም አሠልጣኝ የሀገሬን ብሔራዊ ቡድን የማሰልጠን ሕልም አለኝ፡፡ ከዚያም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀገሬ ጥሩ ውጤት እንድታመጣ ማስቻል እፈልጋለሁ፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ ከቻልኩም በዓለም ዋንጫ የምድብ ጨዋታዎችን አሸንፎ ከነበረው የተሻለ ውጤት ማምጣት ነው እንጂ ብሔራዊ ቡድኑን መያዝ ብቻ አይደለም ራዕዬ፡፡ ብዙ ሰው ብሔራዊ ቡድኑን ማሰልጠን ሕልሙ ነው፤ ነገር ግን ከዚያስ በኋላ የሚለው ይመጣል፡፡ ከዚህ በፊት ሰውነት ቢሻው እና ውበቱ አባተ ቀድመውኛል፤ ብሔራዊ ቡድኑን በማሰልጠን እና የተሻለ ውጤት  በማምጣት ሦስተኛው ሰው መሆን እፈልጋለሁ፡፡

ለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን!

እኔም አመሰግናለሁ!

 

ይቀጥላል

(ቢኒያም መስፍ)

በኲር የጥር 26 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here