እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ1912 በስዊድኗ ስቶክሆልም ከተማ የተጀመረው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዘንድሮ ለ20ኛ ጊዜ በጃፓኗ ቶኪዮ ከተማ አትሌቶችን አፎካክሮ በውጤታቸው መሠረት ሸልሟል፡፡
ዕድሜ ጠገቡ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከጅማሬው አንስቶ እስካሁን ድረስ ስድስት ፕሬዚዳንቶችን አቀያይሯል፡፡ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ስውዲናዊው ሲግፍሪድ ኢድስትሮም ሲሆኑ እሳቸውን ተከትለው እንግሊዛዊው ሎርድ በርግሌይ፣ ኔዘርላንዳዊው አድሪያን ፓውለን፣ ጣሊያናዊው ፕሪሞ ኒብዮሎ፣ ሴኔጋላዊው ላሚን ዲያክ እና አሁን ተቋሙን የሚመሩት እንግሊዛዊው ሴባስቲያን ኮ የዓለም አትሌቲክስን በፕሬዚዳንትነት ያገለገሉ ናቸው፡፡
በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አሜሪካ በርካታ ሜዳሊያዎችን በመሠብሠብ የክብረ ወሰኑ ባለቤት ናት፡፡ አሜሪካ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድሮች ብቻ 211 የወርቅ፣ 139 የብር፣ 119 የነሐስ፣ በድምሩ 469 ሜዳሊያዎችን በመሠብሠብ የመድረኩን የበላይነት ወስዳለች፡፡
ጎረቤታችን ኬኒያ በዚሁ የውድድር መድረክ ላይ በ72 የወርቅ፣ 60 የብር፣ 50 የነሐስ፣ በድምሩ 182 ሜዳሊያዎችን በመሠብሠብ በዓለም የደረጃ ሠንጠረዡ በሁለተኛነት ሥፍራ ላይ ተቀምጣለች፡፡
ሩሲያ 42 የወርቅ፣ 52 የብር፣ 48 የነሐስ፣ በድምሩ 142 ሜዳሊያዎችን አግኝታ የዓለም ሦስተኛዋ የዘርፉ ስኬታማ ሀገር ሆናለች፡፡ ጃማይካ፣ ጀርመን እና ኢትዮጵያ ደግሞ ከአራተኛ እስከ ስድስተኛ ያለውን ደረጃ የያዙ ሀገራት ናቸው፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ የስድስተኛ ደረጃን የያዘችው በ35 ወርቅ፣ በ40 የብር እና በ33 የነሐስ፣ በድምሩ 108 ሜዳሊያዎችን አስመዝግባ ነው፡፡ይሄው የሀገራችን ውጤት ከጎረቤታችን ኬኒያ ጋር ሲነጻጸር በጣም አነስተኛ መሆኑ የሁለቱን ሀገራት የዘርፉ ተፎካካሪነት ላስተዋለ አካል ቁጭትን የሚያሳድር ነው፡፡
በዘንድሮው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 53 ሀገራት ስማቸውን በሜዳሊያ ሠንጠረዥ ውስጥ አስመዝግበዋል፡፡ በምርኩዝ ዝላይ ውድድር ስውዲናዊው ሞንዶ ዱፕላንቲስ በራሱ ስም ተመዝግቦ የነበረውን ክብረ ወሰን በማሻሻል አዲስ የዓለም ክብረ ወሰንን አስመዝግቧል፡፡ ዘጠኝ የሻምፒዮናው ክብረ ወሰኖችም በቶኪዮ ተሻሽለዋል፡፡
አሜሪካዊቷ የአጭር ርቀት ሯጭ ሜሊሳ ጄፈርሰን በ100 እና በ200 ሜትር ውድድሮች በግሏ የወርቅ ሜዳሊያዎችን ያገኘች ሲሆን አራት በመቶ የዱላ ቅብብልም ከቡድን አጋሮቿ ጋር የወርቅ ሜዳሊያን በማሳካት የሦስት ወርቅ ሜዳሊያዎች ባለቤት ሆናለች፡፡
ኬኒያዊቷ ቢትሪስ ቺቤት በ10 ሺህ እና በአምስት ሺህ ሜትር ሩጫ እንዲሁም የስፔኗ የርምጃ ተወዳዳሪ በሁለት የእርምጃ ውድድሮች ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማጥለቅ በቶኪዮ የደመቁ አትሌቶች ሆነዋል፡፡
በቶኪዮው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አንድ ሺህ 992 አትሌቶች ከ193 የተለያዩ ሀገራት ተወክለው ውድድራቸውን አካሂደዋል፡፡
በመድረኩ አስገራሚ ከተባሉት ውጤቶች ውስጥ ታንዛኒያ በወንዶች የማራቶን ውድድር በአልፎንስ ፍሊክስ ሲምቡ የወርቅ ሜዳሊያ አስመዝግባለች፡፡
ይህ የወርቅ ሜዳሊያ ለሲምቡ እና ለታንዛኒያ የመጀመሪያው የወርቅ ሜዳሊያቸው ሆኖ ተመዝግቦላቸዋል፡፡
በ20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አሜሪካ 16 ወርቅ፣ 5 ብር እና 5 የነሐስ ሜዳሊያዎችን በድምሩ ደግሞ 26 ሜዳሊያዎችን በማግኘት አንደኛ ደረጃ ስትሆን ጎረቤታችን ኬኒያ በ7 ወርቅ፣ በ2 የብር እና በ2 የነሐስ፣ በድምሩ በ11 ሜዳሊያዎች ሁለተኛ ደረጃ፣ ካናዳ ደግሞ በ3 ወርቅ፣ በ1 ብር እና በ1 ነሐስ፣ በድምሩ በ5 ሜዳሊያዎች የሦስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል፡፡
ኔዘርላንድ፣ ቦትስዋና፣ ስፔን፣ ኒውዚላንድ፣ ስውዲን እና ፖርቱጋል በመድረኩ ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማግኘት አትሌቲክሳቸውን እያሻሻሉ ከመጡ ሀገራት ተርታ ተሰልፈዋል፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ በ2 የብር እና በ2 የነሐስ ሜዳሊያዎች ከዓለም የ22ኛ ደረጃን አስመዝግባ ተመልሳለች፡፡
እንደ ቢቢሲ ስፖርት ዘገባ ከሆነ 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በብዙ መልኩ ካለፉት የውድድር ጊዜዎች መሻሻል የታየበት እንደሆነም ተዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የመጀመሪያ ሜዳሊያዋን ያገኘችው በፊንላንዷ ሄልሲንኪ ከተማ በተደረገው የመጀመሪያው ውድድር ነበር፤ በዚህ ውድድር ላይ አትሌት ከበደ ባልቻ በማራቶን ውድድር ሁለተኛ በመውጣት ለሀገሩ እና ለአፍሪካም ጭምር የመጀመሪያውን ሜዳሊያ ማስገኘቱን ታሪክ መዝግቦለታል፡፡ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ደግሞ በጀርመኗ ስቱትጋርት በተካሄደው ሻምፒዮና ላይ በ10 ሺህ ሜትር ሩጫ የኢትዮጵያን የመጀመሪያ የወርቅ ሜዳሊያ አሳክቷል፡፡
ሀገራችን በጃፓን ቶኪዮ በተካሄደው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 36 አትሌቶችን ብታሰልፍም አንድም የወርቅ ሜዳሊያ ሳታገኝ ከዓለም 22ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች፤ ይህ ውጤት ከ32 ዓመት በኋላ ኢትዮጵያ በመድረኩ የወርቅ ሜዳሊያ ሳታገኝ ያጠናቀቀችበት የውድድር መድረክ ሆኖም አልፏል፡፡
ኬኒያውያን እና ኢትዮጵያውያን በስፋት በሚታወቁበት የአምስት ሺህ ሜትር የወንዶች ሩጫ በጃፓኗ ቶኪዮ የነገሡት አሜሪካዊው ኮል ሆከር፣ ቤልጅየማዊው አይዛክ ኪሜሊ እና ፈረንሳዊው ጂሚ ግሬሰር ከወርቅ እስከ ነሐስ ያለውን ሜዳሊያ ተቀራምተውታል፡፡
ኢትዮጵያ እና ኬኒያ በብዛት በሚታወቁበት የ10 ሺህ ሜትር ውድድርም ኢትዮጵያዊው አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ የብር ሜዳሊያ ያገኘ ሲሆን ፈረንሳዊው ጂሚ ግሬሰር የወርቅ፣ ስዊድናዊው አንድሬስ አልምሬን የነሐስ ሜዳሊያ ያጠለቁበት ውድድር ሆኖ አልፏል፡፡ ለወርቅ የተጠበቁት ኬኒያና ኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያውን ማሳካት አልቻሉም፡፡ ፈረንሳዊው ጂሚ ግሬሰር በአምስት ሺህ የነሐስ እና በ10 ሺህ ደግሞ የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማጥለቅ የራሱን ደማቅ ታሪክ በእግሮቹ ጽፏል፡፡
በረጅም፣ በመካከለኛ ርቀትና በመሰናክል ሩጫዎች ስመ ገናና የነበረችው ሀገራችን ከቶኪዮ አንድም ወርቅ ሳታገኝ ለአትሌቲክሳችን ቀይ ከመብራቱ በፊት የሚታየውን የማስጠንቀቂያ ቢጫ መብራት ዓይታ ተመልሳለች፡፡ አትሌቲክሱን የሚመሩት የዘርፉ ኃላፊዎች እና አትሌቶቻችንም ጭምር ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ለምትታወቅበት አትሌቲክስ ትንሳኤ የድርሻቸውን እንዲወጡ እናሳስባለን፡፡
በአትሌቲክሱ መንደር ውጤት ሲታጣ በተለያዩ ግለሰቦች ላይ ጣት ከመቀሰር አባዜ ወጥተን አትሌቲክሳችንን ወደነበረበት የከፍታ ማማ ለመመለስም ሁሉም የድርሻውን ጠጠር መጣል ይኖርበታል፡፡ ተተኪዎች ላይ አለመሥራት፣ የአሠለጣጠን ችግር መኖር፣ የቡድን ሥራ መጥፋት፣ የብሔራዊ ቡድን ተወካዮች አመራረጥና ሌሎችም ምክንያቶች በውጤት ልምሻ ለተመታው አትሌቲክሳችን ያው ምክንያት እንጂ መፍትሔ ስለማይሆኑ መፍትሔው ላይ አተኩሮ መሥራትም ብልህነት ነው፡፡
የ”አረንጓዴው ጎርፍ̋ ዘመን እንዲመለስም በዕውቀት ላይ የተመሠረቱ አሠራሮችን መዘርጋት እንጂ የምክንያት ሰበዞችን መምዘዝ የትም አያደርሰንም፡፡ ነገም ከፊታችን የኦሎምፒክ ውድድሮችና የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው በድጋሚ ስለሚመጡ ከአትሌቲክሱ ውጤት ለሚጠብቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚጠብቀውን ጥሩ ውጤት በማምጣት ደስታውን ትመልሱለት ዘንድም አደራ እንላለን፡፡
በቶኪዮ አዳዲስ እግሮች ክሩን መበጠሳቸውን ስላየንም የሀገራችን ተተኪ አትሌቶች የቀደሙትን አትሌቶች ገድል በእግራቸው እንዲጽፉልን አጥብቀን እንመኛለን፡፡
(እሱባለው ይርጋ)
በኲር የመስከረም 19 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም