ክልል አቀፍ ፈተናዉ እና ዝግጅቱ

0
101

በተያዘው ዓመት ከተመዘገቡ ሦስት ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎች ውስጥ ሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን የሚሆኑትን እያስተማረ የከረመው የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከወርሀ ሰኔ ጀምሮ በሚሰጡ ምዘናዎች የማሳለፍ ምጣኔውን ከፍ ለማድረግ በከፍተኛ ማብቃት ሥራ ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ቢሮዉ ይህንን ያለው የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን ከባለድርሻ አካላት ጋር ሆኖ በገመገመበት ወቅት ነው፡፡ በዚህም በክልል እና ሀገር አቀፍ ፈተና ከ402 ሺህ በላይ ተማሪዎች ይፈተናሉ፡፡ በዚህ ሳምንት ዕትማችን የምንመለከተውም በክልል ደረጃ የሚሰጡ ፈተናዎችን በተመለከተ ተፈታኞችን ለማብቃት እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን ነው፡፡

 

ከክልሉ ትምህርት ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው የ6ኛ ክፍል ፈተና ከሰኔ 5 እስከ 6/ 2017 ዓ.ም ይሰጣል፡፡ ሦስት ሺህ 649  ትምህርት ቤቶች ደግሞ አስፈታኝ ናቸው፡፡ የተፈታኞች ቁጥርም 154 ሺህ 260 ናቸው፡፡

የስምንተኛ ክፍል ፈተናም ከሰኔ 3 እስከ 4/ 2017 ዓ.ም ይሰጣል፡፡   2 ሺህ 642 ትምህርት ቤቶች በአስፈታኝነት ተለይተው በጠንካራ ቅድመ ዝግጅት ውስጥ እንዲያልፉ ሲደረግ በሥራቸው ከ148 ሺህ 256 ተማሪዎችን ያስፈትናሉ፡፡

 

ባለፈው ዓመት የትምህርት እንቅስቃሴያቸው በከፍተኛ ችግር ውስጥ ወድቆ የከረመባቸው ዞኖች በዚህ ዓመት በከፍተኛ ንቅናቄ ወደ ትምህርት እንዲመጡ ያደረጓቸውን ተማሪዎች ለማስፈተን፣ የማለፍ ምጣኔያቸውንም ከፍ ለማድረግ እየሠሩ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ከእነዚህ ውስጥ በ2016 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ ከትምህርት እንቅስቃሴ ውጪ ሆኖ የከረመው የምዕራብ ጎጃም ዞን ይገኝበታል፡፡ በዘንድሮው የትምህርታ ዘመን ደግሞ በዞኑ ከሚገኙ 600 ትምህርት ቤቶች ውስጥ በትምህርት እንቅስቃሴ ውስጥ የከረሙት 79 ትምህርት ቤቶች መሆናቸውን የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ የስጋት ደሴ አስታውቀዋል፡፡ ዞኑ በዓመቱ ተቀብሎ ለማስተማር በዕቅድ የተያዘው የተማሪ ቁጥር 396 ሺህ 549 ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በመማር ላይ የሚገኙት 37 ሺህ 168 ተማሪዎች ብቻ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

 

ባለፈው ዓመት በየትኛውም የክፍል ደረጃ አንድም ተማሪን ለፈተና ያላስቀመጠው ምዕራብ ጎጃም ዞን በዚህ ዓመት ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ የሚገኙ ተማሪዎችን በማብቃት ለማስፈተን እየሠራ መሆኑን አቶ የስጋት አስታውቀዋል፡፡ በተለይም ክልላዊ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ በከፍተኛ ትጋት እየተሠራ ነውም ብለዋል፡፡ አንድ ሺህ 792 ተማሪዎች የስድስተኛ ክፍል እንዲሁም አንድ ሺህ 934 ተማሪዎች ደግሞ የስምንተኛ ክፍል ፈተና እንደሚወስዱ ጠቁመዋል፡፡

 

የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር እስከ መጋቢት 30 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ የተማሪ ምዝገባ ማከናወኑን የመምሪያዉ ኃላፊ ደስታው ዓለሙ አስታውቀዋል፡፡ በዚህም ከባለፈው ዓመት የተሻለ ተማሪ ተቀብሎ የመማር ማስተማር ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡ በዚህም 344 ትምህርት ቤቶች ተከፍተው ከ163 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብለው በማስተማር ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

 

ተማሪን ወደ ትምህርት ቤት ማምጣት ብቻውን ግብ አይሆንም ያሉት አቶ ደስታው፣ አሁንም ድረስ ከ300 በላይ ትምህርት ቤቶች ባይከፈቱም በትምህርት ላይ ያሉትን ማብቃት ላይ ትኩረት መደረጉን ገልጸዋል፡፡ መምህራንን ማሟላት፣ መጻሕፍትን ማዳረስ፣ የማጠናከሪያ እና የማካካሻ ትምህርትን በተጠናከረ ሁኔታ መስጠት፣ የቤተ መጻፍት  አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል  ለትምህርት ጥራት እና ለጊዜ ትኩረት ተሰጥቶ  እየሠሩ መሆኑን አቶ ደስታው አስታውቀዋል፡፡

 

እንደ ኃላፊው ገለጻ በብሔረሰብ አስተዳደሩ በስምንተኛ እና ስድስተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና 18 ሺህ ተማሪዎች እንደሚፈተኑ ታውቃል፡፡ የተሻለ የማስተማር ሥነ ዘዴ ያላቸው መምህራን ተለይተው በትርፍ ጊዜያቸው ለተፈታኝ ተማሪዎች የማካካሻ እና የማጠናከሪያ ትምህርት እየተሰጣቸው  ነው፡፡ ቤተ መጻሕፍትን ቅድሜ እና እሁድን ጨምሮ ሙሉ ቀናት ክፍት ሆነው ተማሪዎች እንዲጠቀሙባቸው እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎችም ቀሪ ጊዜያትን በአግባቡ እንዲያሳልፉ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ሌላው የውጤት ማሻሻል ትኩረት ሆኖ እየተሠራበት ይገኛል፡፡

 

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ሙሉዓለም አቤ (ዶ/ር) በበኩላቸው ክልል እና ሀገር አቀፍ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎችን የማብቃት ሥራ የተጀመረው ከወርሀ ታህሳስ ጀምሮ ነው፡፡ 7 ሺህ 300 የስምንተኛ ክፍል እና 7 ሺህ 400 የስድስተኛ ክፍል ተማሪዎች ለክልላዊ ፈተና እንደሚቀመጡ ተለይተው የማብቃት ሥራ እየተከናወነ መሆኑ ታውቋል፡፡

ይዘቶች በአግባቡ እና በወቅቱ እንዲሸፈኑ ክትትል ማድረግ፣ ጥያቄዎችን እያዘጋጁ ለተማሪዎች በመስጠት ራሳቸውን እንዲፈትሹ ማድረግ፣ ቤተ መጻሕፍትን ሙሉ ቀናት ክፍት ማድረግ፣ የማካካሻ እና የማጠናከሪያ ትምህርትን ተማሪዎች በመረጧቸው መምህራን መስጠት ዋና ዋና የተፈታኞች ማብቂያ ሥራዎች ሆነው እየተሠራባቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

 

በጸጥታ ችግሩ ምክንያት ላለፉት ሁለት ዓመታት የትምህርት ሥራው የተስተጓጎለበት የሰሜን ጎጃም ዞንም በዓመቱ መጨረሻ ለሚሰጠው ክልላዊ ፈተና ተማሪዎችን እያዘጋጀ ይገኛል፡፡ የትምህርት መምሪያዉ ኃላፊ ነጋልኝ ተገኘ በትምህርት ዓመቱ በሁሉም የትምህርት ተቋማት መዝግቦ ለማስተማር የተያዘው ዕቅድ 448 ሺህ 939 ተማሪዎች ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት በማስተማር ላይ የሚገኙት ግን 44 ሺህ 600 ተማሪዎች ብቻ ናቸው፡፡

 

በትምህርት ላይ ያሉትን በማብቃት ዓመቱን በድል እንዲያጠናቅቁ በሚያደርጉ ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርገው እየሠሩ መሆናቸውን አቶ ነጋልኝ አስታውቀዋል፡፡ በዞኑ በስድስተኛ፣ ስምንተኛ እና 12ኛ ክፍል ከአራት ሺህ በላይ ተማሪዎች ይፈተናሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 50 በመቶ የሚሆኑት ክልላዊ ፈተና የሚወስዱ ሆነው መለየታቸውን አስታውቀዋል፡፡

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ እየሩስ መንግሥቱ ክልል ዓቀፍ እና ሀገር ዓቀፍ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎችን ተወዳዳሪ እና ብቁ ለማድረግ የተጠናከረ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡  ትምህርት ቤቶች ለተፈታኝ ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት እየሰጡ ቢሆንም ቁጥራዊ አኃዞች የሚያሳዩት ግን አነስተኛ አፈጻጸም መሆኑን ወይዘሮ እየሩስ ቢሮው የዘጠኝ ወራት ግምገማውን በባሕር ዳር ከተማ ባደረገበት ወቅት አስታውቀዋል፡፡

 

ተፈታኝ ተማሪዎች የተረጋጋ ሥነ ልቦና እንዲኖራቸው የሥነ ልቦና ግንባታ የምክር አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑንም ምክትል ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡  የአዳር ጥናት በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በሚወስዱ ተማሪዎች ብቻ ሳይወስኑ የክልላዊ ተፈታኞች ማብቂያ አድርገው እየሠሩ ያሉ አካባቢዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል፤ ተሞክሮውም ሊሰፋ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የቤተ መጻሕፍት አገልግሎትን ማሻሻል፣ የቡድን ጥናት መፍጠር እና እንዲጠናከር ማድረግ፣ የአዳር ጥናት ፕሮግራምን ማስፋት፣ በሞዴል ፈተናዎች የተማሪዎችን ብቁነት ማረጋገጥ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

 

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here