ክረምት እና ልጆች

0
59

ልጆች እንዴት ናችሁ? ሳምንቱስ እንዴት አለፈ? አሁን ላይ ከአፀደ ህፃናት እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለእረፍት የተዘጉበት ወቅት ነው፡፡ ታዲያ ይህንን ከሁለት ወር ያላነሰ የእረፍት ጊዜ ልጆች በምን እያሳለፉ ይገኛሉ?

ልጆች በክረምት የእረፍት ጊዜያችሁ ምን ለመሥራት አስባችኋል፡፡  የእረፍት ጊዜውን እንዴት እንደሚያሳልፍ እና ምን እቅድ እንዳለው ከአንድ ልጅ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡

ተማሪ ሱራፌል አስናቀ በባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ነው፡፡ በክረምት የእረፍት ጊዜው  ከቤቱ ራቅ ብለው ወደሚገኙ ዘመዶቹ ለጥየቃ እንደሚሄድ አጫውቶናል፡፡ የሚሄድበት አካባቢ ከሚኖርበት አካባቢ ራቅ ያለ ስለሆነ ደግሞ ከዘመዶቹ ጋር ያለውን ግንኙነት ከማጠንከሩና ጥሩ ትዝታ ከመፍጠሩ ባለፈ የዚያን አካባቢ ባሕል፣ ወግ እና እሴት የማየት የመማርና የማወቅ አጋጣሚውን ይፈጥርለታል፡፡

ሱራፌል እንደየአቅሙ ወላጆቹን ማገዝ፣ ከጓደኞቹ ጋር መጫወት፣ አስተማሪ እንዲሁም አዝናኝ ፊልሞችን ማየት (በወላጅ ምርጫ) እና መዝናኛ ስፍራዎች በመሄድ ማሳለፍ በክረምቱ ካቀዳቸው ተግባራት መካከል መሆናቸውን ነግሮናል፡፡ በተጨማሪም ክህሎቱን የሚያሳድግበት ማለትም የሙዚቃ መሳሪያ፣ ስዕል፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖታዊ ትምህርቶች፣ ውዝዋዜ እና ስፖርታዊ ክንውኖችን እንዲሁም ሌሎች ስልጠናዎችን ለመውሰድ አስቧል። እንዲሁም ለሚቀጥለው የትምህርት ጊዜ የሚያግዘውን ማጠናከሪያ ትምህርት በመማር፣ መጻሐፎችን በማንበብ፣ በአካባቢው የሚገኙ የሚጎበኙ ስፍራዎችንና ቴአትሮችን በማየት፣ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ መሳተፍ የክረምት ጊዜውን የሚያሳልፍባቸው ናቸው፡፡

ሱራፌል እንዲህ ሲል ልጆችን ይመክራል፡- ያለ ወላጅ ፈቃድ እና እውቅና ከቤት ርቆ ሄዶ መጫወት፣ የመኪና መንገድ ላይ መጫወት፣ ከአቅማቸው በላይ እና ያልተፈቀደላቸውን ተግባራት ማከናወን፣ ረጅም ጊዜ ስክሪን ላይ ማሳለፍና ውሃ ወደሚያቁሩ ቦታዎች እና ወደ ወንዝ በመሄድ ለመዋኘት መሞከር ተገቢ አለመሆኑንና ለአደጋ ያጋልጣል፡፡ ወላጆችም ልጆቻቸው የእረፍት ጊዜያቸውን በፕሮግራም በአግባቡ እንዲጠቀሙና የክረምት ጊዜያቸው አይረሴ እንዲሆን የማድረግ እና የማገዝ ኃላፊነት አለባቸው፡፡

 

ሞክሩ

  1. ከጠጣሁ የምሞት፤ ከበላሁ የምኖር ማነኝ?
  2. ጥርስ አለኝ መብላት ግን የማልችል፤ እኔ ማነኝ?
  3. የሰዉ ልጅ እንዴት ያለ እንቅልፍ ስምንት ቀን ይጓዛል?

 

መልስ

  1. እሳት
  2. ማበጠሪያ
  3. ማታ እየተኛ

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here